ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቤተ-ሙከራ የተሠራ ሥጋ የሚሸጥበት ብቸኛው የዓለማችን ሬስቶራንት
የዶሮ ሥጋ ይመስላል፤ መዓዛውም የዶሮ ሥጋ ነው. . . ጣዕሙም እንደ ዶሮ ሥጋ ነው።
ይህ ጠረጴዛው ላይ መልኩን አሳምሮ የተሰደረው በዶሮ ማሊያ የሚጫወት ምግብ በእርግጥ የዶሮ ሥጋ አይደለም።
ይህ የዶሮ ሥጋ ዶሮዎችን አርብተው ሥጋ እና እንቁላላቸውን ከሚያርቡ አርቢዎች ጓሮ የመጣ አይደለም። ይልቁንስ ከቤት ሙከራ እንጂ።
መሐል ሲንጋፖር ከሚገኝ አንድ የኢንዱስትሪ መንደር ቤተ-ሙከራ ውስጥ ተመርቶ ሥጋው ወደ ምግብ ቤቶች ያቀናል።
የሲንጋፖሩ ሃበርስ ቡቸሪ ኤንድ ሬስቶራንት ከቤተ-ሙከራ የመጣ ሰው ሰራሽ ሥጋ በያይነቱ ሚቀርብበት ብቸኛው ሥፍራ ነው።
ይህን ‘አስመሳይ’ ሥጋ የበሉ “ወደነዋል” የሚል አስተያየት እንደሰጡ የምግብ ቤቱ ባለቤት ይናገራል።
መቀመጫው ካሊፎርኒያ የሆነው ‘ጀስት ኢት’ ሥጋው አስፈላጊውን ሥርዓት የጠበቀ፣ ንፁሕ እና ጤናማ ነው ይላል።
ጣዕሙን እንደጠበቀ ጠረጴዛችሁ ላይ እናቀርባለን ነው የሚሉት።
ለዚህ ፈጠራ ቢሊዮን ዶላሮች ፈሰስ ቢደርግም፣ ዋናው ጥያቄ እንዴት ቤተ-ሙከራ ውስጥ የተሠራ ሥጋ ይዋጥልናል የሚለው ነው።
የመጀመሪያው ቤተ-ሙከራ ውስጥ የተሠራ በርገር ለንደን ውስጥ በፈረንጆቹ 2013፤ በ330 ሺህ ዶላር መሸጡ አይዘነጋም።
ከዚያ በኋላ ነው አንዳንድ ኩባንያዎች በቤተ-ሙከራ ውስጥ ሰው ሠራሽ ምግብ ለማዘጋጀት ይጣደፉ የጀመሩት።
ነገር ግን እስካሁን ጀስት ኢት ብቻ ነው የተመሠከለት እና የተፈቀደ የቤተ-ሙከራ ሥጋ ይዞ ወደ ገበያ የወጣው።
ሲንጋፖር ደግሞ ብቸኛዋ በዓለማችን የቤተ-ሙከራ ሥጋ የምትቸበችብ አገር ሆና ተመዝግባለች።
ነገር ግን እስካሁን ይህ ሥጋ መሣይ ሥጋ በሰፊው ለገበያ አልቀረበም።
አሁን አሁን ሁበርስ በሳምንት አንድ ቀን በሰው ሠራሽ የዶሮ ሥጋ ሳንድዊች እና የዶሮ ሥጋ በፓስታ ለሕዝቡ ማቅረብ ጀምሯል።
“የቤተ-ሙከራ ሥጋ ማለት እኮ ሥጋ ነው። ነገር ግን እሱን ለማድረግ እንስሳ መግደል አይጠበቅብንም” ይላል የጀስት ኢት ሥራ አስኪያ ጆሽ ቴትሪክ።
ከዕፅዋት ከሚሠሩት የሥጋ ምትኮች ይልቅ ቤተ-ሙከራ የሚሠራው ሥጋ. . . ሥጋ ነው።
ከእንስሳት ሴል ይወሰድ እና በቤተ-ሙከራ ውስጥ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች፤ ለምሳሌ ፕሮቲን፣ ስኳር እና ቅባት እየተመገበ ይደልባል።
ሴሎች ተከፋፍለው እንዲያድጉ ይደረግ እና ጊዜው ሲደርስ ተለቅ ባለ ታኒካ ውስጥ እንዲብላላ ይሆናል።
ከአራት እስከ ስድስት ሳምንታት ወስዶ የዕፅዋት ፕሮቲን ተጨምሮበት ይበስላል። ከዚያም በባለሦስት አውታር (3ዲ) ማተሚያ ቅርፅ ይወጣለታል።
ይህ ሥጋ ከፓስታ ጋር ተቀላቅሎ ፊታችን ቀርቦ ስንመገበው ጣዕሙ በተፈጥሮ ከሚገኘው ሥጋ ብዙም ልዩነት የለውም።
“ሥጋ ነው። በጣም ግሩም ነው” ትላለች ከጣልያን ድረስ ይህን ሥጋር ለመመገብ ብላ የመጣችው ተማሪ ካቴሪና።
ሌላኛው የዚህ የቤተ-ሙከራ ሥጋ ተመጋቢ የሲንጋፖር ሰው ነው። እሱም እንዲሁ ሥጋው ጣዕሙ ‘በሬ ለምኔ’ የሚያሰኝ ነው ይላል።
የዶሮ ሥጋ በፓስታ 18.50 ዶላር ነው። አንድ ሺህ ብር ገደማ ማለት ነው። ዋጋው ከጊዜ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
ለጊዜው ቤተ-ሙከራው በሳምንት ሁለት ኪሎ ቢበዛ ደግሞ 3 ኪሎ ግራም ሰው ሠረሽ ሥጋን ያመርታል።
ነገር ግን ሬስቶራንቱ በሳምንት ቢያንስ ከ4 እስከ 5 ሺህ ኪሎ ግራም ተፈጥሯዊውን ሥጋ ይሸጣል።
ወጣም ወረዳ እንደ ኢት ጀስት ያሉ ቤተ-ሙከራዎች መስፋፋታቸው የሚቀር አይመስልም።
እኒህ ቤተ-ሙከራዎች ሥጋ የሚያመርቱበትን ዋጋ መቀነስ እንዲሁም ምርታቸውን መጨመር ከቻሉ ወደፊት በየምግብ ቤቱ የምግብ ዝርዝር ውስጥ ይህንን ሰው ሠራሽ ሥጋ በስፋት እናየው ይሆናል።