አሜሪካ የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መረጃን መንትፈዋል ያለቻቸውን ሦስት ኢራናውያን ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ከዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ መረጃዎቸን ከመመንተፍ ጋር በተያያዘ ሦስት ኢራናውያን ላይ ክስ መሰረተች።
አቃቤ ሕግ የኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ አባላት ናቸው ያላቸውን ማሱድ ጃሊል፣ ሰይድ አሊ አግሃሚሪ እና ያሳር ባላጋሂ “መረጃ በመመንትፍ እና ሰነድ በማሹለክ” ተግባር ላይ “ይኹነኝ ተብሎ" በስም ያልተጠቀሰን የምርጫ ዘመቻ ለማጣጣል ሲሰሩ ነበር ብሏል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ባለስልጣናት የኢራን መረጃ መንታፊዎች ከዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች የወሰዱትን ሰነድ ከባይደን የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች ጋር ግንኙነት ላላቸው ሰዎች መላካቸውን ገልጸው ነበር።
ሦስቱ የመረጃ መንታፊዎች የተከሰሱት በ18 ወንጀሎች መሆኑ ተገልጿል።
በነሐሴ ወር ላይ የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የውስጥ ግንኙነት ልውውጡ በኢራን መረጃ መንታፊዎች መሰረቁን ገልጾ ነበር።
በወቅቱ የኢራን ባለስልጣናት በመረጃ ምንተፋው ላይ እጃቸው እንደሌለበት በመግለጽ አስተባብለዋል።
ከጥቂት ቀናት በኋላ የፌደራሉ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ወደ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ኢራን ሰርጋ መግባቷን አረጋግጧል።
የአሜሪካ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ኢራን በመጪው የአሜሪካ ምርጫ ላይ ክፍፍልን ለመፈጠር እንዲሁም ዜጎች በአሜሪካ መንግሥታዊ ተቋማት ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር ለማድረግ እንደምትጥር አስጠንቅቆ ነበር።
ባለሥልጣቱ ኢራን ይህንን ዓላማዋን ለማሳካት እና የዲሞክራቶች እንዲሁም የሪፐብሊካኖች የምርጫ ማስተባባሪያዎችን በቀጥታ ለመበርብር “ማኅበራዊ ምህንድስና” የተባለ እና ሌሎች ስልቶችን ስትጠቀም ነበር ብለዋል።
ይህንን ስልት ኢራን እና ሩሲያ በሌሎች አገራት ላይ የሚተገብሩት እንደሆነም አንስተዋል።
ቢሮው አክሎም “በዚህ የምርጫ ወቅት ኢራን ይህንን ድርጊቷን በስፋት እንደቀጠለችበት ይታያል” ሲል አስጠንቅቋል።
37 ገጽ የያዘው የመረጃ መንታፊዎቹ ክስ ዝርዝር እኤአ ከ2020 ጀምሮ ከፖለቲካ ምርጫ ጋር ተያይዞ የአሜሪካ መንግሥት፣ የደህንነት ባለስለጣናትን፣ መገናኛ ብዙኀንን፣ እንዲሁም ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር የተገናኙ ግለሰቦች ላይ ትኩረት አድርገው ሲሰሩ ነበር ይላል።
በ2024 ግንቦት ወር ላይ የፍትህ ቢሮ ሦስቱ መረጃ መንታፊዎች “የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 1” ላይ ትኩረት በማድረግ ማሴር ጀምረዋል ሲል ይወነጅላቸዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በምርጫ ዘመቻ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን ኢሜል ለማግኘት በሚል ሀሰተኛ የሆነ አድራሻ በመጠቀም እና ራሳቸውን የአሜሪካ ባለስልጣን በማስመሰል ሰነዶችን እና የመረጃ ልውውጦችን ሰርቀዋል ሲል ወንጅሏቸዋል።
በሰኔ ወር ላይ ደግሞ የተሰረቁትን መረጃዎች ለመገናኛ ብዙኀን እንዲሁም “ከአሜሪካ ምርጫ ዘመቻ 2” ጋር ለተገናኙ ሰዎች በማሹለክ “እንደ መሳርያ ሊጠቀሙበት” መሞከራቸውን ጠቅሶ ይከስሳቸዋል።
ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ አንቶኒ ሜሪክ ጋርላንድ የባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን መረጃዎቹን ተጠቅሞባቸው እንደሆነ ተጠይቀው “ ምንም ዓይነት ፍንጭ አላገኘንም” ሲሉ መልሰዋል።
አክለውም ኤፍቢአይ ከትራምፕ እንዲሁም ከባይደን በኋላም ካማላ ሃሪስ ከተረከበው የምርጫ ቅስቃሳ ቡድን አባላት “ጥሩ ትብብር” ማግኘቱን ገልጸዋል።
የካማላ ሐሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
“ምንም ዓይነት ሰነድ በቀጥታ ለቅስቀሳ ዘመቻው መላኩን አናውቅም፤ የተወሰኑ ግለሰቦች በግል የኢሜል አድራሻቸው አሳሳች መልዕክቶች የሚመስሉ ተልኮላቸዋል” ብለዋል የካማላ ሓሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ፀኃፊ ቃል አቀባይ ሞርጋን ፊንክልተይን።
ቢቢሲ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ቡድን እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት የኢራን ሚሺን ተወካይ ለሆኑት ግለሰብ ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።
የክሱ ዝርዝር እንደሚያስረዳው ከሆነ “የቀድሞ፣ መደበኛ ያልሆኑ የትራምፕ የፖለቲካ አማካሪ” ኢሜል በዚህ የመረጃ መንታፊዎች መረብ ውስጥ ወድቋል። እንዲሁም ስሙ ያልተጠቀሰ በምርጫ ዘመቻው ላይ ተሳትፎ ያለው ኃላፊ እና እርሱን የሚወክል ጠበቃ ኢሜልም እንዲሁ በመረጃ መንታፊዎቹ እጅ ገብቶ ነበር።
የኤፍ ቢአይ ዳይሬክተር ክርስቶፈር ውሬይ በመግለጫቸው ላይ“ዛሬ ለኢራን መንግሥት ኤፍ ቢአይ መላክ የሚፈልገው መልዕክት እናንተ እና መረጃ መነታፊዎቻችሁ ከኮምፒውተራችሁ ጀርባ ተደብቃችሁ አትቀሩም የሚል ነው” ብለዋል።
አክለውም ክሶቹ “ኤፍ ቢአይ ለረዥም ጊዜ ክትትል ያደረገባቸው እና በሚገባ ያደራጀው ማጠቃለያ የቀረበበት ነው” ብለዋል።
ኢራን በእጇ አስገብታዋለች ከተባለው ሰነድ መካከል ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ለምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት እጩ ጄዲ ቬንስ መረጃዎች ናቸው።
እነዚህ ሰነዶች እና ሌሎች መረጃዎች ለበርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኀን የተላኩ ሲሆን በስፋት የተሰራጩት ግን ሐሙስ ዕለት ኬን ክሊፔኒስቴይን የተባለ ጋዜጠኛ በግል ጦማሩ ላይ ካጋራቸው በኋላ ነው።
ክሊፔይንስቴይን “ሮበርት” የተባለ ግለሰብ ሰነዶቹን እንደላከለት የገለጸ ሲሆን ወድያውኑ ከኤክስ ገጹ ላይ ታግዷል።
ኤክስ ባወጣው መግለጫም የግለሰብን መረጃ ይፋ በማድረግ ላይ ያለውም መመርያ ጥሷል ብሏል።












