የያዘን ጉንፋን ይሁን ኮቪድ እንዴት መለየት እንችላለን ? እንዳይባባስ ባለሙያዎች ምን ይመክራሉ?

አልጋዋ ላይ በነጭ የአልጋ ልብስ ተጠቅልላ ቁጭ ያለችና አረንጓዴ ኩባያ የያዘች ሴት።ሴትዮዋ ጥቁር ፀጉር ያላት ሲሆን ወደ መሬት እየተመለከተች ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳል፣ የድምፅ መሻከር እና የጉሮሮ መከርከር ገጥሟችሁ ያውቃል?

እንዲህ ዓይነት ምልክቶች ያሏቸው በቫይረስ የሚመጡ እንደ ጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ያሉ በሽታዎች በየትኛውም ጊዜ ሊያጋጥማችሁ ይችላል።በተለይ ደግሞ በቀዝቃዛ ወቅት በስፋት ይከሰታሉ።

ሆኖም ምልክታቸው ተመሳሳይነት ስላለው አንዳንዴ ለየትኛው በሽታ እንደተዳረግን ግራ እንጋባለን። ለጉንፋን፣ ለኢንፍሉዌንዛ ወይስ ለኮቪድ? እንዴት ልንለያቸው እንችላለን?

የሕክምና ዶክተር እንዲሁም የቢቢሲ ሞርኒንግ ላይቭን ጨምሮ በሌሎች ፕሮግራሞች አቅራቢ የሆነው ዶክተር ኦስካር ዳክ በዚህ ዙርያ የተወሰኑ ምክሮችን ይሰጠናል።

ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ ለጉንፋን ያጋልጣል?

ታዳጊ ልጁን ጭኑ ላይ አስቀምጦ አፍንጫዋን የሚያፀዳ አባት።ታዳጊዋ ቢጫ ቀሚስ የለበሰች ሲሆን አባቷ ደግሞ ጥቁር የዓይን መነጽር እና ካኪ ቀለም ያለው ካናቴራ ለብሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ የበሽታ መከላከል ሥርዓታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድር እንደሆነ የሚያሳዩ ግልጽ ጥናቶች የሉም።

ሆኖም ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ እና የበሽታ መከላከል ሥርዓት መዳከም በተዘዋዋሪም ቢሆን ይገናኛሉ።

በጣም ቀዝቃዛ በሆነ የአየር ጠባይ ወቅት ሙቀት ለማግኘት ስንል ተደርድረን የመቀመጥ፣ የመጠጋጋት እና በቤት ውስጥ የማሳለፍ ሁኔታዎች አሉ። እንዲህ ዓይነት አካባቢ ደግሞ ለቫይረስ መዛመት ምቹ ነው።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ አንዳንድ አገራት ደግሞ ታዳጊ ሕፃናት ከበጋ እረፍት በኋላ ወደ ትምህርት ቤት የሚመለሱት በቀዝቃዛ ወቅት ነው።

ትምህርት ቤቶችና የሕፃናት ማቆያዎች ደግሞ ቫይረሶች በቀላሉ የሚዛመቱባቸው ሥፍራዎች ሲሆኑ፤ ሕፃናቱም እነዚህን ጀርሞች ተሸክመው ወደ ቤት ይሄዳሉ።

በዚህ ወቅት ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ አዲስ ተማሪዎችም ከሌሎች ጋር በሚቀላቀሉበት ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ ጀርሞች ይዛመታሉ። በዚህ ላይ አብዝቶ የአልኮል መጠጥ መጠጣት እና 'ፓርቲ' [የመዝናኛ ድግሶች] ሲጨመሩበት የበሽታ መከላከል ሥርዓትን ያዳክማሉ።

ጉንፋን፣ ኢንፍሉዌንዛ ወይስ ኮቪድ?

የጉንፋን ፣የኢንፍሉዌንዛ እንዲሁም ከበድ ባለ ቫይረስ የሚከሰተው ኮቪድ ምልክቶቻቸው ተቀራራቢ ናቸው።

ሆኖም በየትኛው እንደተያዝን ለመለየት የሚረዱን ጥቂት ፍንጮች አሉ።

ጉንፋን ከሆነ የህመም ስሜቱ እየተሰማን የሚሄደው ቀስ በቀስ ነው። መጀመሪያ አፍንጫችንን እና የጉሮሯችንን መጨረሻ ነው የሚያጠቃን።አንዳንዶች በአፋቸው መጨረሻ የማሳከክ ስሜት ይሰማቸዋል።

ሌላኛው ምልክት ደግሞ በጆሯችሁ ላይ የመደፈን ስሜት መሰማት ነው። ቫይረሱ እየተሰራጨ ከሄደ ወደ ሳንባችን ሊደርስ የሚችል ሲሆን ሳንባችን ጋር ከደረሰ ሳል ይፈጥራል። በአብዛኛው እነዚህን ስሜቶች የተለመዱ አድርገን ስለምንቆጥራቸው ከተለመደው እንቅስቃሴያችን አያስተጓጉሉንም።

አልጋ ላይ የተኛ አንድ ግለሰብ በግራ በኩል ፊቱን በእጁ ይዞ ይታያል።ግለሰቡ ጠቆር ያለ አረንጓዴ ቀለም ያለው ካናቴራ ልብሷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢንፍሉዌንዛም ተመሳሳይ ምልክት ያለው ሲሆን ቁርጥማት ፣ ትኩሳት እና የጡንቻ መዛል ያስከትላል።

አልጋ ላይ ባይጥላችሁም እንደዚያ ዓይነት ስሜት እንዲሰማችሁ ሊያደርግ ይችላል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ኮቪድ ከኢንፍሉዌንዛ ጋር የሚመሳሳሉ ምልክቶች ስላሉት ነገሮች የባሰ እንዲወሳሰቡ አድርጓል።

ሆኖም ኮቪድ ከሌሎቹ የሚለይበት ቁልፍ ምልክት አለው። ይህም የማሽተት ወይም የመቅመስ ችሎታችንን ማጣት ነው።

በክረምት ወቅት 'ስትራተስ' እና 'ኒምበስ' የተባሉ አዳዲስ ዝርያዎችም ተከስተው የነበረ ሲሆን፣ ከባድ የጉሮሮ መከርከር ምልክቶች ነበራቸው።ተቅማጥም የተለመደ ነው።ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ምልክቶች ካሏችሁ ቤት መሆን፣ማረፍ እና ማገገም ይመከራል።

ነገር ግን ሥር የሰደደ በሽታ ካለባችሁ፣ የትንፋሽ ማጠር ወይም ከሦስት ሳምንት በኋላ ህመሙ እየቀለላችሁ ካልመጣ ወደ ሐኪም ለመሄድ ማመንታት የለባችሁም።

ራሳችንን ማከም እንችላለን?


የተለያየ ቀለም ያላቸው ኪኒኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰውነታችን በተፈጥሮው ቫይረሶችን እና ኢንፌክሽኖችን ይዋጋል።ሆኖም በትክክለኛው መድሃኒት ልናግዘውም እንችላለን።

  • ፓራሲታሞል፡ ይህን መድሃኒት መውሰድ ችግር የለውም።ፓራሲታሞል አሊያም 'አይቡፕሮፊን ማስታገሻዎች ናቸው። እነዚህ መድሃኒቶች ትኩሳታችንን ለማብረድ፣ ህመምን ለማስታገስ ጠቃሚ ናቸው። ሆኖም ከሚፈቀደው በላይ መውሰድ የለባችሁም።
  • ቫይታሚን ሲ፡ ብዙውን ጊዜ ቫይታሚን ሲ ጉንፋንን ለመከላከል እንደሚረዳ እናስባለን።ይህንን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች ግን የሉም።በመሆኑም የቫይታሚኑ እጥረት ከሌለባችሁ በስተቀር ጤናማ እና የተመጣጠነ ምግብ ላይ ማተኮሩ ወሳኝ ነው።
  • ቫይታሚን ዲ ፡ በክረምት ወራት ፀሐይ የምትወጣበት ሰዓት በሚቀንስባቸው እንደ ዩኬ ባሉ አገራት ቫይታሚን ዲ መውሰድ ይመከራል።
  • የተዘጋ አፍንጫን ለመክፈት የሚረጭ ፈሳሽ [ ዲኮንጀስታንት ስፕሬይ] ፡ይህ መድሃኒት ወዲያውኑ ህመማችን እንዲታገስልን የሚያደርግ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ይህን ስፕሬይ የምንጠቀም ከሆነ ሊላመድ እና ሥር የሰደደ የመተንፈሻ አካል መዘጋት ሊያስከትል ይችላል። አፍንጫችን ለመድሃኒቱ ጥገኛ በመሆን መድሃኒቱን ካልተጠቀምን እብጠት ሊያመጣ ይችላል።በመሆኑም ይህን መድሃኒት ከአራት ወይም ከአምስት ቀን በላይ መጠቀም አይመከርም።
  • የዶሮ ሾርባ፡ ይህ ምግብ ቫይረስን እንደሚዋጋ የሚያሳዩ ጥቂት መረጃዎች አሉ።ሆኖም ጉሮሯችንን የሚያሞቅልን እና ምልክቶችን የሚያቀልልን ሙቀቱ ነው።ስለዚህ ሌሎችም ቢሆኑ በቂ ፈሳሽን መውሰድ ጠቃሚ ነው።

ክትባትስ?

ክትባት የምትከተብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ የሚከሰቱ ከባድ ህመሞች እና ኢንፌክሽኖችን ለመከላከል ክትባት ውጤታማው መንገድ ነው።

ኢንፍሉዌንዛ በሽታን የሚያስከትለው ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ በየጊዜው ራሱን ይለውጣል።በመሆኑም አዳዲስ ዝርያዎችን ለመዋጋት ክትባቶች በየዓመቱ ይሻሻላሉ። ዶክተር ኦስካር እንደሚለው ክትባቱን ከዚህ ቀደም ካልወሰዳችሁ ዓመታዊውን የጉንፋን ክትባት መውሰድ ጠቃሚ ነው።

ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑት ቅድሚያ ለመስጠት ክትባቱን መውሰድ የሚችሉት ሰዎች እንደየ አገራቱ ይለያያል።

የአውሮፓ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል እንደሚለው ሥር የሰደደ የጤና ችግር ላለባቸው፣ ለነፍሰጡር ሴቶች፣ ከ6 ወር እስከ አምስት ዓመት ላሉ ሕፃናት፣ አረጋውያን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከጉንፋን ጋር በተያያዘ ውስብስብ የጤና እክል ለሚያጋጥማቸው ሰዎች ክትባቱ ወሳኝ ነው።