ከኢትዮጵያ እና ከኢንዶኔዢያ የአውሮፕላን አደጋዎች ጋር በተያያዘ ቦይንግ ላይ የቀረበው ክስ ሊነሳ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ እና የኢንዶኔዢያ አየር መንገዶች ላይ ከደረሱት ሁለት 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች የመከስከስ አደጋዎች ጋር በተያያዘ በአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ላይ የቀረበውን የወንጀል ክስ የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ውድቅ ሊያደርግ ነው።
በሁለቱ አደጋዎች ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች ቤተሰቦች ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት ከተደረገ ስብሰባ በኋላ የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት እንዳሉት ቦይንግ ክሱ ውድቅ ሆኖ ጉዳዩን በስምምነት ለማጠናቀቅ የሚያስችለውን ሁኔታን እያጤኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ውሳኔም የተሰማው ፍርድ ቤት ቀደም ሲል ቦይንግ ጥፋተኝነቱን አምኖ ከስምምነት ለመድረስ የቀረበውን ሃሳብ ፍርድ ቤት ውድቅ ካደረገው በኋላ የቀረበበት የማታለል ወንጀል ክስ በሚቀጥለው ወር መታየት ከመጀመሩ በፊት ነው።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ እና ኢንዶኔዢያ ውስጥ በደረሱት አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቤተሰቦች ጠበቆች በአዲሱ ዕቅድ "በጣሙን መከፋታቸውን" ገልጸዋል።
"ምንም እንኳን የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ቢገልጽም፣ በጽሁፍ የቀረበው ሰነድ ግን የመጨረሻ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ያመለክታል" ሲሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የሞቱ 34 ሰዎች ቤተሰብን የወከለው ድርጅት ጠበቃ ኤሪን አፕልበም ተናግረዋል።
ጨምረውም "ቦይን የእምነት ቃሉን በሰጠባቸው ወንጀሎች ምክንያት ለጠፉ 346 ሰዎች ሕይወት አስካሁን ለፍርድ አልቀረበም። አሁን ደግሞ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ከገንዘብ ቅጣት ያላለፈ ቅጣት ሳያገኘው እንዲያመልጥ ሊያደርገው ነው" ብለዋል።
ከስድስት ዓመታት በፊት በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ አየር መንግድ እና በኢንዶኔዢያው ላየን ኤር አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ በደረሱ ሁለት አሰቃቂ አደጋዎች ምክንያት ቦይንግ በአሁኑ ጊዜ የማጭበርበር ክሶች ቀርበውበታል።
እጅግ ዘመናዊ ናቸው በተባሉት ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ የደረሱት አደጋዎች የሞቱት ሰዎች 346 ሲሆን፣ ምክንያታቸውም አብራሪዎች በአውሮፕላኖቹ ላይ መገጠማቸውን የማያውቋቸው በተገቢው ሁኔታ ያልተሠሩ የበረራ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ናቸው ተብሏል።
ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ቦይንግ የአውሮፕላን መቆጣጠሪያ ሥርዓቱን የተመለከተ ወሳኝ መረጃን ሆን ብሎ ከተቆጣጣሪዎች ደብቋል ብሎ የማጭበርበር ክስ መስርቶበታል።
ቦይንግ መጀመሪያ ላይ የቀረበበትን ክስ ያመነ ሲሆን ቅጣት የሚያስከትል ክስ እንዳይቀርብበት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል እና የአውሮፕላኖቹን የደኅንነት ደረጃ ለማሻሻል ቃል ገብቶ ነበር።
ነገር ግን ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ 737 ማክስ አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ በሩ ተገንጥሎ ከወደቀ በኋላ ክሱ በድጋሚ ተከፍቷል። የፍትህ መሥሪያ ቤቱም ቦይንግ የተደረሰውን የስምምነት ነጥቦችን አላከበረም በሚል ክስ አቅርቦበታል።
ባለፈው ዓመት ደግሞ ቦይንግ ለቀረበበት የማጭበርበር ክስ ጥፋተኝነቱን በማመን ተጨማሪ 243 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ለመክፈል እና ፍርድ ቤት ሥራውን የሚቆጣጠር አካል ለተወሰነ ጊዜ እንዲሰይም ከአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ጋር ከስምምነት ላይ ደርሷል።
ነገር ግን ባለፈው ታኅሣሥ ቦይንግን የሚቆጣጠረው አካል እንዴት እንደሚሰየም አጠያያቂ ነው በማለት ጉዳዩን የሚከታተሉ አንድ ዳኛ ከዐቃቤ ሕግ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ውድቅ አድርገውት ነበር።
በዚህም ምክንያት በፕሬዝዳንት ባይደን ዘመን የተጀመረው ሂደት ጉዳዩን ቀለል ባለ የሕግ ሂደትን እንሚይዙት ቃል ወደገቡት የፕሬዝዳንት ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ለመሸጋገር በቅቷል።
በቦይንግ ላይ የቀረበው ክስ ሊነሳ ስለመሆኑ አውሮፕላን አምራቹ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ ሲሆን፣ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱም ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
እንዲህ ያለው ክስ ውጪ የሚደረስ ስምምነት የቀረቡ የወንጀል ክሶችን ማመን አይጠይቅም። ይህም ቦይንግን ከወንጀል ማኅደር ውስጥ እንዳይካተት ያደርገዋል።















