ዩናይትድ ከስፐርስ፡ ማን ያሸንፋል? የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግምት

ብሩኖ ፈርናንዴዝ እና ሶን ሂዩንግ ሚን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስድስተኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሲቀጥል ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም ሆትስፐር እሑድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ እና አንጅ ፖስቴኮግሉ የውድድር ዓመቱን የጀመሩበት መንገድ ለትችት አጋልጧቸዋል።

“የሚኖረው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ብዬ አልገምትም” ይላል የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን።

ሱተን ይህንን እና ቀሪዎቹን ሊጉን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ገምቷል።

ቅዳሜ

ኒውካስል ከ ማንቸስተር ሲቲ

ኒውካስል ወደ ድንቅ ብቃቱ ባይመለስም ነጥቦችን እየሰበሰበ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በሜዳቸው ሴንት ጀምስ ፓርክ ማንቸስተር ሲቲን ቢፈትኑም በዚህ ጨዋታ ግን የሚፎካከሩ አይመስልም።

ሲቲ ሮድሪን ቢያጣውም እሱን ተክተው የሚገቡ ተጫዋቾች ስላሉት ጨዋታውን ያሸንፋል።

ግምት፡ 1 – 3

የአርሰናል እና ሌስተር መለያ አርማ

አርሰናል ከ ሌስተር

አርሰናል ባለፈው ሳምንት ከሲቲ ጋር በነበረው ጨዋታ አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት አውቶብሶችን አቁሞ ሲከላከል ነበር።

ከሲቲ ጋር ብቻ ሳይሆን መድፈኞቹ በሻምፒዮንስ ሊጉም ከአታላንታ ጋር መከላከልን መርጠው ነበር።

በመከላከል የሊጉን ዋንጫ ካነሱ ለአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ትልቅ አክብሮት ይጎርፍለታል። በዚህ ጨዋታ ግን ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ እንደሚመለሱ ይገመታል።

ሌስተር በፕሪሚየር ሊጉ ውጤታማ ዓመታትን ማሳለፍ ችሏል።

ቡድኑ አማካዩ ኪየርናን ዴውስበሪ-ሆል በቼልሲ መነጠቁ የመሐል ክፍሉን አሳስቶበታል።

ጨዋታው ለሌስተር ከባድ ይሆናል።

ግምት፡ 2 – 0

ብሬንትፎርድ ከ ዌስት ሃም

አሰልጣኝ ሎፔቴጉ ከውጤት በተጨማሪ ጥሩ አጨዋወትም ሊያሳዩ ይገባል። በእስካሁኑ ደጋፊዎች የጠበቁት ለውጥ አልተመዘገበም።

ባለፈው ሳምንት በቼልሲ ከመሸነፋቸውም በላይ ስጋት የፈጠረው ተከላካይ መስመሩ ደካማነት ነው።

ቡድኑ በሊቨርፑል ተሸንፎ ከካራባኦ ዋንጫ ውጭ ሆኗል።

ምንም እንኳን ሁለቱንም ጨዋታዎች ቢሸነፍም ብሬንትፎርድ የጎል ዕድል ለመፍጠር የሚችል ቡድን መሆኑን ከማንቸስተር ሲቲ እና ቶተንሃም ጋር ቀድሞ ጎል በማስገባት አሳይቷል።

በጉዳት ከሜዳ ከራቀው ዮአን ዊሳ ውጭም ቡድኑ ጠንካራ መሆኑን አሳይቷል።

ግምት፡ 2 – 1

የቼልሲ እና ብራይተን መለያ አርማ

ቼልሲ ከ ብራይተን

ቼልሲ ደካማ በሆነበት ጊዜ ትችት አሁን ደግሞ ውጤቶች በመቀየራቸው ሙገሳ ያስፈልገዋል።

የቡድኑ ቦርድ ውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ቢኖርም በሜዳ ላይ ያለው ውጤት መልካም የሚባል ነው።

ከዚህ ቀደም የቡድኑን ውጤት ለመገመት ከባድ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

ይህንን ጨዋታ ለመገመት ግን ከባድ ነው። ምክንያቱም ብራይተንም የውድድር ዓመቱን በጥንካሬ መጀመሩ ነው።

ኮል ፓልመር በተለመደ አጨዋወቱ፤ ኒኮላስ ጃክሰን ደግሞ በድንቅ ብቃቱ ቼልሲን ለድል ያበቁታል።

ግምት፡ 2 – 1

ኤቨርተን ከ ክሪስታል ፓላስ

ክሪስታል ፓላስ ድንቅ ቡድን መሆኑን ደጋግሞ ቢያሳይም ከሰሞኑ ግን ይህንን ማሳየት አልቻለም።

የኤቨርተኑ ሰልጣኝ ሾን ዳይሽ ከቡድናቸው ጥሩ ውጤት ይጠብቃሉ። መጥፎ ውጤት ከተመዘገበ ደጋፊው ፊቱን እንዳያዞር ያሰጋል።

ቡድኑ ጎል አስቆጥሮ መምራት ቢችልም የተከላካይ መስመሩ ውጤቱን ማስጠበቅ ይኖርበታል።

ይህንን ጨዋታ ኤቨርተን የማሸነፍ ብቃት ቢኖረውም በጉዳት ከሜዳ ከራቀው ተከላካዩ ጃሬድ ብራንትዌት ሳይሰለፍ የሚሳካ አይመስለም።

ግምት፡ 1 – 1

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ፉልሃም

ፉልሃም በሜዳው ጥሩ ቢሆንም ከሜዳው ውጭ ግን ብዙ መሻሻል ይኖርበታል።

ኖቲንግሃም ፎረስት ሞርጋን ጊብስ-ዋይትን በቅጣት ማጣቱ ዕድለ ቢስ ያደርገዋል።

ይህ ምርጥ ጨዋታ ቢሆንም በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 1 – 1

ዎልቭስ ከ ሊቨርፑል

ዎልቭስ የውጤቱን ያህል መጥፎ ቡድን ባይሆንም ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ጋሪ ኦኒል ላይ ፊታቸውን ሊያዞሩ ይችላሉ።

ቡድኑ ባለፈው ዓመት ጥሩ የነበረ ቢሆንም በውድድር ዓመቱ መገባደጃ ላይ እና ዘንድሮ ግን ደካማ ሆኗል።

ሊቨርፑል ካለው የአጥቂዎች ብቃት አንጻር ይህንን ጨዋታ የማሸነፍ ዕድል አለው።

ግምት፡ 1 – 2

እሑድ

ኢፕስዊች ከአስቶን ቪላ

ኢፕስዊች ዘንድሮ ማሸነፍ ባይችልም የተሸነፈው በማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ብቻ መሆኑ አስደናቂ ነው።

የኬራን ማኬና ቡድን ባለፈው ሳምንት ሳውዝሃምፕተን ላይ ባለቀ ሰዓት ጎል አስቆጥሮ አቻ መውጣቱ የቡድኑን በራስ መተማመን ያሳድገዋል።

በዚህ ጨዋታ ግን ምንም ነጥብ አያገኝም። ቪላ ጎሎችን ቢያስተናግድም በሚሳተፍባቸው ውድድሮች ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ቀጥሏል።

ኢፕስዊች በዚህ ጨዋታ ጎል ማስቆጠር ቢችልም ቪላን የማንበርከክ አቅም አይኖረውም።

ግምት፡ 1 – 2

የማንቸስተር እና ቶተንሀም መለያ አርማ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ቶተንሃም ሆትስፐር

ማንቸስተር ዩናይትድ ከኤፍሲ ትዌንቴ ጋር አቻ በመለያየቱ ትችቶች እየተሰነዘሩበት ነው።

ስፐርስም በተቃራኒ ቡድን ጎል ፊት ያለውን ድክመት ማረም ይኖርበታል።

የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን እንደስፐርስ ያለ አጨዋወት ለሚከተለው የመልሶ ማጥቃት ስለሚመቸው ይህንን ጨዋታ ያሸንፋል።

ስፐርስን ስለማሸነፋቸው ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ማንቸስተር የአማካይ ክፍል አሳሰቢ ነው። ክርሲቲያን ኤሪክሰን ድንቅ ተጫዋች ቢሆንም እንደቀድሞው ተሯሩጦ ለመጫወት አለመቻሉ ተደጋግሞ ታይቷል።

ግምት፡ 2 – 1