በዩኬ የተደራጀ የወንጀል ቡድን መሪው 1 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲከፍል ወይም ተጨማሪ እስር እንደሚጠብቀው ተወሰነ

አየርላንዳዊው ቶማስ ካቫናግ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በዩኬ ኪንሃን የተሰኘው የተሰኘ የተደራጀ የወንጀል ቡድን የሚመራው ግለሰብ 1 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲከፍል ያለበለዚያ ተጨማሪ የእስር ቅጣት እንደሚጠብቀው ውሳኔ መሰጠቱን አቃብያነ ህግ ገለጹ ።

የቡድኑ መሪ የ57 ዓመቱ አየርላንዳዊው ቶማስ ካቫናግ በአውሮፓውያኑ 2022 ኮኬይንን ጨምሮ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር 21 ዓመት እስር የተፈረደበት ሲሆን ፤ በቀጣዩ ሶስት ወራት ውስጥ የተቀመጠውን ገንዘብ የማይከፍል ከሆነ 12 ዓመት ተጨማሪ እስር እንደሚጠብቀው መበየኑን አቃብያነ ህጉ ተናግረዋል።

ከአውሮፓ የሚመጡ አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር መረብንን በዩናይትድ ኪንግደም በዋናነት ይመራል የተባለው ኪንሃን የተሰኘው ይህ ቡድንን የሚመራው ካቫናግ 30 ሚሊዮን ፓውንድ ሃብት እንዳለው ይገመታል።

ካቫናግ 12.3 ሚሊዮን ፓውንድ እና ተባባሪው ጌሪ ቪኬሪ 10.1 ሚሊዮን ፓውንድ በዚህ የወንጀል ተግባራቸው ማፍራት እንደቻሉ በዳኛ መገመቱን አቃቤ ህግ አስታውቋል።

በኢፕስዊች ፍርድ ቤት የሚገኙ ዳኛ በካቫናግ ንብረት ላይ ተመስርተው 1. 1ሚሊዮን ፓውንድ ገደማ እንዲከፍል ያዘዙት ሲሆን ይህም፤ በታምወርዝ የሚገኘው ቅንጡ ቤቱ 50 በመቶ፣ በዩኬ ከሚገኙ ሌሎች ንብረቶች ሽያጭ፣ በስፔን የሚገኝ ቪላ እንዲሁም 150 ሺህ ፓውንድ በጣም ውድ ከሆኑ አልባሳት እና ምርቶች እንዲከፍል ትዕዛዝ መስጠታቸውን የብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ አስታውቋል።

ካቫናግ በአደንዛዥ ዕጾች እና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎች ጥፋተኝነቱን ካመነ በኋላ የተፈረደበት በአውሮፓውያኑ 2022 ነበር።

ሌላኛው ተባባሪው ቪከሪ በበኩሉ 109 ሺህ ፓውንድ ገደማ በሶስት ወር እንዲከፍል ያለበለዚያ ተጨማሪ ሁለት ዓመታትን በእስር እንደሚያሳልፍ ውሳኔ ተላልፎበታል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ችሎቶች ኦደማዝ ፒጌ የተሰኘ 75 ሺህ ፓውንድ የሚያወጣ ሰዓት፣ እንዲሁም በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት በሆቴሉ የተያዘው 100 ሺህ ዩሮ በላይ ገንዘብ እንዲከፍል ትዕዛዝ መተላለፉን ነው አቃብያነ ህጉ የገለጹት።

ካቫናግ ከዚህ ቀደም ከተጣለበት የእስር ቅጣት በተጨማሪ በተመሳሳይ ጊዜ የሚቆጠር የስድስት ዓመታት እስር ባለፈው ዓመት ተፈርዶበታል።

ለዚህም በሚሊዮኖች ፓውንድ የሚገመተውን የአደንዛዥ ዕጽ ኢንተርፕራይዝ ወንጀል ቀላል የእስር ቅጣት እንዲፈረድባቸው በሚል የብሔራዊ ወንጀል ኤጀንሲ መኮንንኖችን በማታለል ወደተቀበሩ 11 የጦር መሳሪያዎች ለመምራት አሲሯል በሚል ነበር የተፈረደበት። መሳሪያዎቹን ሆን ብሎ በሰሜናዊ አየርላንድ በመቅበር እና ለፖሊስ የሚገኙበትን ቦታ በመጠቀም በሃሰተኛ መንገድ መሳሪያዎች የተገኙ አስመስሏል በሚል ወንጀል ነበር የተከሰሰው።

ሴራውን ከእስር ቤት አቀነባብሯል የተባለው ካቫናግ መኮንኖቹን ሆን ብሎ ለማታለልም የወንድሙ ሊያን ባይረን እና ተባባሪው ሻውን ኬንት እጅ እንዳለበት ተናግሯል።

ባይረን በዚህ ሴራ አምስት ዓመት ሲፈረድቤት ኬንት ደግሞ ስድስት ዓመት ተፈርዶበታል።