የጋዛው ትልቁ ሆስፒታል በአስከሬኖች እንደተጨናነቀ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋዛ በሚገኘው ትልቁ ሆስፒታል አልሺፋ ጦርነት ሸሽተው ከተጠለሉ በሺዎች ከሚቆጠሩ ነዋሪዎች በተጨማሪ አስከሬኖች እየተከማቹ መሆኑን ባለስልጣናት አስጠንቅቀዋል።
ከኃይል መቆራረጥ እና ከነዳጅ እጥረት ጋር ግብግብ ውስጥ የገባው አል ሺፋ ሆስፒታል መደ “መቃብር ስፍራነት ተቀይሯል” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።
የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ በእስራኤል ከበባ ውስጥ በመሆናቸው ምክንያት ያሉት ውሾች አስከሬን መብላት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ቀናት በሆስፒታሉ አቅራቢያ ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በሆስፒታሎቹ ላይ የምትወስደው እርምጃ “ተገቢ” በሆነ መልኩ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸው፣ የህክምና ማዕከሉ “መጠበቅ አለበትም” ብለዋል ።
በጋዛ ከተማ ከቅርብ ቀናት ወዲህ በእስራኤል እና በሐማስ ሃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ተፋፍሞ ታይቷል። አብዛኛው ውጊያው ለሆስፒታሉ ቅርብ በሆኑ መንገዶች ሲካሄድ ቆይቷል። ታንኮች እና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ከሆስፒታሉ በር በጥቂት ሜትሮች ብቻ ርቀው እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል።
ሐማስ በሆስፒታሉ ስር ባሉ ዋሻዎች ውስጥ የትዕዛዝ እና የቁጥጥር ማዕከል አለው ስትል እስራኤል ብትከስም፤ ሐማስ እና ሆስፒታሉ ግን ጉዳዩ ሐሰት ነው ሲሉ አልተቀበሉትም። የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድረው ሐማስ "ሰብዓዊ ድጋፎችን ከልክሏል" ስትል እስራኤል ጨምራ ትከሳለች።
የእስራኤል ጦር አልሺፋ አቅራቢያ ግጭቶች መኖሩን ጠቅሶ በሆስፒታሉ ላይ የተከፈተ ተኩስም ሆነ ከበባ የለም፤ መውጣት የሚፈልግ ሁሉ መውጣት እንደሚችልም ገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ ክርስቲያን ሊንድሜየር በበኩላቸው ወደ 600 የሚጠጉ ሰዎች በሆስፒታል ውስጥ እንደቆዩ እና ሌሎች ደግሞ በሆስፒታሉ መተላለፊያዎች መጠለላቸውን ገልጸዋል።
"በሆስፒታሉ አካባቢ እንክብካቤ የማይደረግላቸው ወይም የማይቀበሩ ወይም ወደ የትኛውም የሬሳ ክፍል የማይወሰዱ አስከሬኖች አሉ። ሆስፒታሉ በሚፈለገው መልኩ እንደመሥራት የመቃብር ስፍራ ሆኗል" ብለዋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሆስፒታሉ ውስጥ ቢያንስ 2,300 ሰዎች አሁንም አሉ ብሏል። እስከ 650 የሚደርሱት ታካሚዎች ሲሆኑ፤ ከ200 እስከ 500 ሠራተኞች እና ወደ 1,500 የሚጠጉ ተፈናቃዮች መጠለያ እንዳደረጉት አስታውቋል።
ዶክተሮችም በሆስፒታሉ ውስጥ የሚከመሩ እና የሚበሰብሱ አስከሬኖች እንዳሉ ገልጸዋል። የአል-ሺፋ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶ/ር ሞሐመድ አቡ ሰልሚያ 150 የሚጠጉ አስከሬኖች በመበስበስ "መጥፎ ጠረን ፈጥረዋል" ብለዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት አሁንም አስከሬኖቹ ከሆስፒታሉ ወጥተው እንዲቀበሩ ፍቃድ እንዳልሰጡና ውሾች ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ በመግባት አስከሬኖቹን መብላት መጀመራቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በተጨማሪም በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት በኢንኩቤተር (የጨቅላ ማሞቂያ) ውስጥ መቆየት የማይችሉ በርካታ ህጻናት በሞት አፋፍ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
ዶ/ር ሰልሚያ እንዳሉት ከእነዚህ ህጻናት መካከል ሰባቱ በኦክስጅን እጥረት ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
ህጻናቱን ለማስወጣት ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር ድርድር ቢደረግም ስምምነት ላይ አለመደረሱን ተናግረዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፍተኛ አማካሪ ማርክ ሬጌቭ በበኩላቸው እስራኤል ህጻናቱን ለማስወጣት "መፍትሄዎችን" እየሰጠች ቢሆንም ሐማስ ሃሳቦቹን አልተቀበለም ሲሉ ከሰዋል።
"ለጄነሬተሮቻቸው የቀረበውን ነዳጅ አይወስዱም። በአምቡላንስ ሕፃናቱ እንዲንቀሳቀሱ አይደግፉም። ስለዚህ እዚያው ቀርተዋል። ምክንያቱም (ሃማስ) እነዚያን አስፈሪ ፎቶግራፎች ይፈልጋቸዋል" ብለዋል።
ከስሩ ዋሻዎችን በመገንባት ሆስፒታሉን “የጦርነት ቀጠና” አድርጎታል ሲሉ ሐማስን ከሰዋል። ሐማስ ሆስፒታሉን ስለመጠቀሙ የማይቀበለው ሲሆን፤ እዚያ የሚሠሩ ዶክተሮችም ሐማስ የለም ሲሉ ይከራከራሉ።
ከአል-ሺፋ በተጨማሪ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ሌሎች ሆስፒታሎች በጦርነቱ ምክንያት የግብዓት አቅርቦት እና የሃይል እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።












