ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ብራዚል. . .በዓለም አቀፍ ቱሪስቶች እንዲመረጡ ያደረጋቸው ምሥጢር ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ከመቼውም በላይ እየተነቃቃ ነው። በአውሮፓውያኑ በ2025 1.5 ቢሊዮን ቱሪስቶች የተለያዩ አገራትን ጎብኝተዋል። በአገራቱ ዝርዝር ከተካተቱ መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናት።
የተባበሩት መንግሥታት ባስቀመጠው የዓለም አቀፍ የቱሪዝም መለኪያ መሠረት ጉብኝቶች በ4 በመቶ ጨምረዋል። ይህም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ከነበረው ጋር የሚነጻጸር ነው።
በዓለም ከፍተኛ ጎብኚዎች የምታስተናግደው አውሮፓ ናት። በ2024 ከነበረው የጎብኚዎች መጠን የአምናው 6 በመቶ ጨምሯል።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ 800 ሚሊዮን ሰዎች አውሮፓን ጎብኝተዋል።
በርካታ ቱሪስት ካስተናገዱ አገራት መካከል በጎብኚዎቻቸው ቁጥር በቅደም ተከተል የተቀመጡት ብራዚል (37%)፣ ቡታን (30%)፣ ግብፅ (20%)፣ ኢትዮጵያ (15%) እና ሲሸልስ (13%) ይጠቀሳሉ።
ሬቪጎርቴ የተባለው አስጎብኚ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ስቲቨን ቪጎር "እነዚህ አገራት እንደ መዳረሻ በመወሰድ ረገድ ታዋቂ እየሆኑ መጥተዋል" ይላል።
ዎርልድ ቱሪዝም ባሮሜትር (World Tourism Barometer) በተሰኘው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ እና የቱሪዝም ፍሰታቸው ከፍተኛ የሆኑ አገራትን በዝርዝር እንመለከታለን።
ኢትዮጵያ
በአውሮፓውያኑ በ2025 የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መጠን በ15 በመቶ ጨምሯል።
በአፍሪካ ውስጥ ካለው ጠቅላላ የቱሪዝም ዕድገት የኢትዮጵያ 8 በመቶውን ድርሻ ይዟል።
በዝርዝሩ ውስጥ ከፍተኛ ቀጣናዊ የቱሪዝም ዕድገት ከተስተዋለባቸው አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
በትግራይ ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየው ቱሪዝም በረራዎች ከተከፈቱ በኋላ ማገገሙ ተገልጿል።
በኢንቨስትመንት በኩል ካለው መሻሻል በተጨማሪ ተጓዦች ወደ ኢትዮጵያ እያቀኑ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ 'ቪዚት ኢትዮጵያ' ያሉ ንቅናቄዎች እንዲሁም የሆቴሎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጭዎች መሻሻል የቱሪስቶች ፍላጎት ከፍተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የኒውፓዝ ኤክስፒዲሽን አስጎብኚ ድርጅት መሥራች ዮርግ ሳላስ-ጉቬራ "ለረዥም ጊዜ ደንበኞቻችን የሆኑ ተጓዦች ወደ ኢትዮጵያ የመሄድ ፍላጎታቸው ጨምሯል። ለዓመታት የጉዞ ዕቅዳቸውን ሲለውጡ የቆዩ ቱሪስቶችም አሁን ላይ ለመጓዝ ዝግጁ ናቸው" ይላል።
የተለያዩ የአደባባይ ክንውኖች የሚማርኳቸው ወጣት ተጓዦች ቁጥር ከፍተኛ እየሆነ እንደመጣም ያስረዳል።
የቲምቡክቱ አስጎብኚ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ጆኒ ፕሪንስ እንደሚለው፤ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2024 እስከ 2025 ባሉት ወራት ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ያለው ፍላጎት 40 በመቶ አንሰራርቷል።
"ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እና ወደ ግብፅ ያለ ፍርሃት መጓዝ ጀምረዋል። በዚህ ዓመት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የተመዘገቡ የትምህርት ቡድኖች ከ20 በላይ ናቸው" ሲል ያስረዳል።
ኢትዮጵያ በተለይም የቅሪ አካል ምርምር፣ የሥነ ሰብ ጥናት እንዲሁም ተፈጥሮ ለሚማርካቸው ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ መሆኗን ሳላስ-ጉቬራ ያስረዳል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር ቤተ መንግሥቶች እና ስሜን ተራሮች ዋነኛ መዳረሻ ናቸው።
በስሜን ተራሮች ጭላዳ ዝንጀሮን የሚጎበኙ እና ወደ ኦሞ ሸለቆ የሚጓዙ ጎብኚዎች በርካታ ናቸው።
በኢትዮጵያ ዘመናትን ያስቆጠሩ ባህላዊ ክንውኖች ለመመልከትም ቱሪስቶች ይጓዛሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ግብፅ
በግብፅ ያለው የቱሪስት ፍሰት 20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከኮሮናቫይስ በኋላ ቱሪዝማቸው በፍጥነት ካገገመ አገራት መካከል ትጠቀሳለች።
ሳላስ-ጉቬራ እንደሚለው፤ ለረዥም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የግብፅ ትልቁ ሙዚየም መከፈት ቱሪስቶችን እየሳበ ነው።
"ከ20 ዓመት በላይ ሲጠበቅ የቆየ ሙዚየም ነው። ሙዚየሙ እስኪከፈት ሲጠብቁ የነበሩ እና ሌሎች መዳረሻዎችን ለመጎብኘት ዕቀድ የያዙ ቱሪስቶችም እየመጡ ነው" ይላል።
ሙዚየሙ ፒራሚዶች አቅራቢያ የሚገኝ መሆኑ ለቱሪስቶች ቀላል አድርጎታል።
ፕሪንስ እንደሚለው፤ በግብፅ የቱሪስቶች ቁጥር 50 በመቶ የጨመው እንደ አውሮፓውያኑ ከ2024 እስከ 2025 ባሉት ወራት ነው።
ግብፅ ለቱሪስቶች ደኅንነቱ የተጠበቀ አገር መሆኑ ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር እንዲጓዙ እና ሴቶችም ብቻቸውን ወደ አገሪቱ እንዲያቀኑ ምክንያት ሆኗል።
በአውሮፓውያኑ 2027 የፀሐይ ግርዶሽን በግብፅ ለማየት እየተጠባበቁ የሚገኙ ቱሪስቶችም ይጠቀሳሉ።
በናይል ወንዝ ላይ የሚደረግ ሽርሽር ቱሪስቶች ከሚመርጧቸው ክንውኖች አንዱ ነው።
በአውሮፓ ላለፉት 50 ዓመታት የሠራው 'ቦት ባይክ ቱርስ' አስጎብኚ ድርጅት ግብፅን መዳረሻ በዝርዝሩ ውስጥ አካትቷል።
ሥራ አስኪያጁ ላውረንስ ዊንክል "በሳይክል የቱሪስት መዳረሻዎችን መጎብኘት እየተለመደ ነው። ጊዜ ወስዶ እያንዳንዱን መዳረሻ መጎብኘት ይቻላል" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ብራዚል
ብራዚል በየዓመቱ የምታስመዘግበው የቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 2025 የአገሪቱ የቱሪስቶች ፍሰት 37 በመቶ አድጓል።
የብራዚል ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ተቋም በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች ጥምረት አውሮፕላን ማረፊያዎችን በማዘመን እና አዳዲስ የአውሮፕላን ጉዞ መስመሮችን በመዘርጋት ጎብኚዎችን ለመሳብ ይሞክራል።
ብራዚል ዓለም አቀፍ ቱሪዝምን ለማሳደግ የወሰደቻቸው እርምጃዎች ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል።
የብራዚል ዓለም አቀፍ ቱሪዝም መሥሪያ ቤት ፕሬዝዳንት ማርሴሎ ፍሬክሶ "አዳዲስ የአውሮፕን ጉዞ መስመሮች መዘርጋት የብራዚልን ዓለም አቀፍ ቱሪዝም እያሳደረ ነው" ይላሉ።
የማይነር ሆቴልስ ምክትል ፕሬዝዳንት ማርኮ አማራልም በዚህ ሐሳብ ይስማማል።
በሪዮ የተካሄደው ኦሊምፒክ እንዲሁም የዓለም ዋንጫ እና በቀጣይ ዓመት የሚጠበቀው የሴቶች የዓለም ዋንጫ የብራዚል ቱሪዝም የጀርባ አጥንት ናቸው።
ብራዚል በሙዚቃ እና በምግብም ጥሩ ስም አግኝታለች።
ለተፈጥሮ ቅድሚያ የሚሰጡ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚጓዙ ቱሪስቶች ቁጥርም ጨምሯል።
ብራዚል ከ9,000 ኪሎሜትር በላይ የባሕር ዳርቻ አላት። የቀደምት ማኅበረሰቦች መገኛም ናት።
የግሎባል ቪዥን አክሰስ አስጎብኚ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ጂዜል አብራሆ እንደምትለው፤ መዳረሻዎችን እና ክንውኖችን በተገቢው መንገድ ማስተዋወቅ የጎላ ሚና አለው።
በመዳረሻዎች አካባቢ ለሚኖሩ ማኅበረሰቦች ቅድሚያ መስጠትንም ትጠቅሳለች።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ሲሸልስ
ሲሸልስ የቱሪዝም ፍሰቷን በ13 በመቶ ማሳደግ ችላለች። በአፍሪካ የቱሪዝም ሰንጠረዥ ላይ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ናት።
የአገሪቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች መካከል ያለን ጥምረት ያበረታታል።
የአገሪቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር ፀሐፊ ሸሪን ፍራንሲስ እንደሚናገሩት፤ የአገሪቱ ቱሪዝም እንዲያድግ ይህ ጥምረት ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።
ሲሸልስ የጫጉላ ሽርሽር መዳረሻ በመሆን ዝነኛ ስትሆን፤ አሁን ሌሎች የቱሪስት መስህቦችንም እያስተዋወቀች ነው።
የአናናትራ ማያ ሲሸልስ ቪላስ ሥራ አስኪያጅ ናጂ ኤስታ "ከባሕር ዳርቻ ሽርሽር በተጨማሪ ፏፏቴ ማየት፣ የእሳት ዳር ጨዋታ እና ቆንጆ ምግብም እናቀርባለን" ትላለች።
ሲሸልስን በብዛት የሚጎበኙት ጥንዶች ናቸው። የሲሸልስ የቱሪስት መዳረሻዎች ለአትክልት ተመጋቢዎች የሚሆን የምግብ ዝርዝር በማዘጋጀት እና በሌሎችም መንገዶች የቱሪስቶች ስብጥሩን ለማስፋት ይሞክራሉ።
ሲሸልስ 30 በመቶ የውቅያኖስ ክፍሏን ጥብቅ አካባቢ በማድረግ ትታወቃለች።

የፎቶው ባለመብት, Alamy
ቡታን
በሂማሊያ ተራሮች አቅራቢያ የምትገኘው ቡታን ለመጀመሪያ ጊዜ በሯን ለቱሪስቶች ክፍት ያደረገችው በአውሮፓውያኑ 1970 አካባቢ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2025 ብቻ የቱሪስቶች ፍሰት ወደ 30 በመቶ ደርሷል።
ቱሪስቶች ለቡታን ዘላቂ ዕድገት የሚውል ዕለታዊ የ100 ዶላር ክፍያ ይከፍላሉ። ይህም የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማዘመን እና አገሬውን ለመጥቀም ይውላል።
የቡታን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ሎታይ "አገራችንን እና ባህላችንን እንዲያዩ ሁሉንም ዓይነት ቱሪስቶች እንጋብዛለን። ከእነሱ ለመማርም ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ቡታን እንደ ጠቅላላይ የአገር ውስጥ ምርት ልኬት ሁላ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ደስተኛነት ልኬት በማስተዋወቅ ዝነኛ ሆናለች።
የሂማሊያን ኤኮስ ሥራ አስኪያጅ የሺን ጎል "ዘመነኛ የቱሪስት መዳረሻዎች ለሰለቿቸው ቱሪስቶች ሁነኛ አማራጭ ሆናለች" ይላል።
ብዙ አገራት ቢጎበኙም አንዳች "ጥልቅ ስሜት" የሚሰጥ ጉዞ ለሚሹ ጎብኚዎች መዳረሻ በመሆን ስሟን ገንብታለች።
አገሪቱ ተራራማ እንደመሆኗ ብዙዎች በሞተርሳይክል እየተዘዋወሩ መጎብኘት ይመርጣሉ።
ዘለግ ላለ ጊዜ በጽሞና ለማሰላሰል እና ለመረጋጋትም ተመራጭ የቱሪስቶች መዳረሻ ናት።















