በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች በሰኔ ወር በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና መታገታቸውን ኢሰመጉ ገለጸ

ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በሰኔ ወር በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ታፍነው መወሰዳቸውን መንግሥታዊ ያልሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታወቀ።

ተቋሙ ሐሙስ ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች ከሰኔ 6 እስከ 23/2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ቀበሌዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ቢያንስ 10 ሰዎች ተገድለዋል።

በተጨማሪም ከ20 በላይ ሰዎች ታግተው ተወስደው የደረሱበት እንደማይታወቅ እና በርካታ ሰዎች ጥቃቱን በመፍራት አካባቢያውን ለቀው ለመሰደድ እንደተገደዱ አመልክቷል።

እንዲሁም በምስራቅ አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ በሚገኙ ሁለት ቀሌዎች ውስጥ ታጣቂዎች አባት እና ልጅን ሲገድሉ፣ ሦስት ሰዎች አግተው መሰወራቸውን እና ነዋሪዎችም ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ኢሰመጉ መረዳቱን ገልጿል።

በተመሳሳይ በክልሉ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ አቤ ዶንጎሮ ወረዳ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን አማያ ወረዳ፣ ኖኖ እና ሜጫ ወረዳ፣ እሙሩ እና ጃርቲ ወረዳዎች ከሰኔ 20 እስከ 30/2016 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ አካላት እና በአካባቢው ከሚንሳቀሱ የታጠቁ አካላት ጋር በነበረ ግጭት ጉዳት ደርሷል ብሏል።

በግጭቱ ምክንያት ኢሰመጉ ቁጥራቸውን በውል ያላስቀመጣቸው ሰዎች ላይ ግድያ፣ እገታ እና አፍኖ መሰወር የተፈጸመ ሲሆን፣ የአካባቢው ማኅበረሰብም ለከፍተኛ እንግልት እና ምሬት በመዳረጉ ቀየውን ለቆ ለመፈናቀል መዳረጉን አስታውቋል።

ከእነዚህም መካከል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ድንበር ተጠልለው በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ ሐምሌ 9/2016 ዓ.ም. ንጋት በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ንጹሃን ሰዎች የሞት እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የሰብአዊ መብት ተቋሙ ኢሰመጉ አመልክቷል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ “ግድያ፣ እገታ እና አፍኖ የመሰወር ድርጊት በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፋ ነው” ያለው ኢሰመጉ በዚህም የተነሳ የሰዎች በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደኅንነት እና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል።

ለዚህም የሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል መንግሥታት በክልላቸው ውስጥ የሚፈጸሙትን እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ችግሩ እየተስፋፋ እና እየተባባሰ ሕዝቡን ለምሬት እና ለእንግልት እየዳረገው ነው ብሏል።

ኢሰመጉ በመግለጫው ላይ እነዚህን አሳሳቢ እየሆኑ ናቸው ያላቸውን የበርካታ ሰዎች ሕይወት እና ደኅንነትን አደጋ ላይ እየጣሉ ያሉ ድርጊቶችን የፌደራል መንግሥት እና የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ ሕጋዊ ግዴታቸውን በመወጣት እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርቧል።