ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ጋር ከተወያዩ በኋላ ምንም ዓይነት ስምምነት ባይፈራረሙም "ድንቅ" ነበር ሲሉ አሞካሽተዋል

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት እና የቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ከስድስት ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በደቡብ ኮሪያ ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ "ድንቅ ውይይት" ማካሄዳቸውን ገለፁ።

የሁለቱ ፕሬዚዳንቶች መገናኘት እና መነጋገር በመካከላቸው የተፈጠረውን የንግድ መካረር ያረግባል የሚል ተስፋ ፈጥሯል።

ዶናልድ ትራምፕ በደቡብ ኮሪያ ከታካሄደው ውይይት በኋላ "ድንቅ ነበር" ሲሉ ቤይጂንግ በበኩሏ "ዋና የንግድ ጉዳዮችን" ለመፍታት ከመግባባት ላይ ተደርሷል ብላለች።

ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና ወደ አገራቸው በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ገብቶ ቻይና ተመሳሳይ እርምጃ እንድትወስድ አድርጓታል።

ሁለቱ አገራት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ከስምምነት ላይ ቢደርሱም ውጥረቱ ግን እንደቀጠለ ነበር።

ሐሙስ ዕለት በደቡብ ኮሪያ ያካሄዱት ውይይት ይፋዊ ስምምነት ላይ እንዲደርስ ያደረገ ባይሆንም መንገዶችን ግን የጠረገ ነበር ተብሏል።

በስብሰባው ወቅት የተነሱ ጉዳዮች እና መግባባት የተደረሰባቸው የትኞቹ እንደሆኑ ግን እስካሁን ድረስ በይፋ አልተገለጸም።

የንግድ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ለዓመታት የሚካሄዱ ንግግሮች እና ድርድሮችን ይጠይቃሉ።

የዓለም አገራት ከዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ታሪፍ በኋላ ያሉትን ክፍተቶች ለመፍታት ወዲያውኑ እርምጃ ሲወስዱ ታይተዋል።

ከፍተኛ ታሪፍ ከተጣለባቸው የአሜሪካ ቁልፍ የንግድ አጋሮች መካከል የተወሰኑት የሚገኙት በእሲያ ሲሆን ትራምፕ ባለፉት ቀናት በርካቶቹን አግኝተው የማነጋገር አጋጣሚውን አግኝተዋል።

ቻይና የብርቅዬ ማዕድናት ወጪ ንግድ ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር ለማንሳት ቃል የገባች ሲሆን ይህም አሜሪካ ከስማርት ስልኮች እስከ ተዋጊ ጄቶች ለማምረት የሚያስፈልጓትን ማዕድናት እንድታገኝ ያደርጋታል።

ይህ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዢ ጋር ከነበራቸው ውይይት በኋላ የተገኘ ውጤት ተደርጎ ተወስዷል።

በውይይቱ ደስተኛ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኤር ፎርስ ዋን እየሄዱ ለጋዜጠኞች ቻይና "ከፍተኛ መጠን ያለው የአኩሪ አተር እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን " እንድትገዛ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ቻይና የዶናልድ ትራምፕን ታሪፍ ተከትሎ ከፍተኛ ቀረጥ ከጣለችባቸው የአሜሪካ የግብርና ምርቶች መካከል አንዱ የአኩሪ አተር ሲሆን ይህም የአሜሪካ ገበሬዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል ተብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ሐሙስ ዕለት ባደረጉት ውይይት በቻይና ላይ የጣሉትን ታሪፍ ለመቀነስ ቤጂንግ በበኩሏ ሕገወጥ የፌንታኒል ንግድን ለመግታት መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቻይና የአሜሪካን የአኩሪ አተር መግዛቷን የምትቀጥል ሲሆን ብርቅዬ የምድር ማዕድናትን ወደ ውጭ መላኳንም ትቀጥላለች።

ትራምፕ ከደቡብ ኮሪያ ለመውጣት የኤር ፎርስ ዋን አውሮፕላናቸውን እየተሳፈሩ ከፕሬዚዳንት ዢ ጋር የነበራቸውን ውይይት "በጣም ድንቅ ውይይት ነበር" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው "ከ10፣ 12 እሰጠዋለሁ" ብለዋል።

ትራምፕ ከቻይና ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣለው ታሪፍ ከ57 በመቶ ወደ 47 በመቶ እንደሚቀንስና ከፌንታኒል ንግድ ጋር በተገናኘ የታሪፍ መጠን በግማሽ ወደ 10 በመቶ ይቀንሳል ብለዋል።

ቻይና በበኩሏ መኪና፣ አውሮፕላን እና ጦር መሣሪያ ለማምረት የሚውሉ ብርቅዬ ማዕድናት ላይ የምትደርገውን የወጪ ንግድ ቁጥጥር እንደምታነሳ ተገልጿል።