ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ ልትገነባው ያቀደችው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት በኋላ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታ እንደምትጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማከስኞ ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. አስታውቀዋል።
የኃይል ማመንጫው "የታላቁ የሕዳሴ ግድብን የሚስተካከል" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ለሰላማዊ" ዓላማ ብቻ የሚውል እንደሆነም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት መንግሥታቸው በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ሊሠራቸው ያቀዳቸውን የ30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ኒውክሌር ኃይል ማመንጫው ዝርዝር መረጃ ባይጠቅሱም፤ የኒውክሌር ኃይል ማመጫው የመገንባት ዕቅድ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም።
የካቲት መጨረሻ 2010 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ ከአንድ ወር በፊት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ ከወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር በኒውክሌር መርሃ ግብር እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መስማማታቸው ተዘግቧል።
በ2011 ዓ.ም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርገው ኢትዮጵያ በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ የኒውክሌር ኃይል ማዕከል እና ማብላያ ጣቢያ ልትገነባ መሆኑን ዘግበዋል።
ለግብርና እና ለጤና ዘርፎች ይሆናል የተባለውን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ተጨባጭ እርምጃዎች ተወስደው የነበረ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የኒውክሌር ስምምነት ተፈራርመዋል።
የዚህ ስምምነት ቀጣይ አካል ነው የተባለ የኒውክሌር ፍኖተ ካርታ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና የሩሲያ አውቶሚክ ኃይል ኮርፖሬሽን (ሮሳቶም) በ2015 ዓ.ም.፤ ሁለተኛው ፍኖተ ካርታ ደግሞ በ2017 ዓ.ም. መፈራቸውን አስታውቀዋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ለመገንባት ዘግይታለች ስለሚሉት የኒውክለር ኃይል ማመንጫ እስካሁን ዝርዝር መረጃዎች አላወጡም።
ይሁን እንጂ የዓለም የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአንዴም ሁለት ጊዜ ስለኒውክሌር ኃይል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተነጋግረዋል።
ለመሆኑ ግን የኒውክሌር ኃይል ምንድን ነው?
የኒውክሌር ኃይል ከከሰል አሊያም ከጋዝ እንደሚወጣ ኃይል ተመሳሳይነት አለው። ነገር ግን ሳይንሱ እና የማምረቻ መንገዱ ለየቅል ነው።
የኒውክሌር ኃይል መሠረቱ ሰውን ጨምሮ ሁሉም ቁስ የተገነባበት 'አተም' (Atoms) ነው።
በአጭሩ የኒውክሌር ኃይል አተሞች ለሁለት እና ከዚያ በላይ ተሰባብረው (ኒውክለስ) ሲብላሉ የሚለቁት የኃይል ነው።
በመላው ዓለም ኒውክሌርን በማብላላት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የተለመደ መንገድ ሲሆን፤ ተሰብብረው የተብላሉት አተሞች በሚለቁት ሙቀት የሚፈላው ውሃ እንፋሎት በመፍጠር ተርባይኖችን እና ጀነሬተሮችን በማንቀሳቀስ ኤሌክትሪክ ይመረታል።
የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ (ኒውክሌር ፕላንት) አብላልቶ ሙቀት ለማምረት 'ዩራኒየም-235' የተባለውን ንጥረ ነገር እንደ ነዳጅ ይጠቀማል።
ጣቢያው በውስጡም የኒውክሌር ማብላያዎችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን የያዘ ነው።
ለምን ተመራጭ ሆነ? ስጋቱስ?
የኒውክሌር ኃይል እንደ ሌሎች ታዳሽ ኃይሎች ሳይሆን በቀን ለ24 ሰዓታት አየር ንብረት ሁኔታ ሳይበግረው ኃይል ማመንጨት ይችላል።
በአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ አገራት የኒውክለር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ሲያቋቁሙ የኒውክሌር ኃይል በሚሰጠው ያልተገደበ አቅም ላይ ዓይናቸውን ጥለውበታል።
በአንድ ኪሎ ግራም ዩራኒየም የሚመረት የኒውክሌር ኃይል በከሰል ከሚመረተው ኃይል በ20 ሺህ እጥፍ የሚበልጥ ኃይል መሆኑ የዓለም የወደፊት የኃይል ምንጭ እንዲባል አስችሎት ነበር።
ዝቅተኛ ካርቦን ልቀት ያለው የኒውክሌር ኃይል፤ የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት በተለይም ከሌሎች ታዳሽ ኃይሎች በለጠ ተጨባጭ ሆኖ ይታያል።
አስተማማኝ መሆኑም ተመራጭ እንዲሆን ያስቻለው ሲሆን፤ በተለይን 'አዲስ ትውልድ' የሚባሉት የኒውክሌር ማመንጫ ጣቢያዎች ከከሰል አሊያም ከጋዝ ማመንጫ ጣቢያዎች በበለጠ እስከ 80 ዓመት መሥራት የሚችሉ ናቸው።
ነገር ግን ይህ ቴክኖሎጂ የተጣለበት ዓይኖችን ወደ ስጋት ለመቀየር ጥቂት አስርት ዓመታት ብቻ ነው የፈጀበት።
በአውሮፓውያኑ 1986 የተከሰተው የቼርኔቤል ኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የደረሰው አደጋ በመላው አውሮፓ 'የሬዲዮአክቲቭ' ብክለት ማሠራጨቱ በፍርሃት እንዲታይ አድርጎታል።
በአውሮፓውያኑ 2011 የጃፓኑ ፉኩሺማ ማመንጫ አደጋ ደግሞ በነበረው ፍርሃት ላይ የተጨመረ ሌላ ስጋት ሲሆን፤ ጃፓንን እና ጀርመንን ጨምሮ በርካታ አገራት ጣቢያዎቻቸውን ዘግተው ወደ ሌሎች የኃይል ምንጮች ፊታቸውን እንዲያዞሩ አድርጓል።
የደኅንነት፣ የዋጋ እንዲሁም ከማመንጫው የሚወጣው የተበከለው ዝቃጭ የት ይገባል የሚል ስጋት የኃይል አብዮት በተባለው የኒውክሌር ኃይል ላይ የነበረውን ተነሳሽነት ላይ ውሃ የቸለሱ ምክንያቶች ናቸው።
በዚህም የተነሳ እንደ ዓለም አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ መረጃ ከ2011 እስከ 2020 ባሉ ዓመታት ብቻ በመላው ዓለም 49 ጊጋ ዋት ኃይል ታጥቷል።
ይሁን እንጂ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኒውክሌር ኃይልን ዳግም ለመመለስ ጥረቶች የተጀመሩ ሲሆን፤ እንደ ማይክሮሶፍት፣ ጉግል እና አማዞንን የመሰሉ የዓለማችን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት ይህንን ኃይል ለማልማት በጀት መድበዋል።
የትኞቹ የአፍሪካ አገራት የኒውክሌር ኃይል ያመነጫሉ?
ከዓለም ከፍተኛ የኒውክሌር ኃይል በማምረት ቀዳሚዋ አገር አሜሪካ ስትሆን፤ የኒውክሌር ኃይል ከአጠቃላይ የኃይል አቅርቦቷ 19 በመቶውን ይሸፍናል።
ፈረንሳይ ከቻይና በመቀጠል የዓለም ሦስተኛዋ ከፍተኛ ኒውክሌር ኃይል አምራች ስትሆን፤ ከአጠቃላይ የኃይል አቅርቦቷ 67 በመቶ በላይ ኃይሏን ከኒውክሌር ኃይል በማግኘት ቀዳሚዋ አገር ናት።
ከአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው አሁን ላይ 33 የሚሆኑ አገራት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ አላቸው።
የኒውክሌር ኃይል ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው ሩሲያ የዓለም አራተኛ ኒውክሌር ኃይል አምራች አገር ስትሆን 26 ማብላያ ጣቢያዎች አሏት።
ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም የኒውክሌር ኃይል የሚመነጨው በአምስት አገራት ውስጥ ነው።
ከዓለም ዝቅተኛ የኃይል አቅርቦት ያላት አህጉረ አፍሪካ ክፍተቱን ለመሙላት ወደ ኒውክሌር ኃይል እየተራመደች ይመስላል።
ደቡብ አፍሪካ የአህጉሪቱ የመጀመሪያው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ያላት አገር ስትሆን፣ ሁለት ጣቢያዎች አሏት።
ግብፅ ሁለተኛዋ አፍሪካ አገር ለመሆን በሜዲትራኒያን ባሕር አቅራቢያ ኤል ዳባ በተባለ አካባቢ 4.8 ጊጋ ዋት የሚያመነጭ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እየገነባች ነው።
የኒውክሌር ጣቢያ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመው የሩሲያው መንግሥታዊ ድርጅት ሮሳቶም ግንባታውን እያካሄደ ሲሆን፤ ጣቢያውን ለ10 ዓመታት እንደሚያስተዳደርም ዘገባዎች ያመለክታሉ።
በአፍሪካ እያደገ ያለው የሩሲያ ተሳትፎ በርካታ አገራት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎችን ለመገንባት ዝንባሌ እንዲያድርባቸው እያደረገ ይመስላል።
የሩሲያ አቶሚክ ኃይል ኮርፖሬሽን (ሮሳቶም) በቅርብ ዓመታት ለናይጀሪያ እና ለሱዳን ኒውክሌር ኃይል ልማት ዕቅድ መንደፉ ተዘግቧል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደ ጋና፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ሞሮኮ ያሉ አገራትም የኒውክሌር የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
'ኒውክሌር ለአፍሪካ' የተባለ ተሟጋች ድርጅት መሥራች የሆኑት ፕሬንሰስ ሙቶምቢኒ ኢንዱስትሪያቸውን ለማሳደግ ለአፍሪካ አገራት ኒውክሌር ፍቱን መፍትሔ ነው ብለው ያምናሉ።
ምንም እንኳ ከዚህ ኃይል የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ ቢሆንም፤ ጣቢያውን ለመገንባት ግን ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይጠይቃል።
ለዚህም ይመስላል በአፍሪካ አንድ ብቻ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ በደቡብ አፍሪካ የተገነባው።
የኢትዮጵያን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ወጪን የሩሲያ አቶሚክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንዲሸፍን አሊያም ከሩሲያ ባንኮች ብድር ለማግኘት ንግግሮች እተካሄደ መሆኑን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።