በደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእጩ ጥቆማ ጥሪ "የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ" ነው አለ

በዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት መረጣ ያቀረቡትን የእጩ ጥቆማ ጥሪ፤ "የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ አካሄድ" እንደሆነ በመግለጽ ተቃወመ።

የፌደራል መንግሥት "የትግራይን ህልውና የሚፈታተኑ ሁካታ እና ግጭትን የሚፈጥሩ ስራዎችን" እያከናወነ ነው ሲልም ከስሷል።

ክንፉ፤ ትናንት ረቡዕ መጋቢት 17/2017 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ደም አፋሳሹን ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ሊፈጽማቸው ይገባ የነበሩ "የትግራይ መብት እና ደህንነትን የሚመለከቱ ወሳኝ የስምምነቱ ይዘቶች የመፈጸም ተግባር" እያከናወነ አለመሆኑን ገልጿል።

"በስምምነቱ የሌሉ ጉዳዮች በብቸኝነት በትግራይ ላይ በመጫንና የሰላም ሂደት በሚጎዱ ተግባራት ተጠምዶ ይገኛል" ሲልም የፌደራል መንግሥትን ወቅሷል።

"በአሁን ሰዓት የትግራይ ህዝብ የተመረጠ መንግሥት ሊኖረው ይገባ" እንደነበር የገለጸው ፓርቲው፤ ይህ ያልተሳካው የፌደራል መንግሥት ስምምነቱን አፈጻም በተመለከተ በተከተለው "የተሳሳተ አካሄድ እና የፖለቲካ ትርምስ እንዲኖር በመስራቱ" ምክንያት እንደሆነ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

በአሁኑ ሰዓትም ከዚህ ቀደም ከነበሩ "የፕሪቶሪያ ስምምነት የሚፃረሩ ተግባራት ሌሎች አዳዲስ ጥሰቶች በኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈፀሙ" መሆኑንም ገልጿል።

የፓርቲው ክንፍ ይህንን ክስ ያቀረበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራይ ህዝብ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትን የሚተካ እጩ በኢሜይል እንዲጠቁም ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትናንት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸውን በትግርኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት የፕሪቶሪያ ስምምትን ተከትሎ በ2015 ዓ.ም. የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሁለት ዓመት ስራ ጊዜ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ይኹን እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ በክልሉ መደበኛ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ምርጫ ለማከናወን "ሁኔታዎችን ማመቻቸትን" ጨምሮ ማከናወን የነበረበትን "ቁልፍ ተግባራቶች በወቅቱ ማከናወን እንዳልቻለ" ጠቅሰዋል።

በክልሉ ያለውን "ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት" የሕግ ማሻሻያ ተደርጎ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ዘመን በአንድ ዓመት እንዲራዘም እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመት በአቶ ጌታቸው ረዳ ሲመራ የነበረው ጊዜያዊ አስተዳደር የስልጣን ዘመኑ ሲራዘም አዲስ ፕሬዝዳንት እንደሚሾምለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የትግራይ ሕዝብም "በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚሰጣቸውን ተግባራት በብቃት ይወጣሉ" እንዲሁም "የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ይችላሉ" ብሎ የሚያምንባቸውን እጩዎች በኢሜይል ለፕሬዝዳንትነት እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።

ዐቢይ በዚህ መልዕክታቸው፤ "የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትን መሾም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነት" መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማቋቋም በ2015 ዓ.ም. የወጣውን ደንብ በመጥቀስ ነው።

አስተዳደሩን ለማቋቋም የወጣው የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብ፤ "ርዕሰ መስተዳድሩ በሰላም ስምምነቱ መሠረት በሚደረግ የፖለቲካ ምክክር ተለይቶ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል" ይላል።

ይህ ደንብ የወጣው "የፌደራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ" በ1995 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ መሰረት በማድረግ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሁለት ዓመት የስልጣን ጊዜ መጠናቀቀን ሲገልጹ የጠቀሱት ይህንኑ ከ22 ዓመት በፊት የወጣ አዋጅ ነው።

ትናንት ምሽት መግለጫ ያወጣው በዶ/ር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ግን እነዚህን ህጎች "አግባብነት የሌላቸው" ሲል ጠርቷቸዋል።

የፌደራል መንግሥት በእነዚህ ሕጎች እየተመራ ያለው "ግጭት የማቆም ስምምነትን መንፈስ እና ይዘት ወደ ጎን" በመተው እንደሆነ በመግለጫው ጠቅሷል።

የፌደራል መንግሥት "ተደራዳሪ ወገኖች በድርድር እና በመግባባት የደረሱበትን የጋራ ስምምነት" ችላ እንዳለ ያንሳው መግለጫው፤ "አግባብነት በሌላቸው ህጎች (አዋጅ 359/1995፤ ደንብ 533/2015) ብቻውን እንደ ፈለገው ለመሄድ እየሰራ ይገኛል" ሲል ተችቷል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተደራዳሪዎቹ ህወሓት እና የኢትዮጵያ መንግሥት "ስምምነት" እንደሚቋቋም መደንገጉን በመግለጫው አስታውሷል።

ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ግጭትን ለማቆም በተደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 10 (1) መሰረት ሁሉን አካታች የሆነ የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር የሚቋቋመው ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥት በሚያደርጉት ፖለቲካዊ ምክክር ይሆናል ይላል።

በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ መግለጫ፤ ". . . በትግራይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያ ስምምነት ውጤት እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ውሳኔ ውጤት አይደለም" በማለት አጽንኦት ሰጥቷል።

ይኹን እንጂ ይህንን የስምምነት ድንጋጌ "የሚጥስ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል" ሲል ከስሷል።

ባለፉት ሳምንታት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሚተኩበትን አካሄድ በተመለከተ ከፌደራል መንግሥት ጋር ንግግር እንደተደረገ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ በዶ/ር ደብረፅዮን በሚመራው የፓርቲው ክንፍ ተቀባይነት ያጡት ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ከስልጣን መነሳታቸው በይፋ ባይገለጽም በክልሉ መዲና መቀለ ከተማ ሆነው መዋቅሩን እየመሩ አይደለም።

የፓርቲው ክንፍ በመግለጫው፤ "የጊዜያዊ አስተዳደሩን አፈፃፀም በመገምገም ፕሬዝዳንቱን ለመቀየር ስምምነት" ላይ መደረሱን ገልጿል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ "የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደወሰነ" እና ይህ ውሳኔ "በኢትዮጵያ መንግሥት በኩልም ተቀባይነት እንዳገኘ" ፓርቲው አስታውቋል።

ክንፉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያቀረቡት የእጩ ጥቆማ ጥሪ ይህንን "ስምምነት ወደ ጎን በመተው" የተከናወነ መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟል።

ጥሪው "ፕሬዝዳንት የመሾም ስልጣን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናጠል ውሳኔ የሚያስመስል እና የፕሪቶሪያው ስምምነት የሚጥስ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም" ሲልም ውድቅ አድርጓል።

መግለጫው፤ ሌሎች ጉዳዮችንም በማንሳት የፌደራል መንግሥትን በፕሪቶሪያ ስምምነት "በመጣስ" ድርጊት ከስሷል።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት "ተፈራራሚ ወገኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንዱ ሌላውን ያለመተንኮስ ግዴታ" እንደተጣለባቸው እና "ተንኳሽ የፕሮፖጋንዳና የሚድያ ስራዎችን" ማከናወንም እንደተከለከለ ጠቅሷል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህ ግዴታዎችን በመጣስ የትግራይን ህልውና የሚፈታተኑ፣ ሁካታና ግጭትን የሚፈጥሩ ስራዎች ከጀመረ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቷል" ሲል ወቅሷል።

የፌደራል መንግሥት ይህንን እያደረገ ያለው "ልክ የሌለው ሃብት በማፍስ" እንደሆነም በመግለጫው አስፍሯል።

"በተጨማሪም የሕዝብ ሰላም የሚያተራምሱ ሰፋፊ እንቅስቅሴዎች እየተደረጉ ናቸው" ያለው ክንፉ፤ "ሰላምን ጠብቀው ዋጋ እየከፈሉ ያሉና የመከታችን ዋልታ የሆኑ የትግራይ ሰራዊት እና አመራሩ በ'በሬ ወለደ' በኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት እየተወነጀሉ ይገኛሉ" ብሏል።

መግለጫው፤ ወደ ትግራይ ክልል "ነዳጅ እና ሌሎች በመንግሥት የሚተዳደሩ ወሳኝ ሸቀጦችና አገልግሎቶች" እንዳይገቡ "መከልከላቸውን" በመጥቀስ "በትግራዋይ ሕይወትና ኑሮ መጫወቱ ቀጥሏል" ሲል መንግሥትን ከስሷል።

የትግራይ ክልል ንግድ እና ኤክስፖርት ቢሮ ላለፉት 11 ቀናት ከሌሎች ክልሎች "በተለየ ሁኔታ" ወደ ትግራይ ክልል ምንም ዓይነት ነዳጅ አለመጫኑን ለቢቢሲ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለሁሉም ክልሎች የሚያጋራው የነዳጅ ስርጭት መረጃ፤ የነዳጅ አቅርቦት ሙሉ ለሙሉ የቆመው "በትግራይ ክልል ብቻ" እንደሆነ እንደሚያመለክት በቢሮው የሸማቾች ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ክንደያ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እንደነዚህ የመሰሉ ኢሰብዓዊ ተግባራት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ብቻ ሳይሆን ዓለም ዓቀፍ ሕጎችን የሚፃረሩ እና እጅጉ አስነዋሪ የሰው ልጅ ፀር የሆኑ ወንጀሎችና በዘር ማጥፋት የሚያስጠይቁ ተግባሮች ናቸው" ብሏል።

ክንፉ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት መፈጸም ነበረባቸው ያላቸውን "የተፈናቀሉና የተሰደዱ ዜጎች ወደ ቀያቸው" መመለስ፣ "የትግራይ ሉዓላዊነት" ማረጋገጥ፣ "ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲነግስ" ማድረግ፣ እንዲሁም "የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸውን" የመካስ ተግባራት እንዲከናወኑ ጠይቋል።

"በትግራይ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖር ርብርብ እንዲደረግና ተዛማጅ ተግባሮች በስምምነቱ መሰረት እንዲፈፀሙም" ጥሪ አቅርቧል።

መግለጫው አክሎም፤ "የኢትዮጵያ መንግሥት በግልፅ እየታዩ ካሉትና ለሕዝብ ጎጂ የሆኑትን ሁካታና ግጭት ከሚፈጥሩ ተግባሮች ተቆጥቦ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ጥቅም በሚያረጋግጡ ተግባሮች [ላይ] እንዲያተኩር ጥሪያችን እናቀርባለን" ሲልም የፌደራል መንግሥቱን አሳስቧል።