ሕዝበኝነት ምንድን ነው? ለዲሞክራሲስ ጠንቅ ሊሆን ይችላል?

ሕዝበኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአርጀንቲናው ሃቪየር ሚሌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሕዝበኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአርጀንቲናው ሃቪየር ሚሌ

“የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ ነው!” ሲሉ የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ኦርባን ከሰሞኑ የተካሄደውን የኔዘርላንድስ ምርጫ ውጤት ካዩ በኋላ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ጃቪየር ሚሌ “አርጀንቲናን እንደገና ታላቅ ያደርጋታል” ሲሉ አንቆለጳጵሰዋቸዋል።

በአርጀንቲና የቀኝ አክራሪው ሚሌ እና በኔዘርላንድስ ደግሞ ፀረ-እስልምና አቋም የሚያራምዱት ገርት ዋይልደርስ የተቀዳጇቸው ድሎች ትኩረትን የሚስቡ ሆነዋል።

ሁለቱም ሰዎች “ሕዝበኛ (ፖፑሊስት)” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል። ስኬታቸውም ተመሳሳይ እሳቤ በሚያራምዱ ፖለቲከኞች እየተወደሰ ነው። ለመሆኑ ሕዝበኝነት (ፖፑሊስት) ምን ማለት ነው?

ሕዝበኝነት ማለት ምን ማለት ነው?

በፖለቲካል ሳይንስ እሳቤ መሠረት ሕዝበኝነት ማለት በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቃርኖ በሚፈጠርበት ወቅት “ንጹሐን ዜጎች” እና “የላሸቁ ልሂቃን” በሚል በሁለት ቡድን ይከፈላል ይላሉ የ‘ፖፑላሪዝም፡ ኤ ቬሪ ሾርት ኢንትሮዳክሽን’ ፀሐፊ ካስ ሙዲ።

የሕዝበኝነት ፖለቲካ የሕዝቡ አጠቃላይ ፍላጎት መግለጫ መሆን አለበት ሲሉም ይሞግታሉ።

በጉዳዩ ዙሪያ መጽሐፍ የጻፉት ቤንጃሚን ሞፊት ክስተቱ ራሱን በርዕዮተ ዓለም፣ በአደረጃጀት ስልት፣ በአፈፃፀም፣ በንግግር ሊገለጽ ይችላል። “ሁሉም ክርክሮች የሚያጠነጥኑት ግን በሕዝብ እና በሊቃውንት መካከል በሚፈጠር መከፋፈል ነው” ይላሉ።

“ሕዝበኛው በሕዝብ ስም ይናገራል። ልሂቃኑን ደግም የሕብረተሰቡ ዋነኛ ችግር እንደሆኑ አድርጎ ያቀርባል።”

በኔዘርላንድ ማሸነፍ የቻሉት ጊርት ዋይልደርስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኔዘርላንድ ማሸነፍ የቻሉት ጊርት ዋይልደርስ

ሕዝበኝነት ከጽንፈኛ ቀኝ ዘመሞች ጋር በሰፊው ተቆራኝቷል። የግራ ክንፍ ሕዝበኝነትም እንዳለ ግን መረሳት የለበትም። የቀድሞው የቬንዙዌላ መሪ ሁጎ ቻቬዝ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። በአንድ ወቅት “እኔ ግለሰብ አይደለሁም። እኔ የሕዝብ ነኝ” ብለው ነበር።

ሙዲ ሕዝበኝነትን “በጥቂቶች ላይ ያተኮር ርዕዮተ ዓለም ነው” ሲል ይገልጸዋል። ከፖለቲካ አጀንዳው ከፊሉን ብቻ የሚመለከት ነው። የተሻለው የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ሥርዓት ምን እንደሆነ ምንም ሐሳብ የለውም።

“ብዙዎቹ ስኬታማ ሕዝበኞች ሕዝበኝነትን ከሌላ ርዕዮተ ዓለም ጋር ያዋህዱታል። ይህንን አስተናጋጅ ርዕዮተ ዓለም ተብሎ ይጠራል። እነዚህም መሠረታዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰው” ብለዋል።

“በአጠቃላይ ካየነው አብዛኞቹ የቀኝ ክንፍ ሕዝበኞች ሕዝበኝነትን ከየአገሬው ተወላጆች ጋር ያያይዙታል። አብዛኞቹ የግራ ክንፍ ሕዝበኞች ሕዝበኝነትን ከሶሻሊዝም ጋር አዋህደው ያቀርቡታል።”

የሕዝበኛ መሪ ባህሪያት ምንድ ናቸው?

በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ጃን-ዌርነር ሙለር ‘ዋት ኢዝ ፖፑሊዝም?’ በተሰኘው መጽሐፋቸው ሕዝበኛ መሪዎች ዋናውን “የሕዝብ ፈቃድ” እንወክላለን ይላሉ በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

“ሕዝበኞች ጎልተው እንዲወጡ የሚያደርጋቸው 'የእውነተኛው ሕዝብ' ወይም ‘ድምጹን የማያሰማው አብዛኛው’ ተወካዮች ነን ማለታቸው ነው።”

“በዚህ ምክንያትም ተፎካካሪዎቻቸውን በሙሉ ሕገ-ወጥ ናቸው በማለት ያወግዛሉ። ሌሎቹን ተፎካካሪዎች 'ሙሰኞች' እና 'የማይረቡ' ናቸው በማለት ያብጠለጥሏቸዋል።

ዶናድል ትራምፕ እንደ ጥሩ የሕዝበኛ ምሳሌ ይቀርባሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናድል ትራምፕ እንደ ጥሩ የሕዝበኛ ምሳሌ ይቀርባሉ

በዚህ ረገድ ካየነው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጥ የሕዝበኝነት ምሳሌዎች አንዱ ተደርገው ይወሰዳሉ።

ሕዝበኞች ራሳቸውን እንደ “ጠንካራ” አድርገው ያቀርባሉ። ፀረ-ስደተኛ፣ አምባገነናዊ አቋምን በማጣመር እና ብዙ ባህላዊ ፖለቲከኞች ሊያስወግዷቸው የሚፈልጓቸውን ተግባራዊ የማይሆኑ ቃሎችን ይገባሉ።

የሕግ አውጪዎችን ወይም የፍትህ አካላትን የሚያካትቱ የተወሳሰቡ ዲሞክራሲያዊ መንገዶችን ከመከተል ይልቅ ሕዝበ ውሳኔን፣ የፕሬዝዳንታዊ ድንጋጌዎችን ወይም የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዞችን በማስተላለፍ “ዓላማቸውን ማስፈጸምን” እንደ መሳሪያ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

ቤንጃሚን ሞፊት ከተለመደው የሕዝበኛ መሪ ጋር የተያያዙ በርካታ ባህሪያትን ተመልክተዋል።

አንደኛው “መጥፎ ሥነ ምግባር” ወይም የፖለቲከኞች መለያ ያልሆነ ባህሪን ማሳየት ነው። ይህ ደግሞ በትራምፕ እና በቅርቡ ደግሞ በአርጀንቲናዊው ሚሌ ታይቷል። ሚሌ ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ቦታ የኤሌክትሪክ መጋዝ በመያዝ የመንግሥት ወጪን ለመቀነስ ቃል ገብተዋል።

“ችግርን ማስቀጠልን” እና ሁልጊዜም ራሳቸውን እንደ ተጠቂ ያቀርባሉ።

ሞፊት አክለውም “ሁልጊዜም ጥፋት እየመጣ መሆኑን እና ማስተካከያ ዘዴውን እነሱ ብቻ እንደሚያውቁት ያቀርባሉ” ብለዋል።

ሁዋን ፔሮን እና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሁዋን ፔሮን እና ባለቤታቸው

ምርጥ የሕዝበኛ መሪ ምሳሌዎች እነማን ናቸው?

አርጀንቲናዊው ሁዋን ዶሚንጎ ፔሮን ብዙ ጊዜ እንደ ዋና የሕዝበኛ ምሳሌ ይጠቀሳሉ። እአአ በ1974 ሕይወታቸው ቢያልፍም ስማቸው አሁንም የፖለቲካ እና የአርጀንቲ እና ማኅበረሰብ ዋነኛ መከፋፈያ ነው። ፔሮኒስት ወይስ ፀረ-ፔሮኒስት ነዎት? የሚል ጥያቄ መቅረቡ የተለመደ ነው።

ከቀናት በኋላ ደግሞ ሌላኛው ሕዝበኛ መሪ ሚሌ መንበረ ሥልጣኑን ይረከባሉ።

በተዘበራረቀው ፀጉራቸው፣ መያዣ መጨበጫ ባጣው ፍላጎታቸው እና ወጣ ባለ ልምዳቸው “ኤል ሎኮ” (እብዱ ሰው) የሚል ቅጽል ስምም አግኝተዋል።

የአገሪቱን መገበያያ ገንዘብ ፔሶን በአሜሪካ ዶላር ለመቀየር ወስነዋል። ማዕከላዊ ባንክን “መበተን” እና የመንግሥት ሥራዎችን ማሳጠርን ጨምሮ ትልልቅ ለውጥ ለማድርግ ቃል ገብተዋል።

“ላቲን አሜሪካ የሕዝበኝነት እንቅስቃሴ ምልክት ናት” ይላሉ ኢምዳት ኦነር የተባሉት የአውሮፓ የሥነ ሕዝብ ጥናት ማዕከል ባልደረባ።

“የግራ ክንፍ ሕዝበኛው ሁጎ ቻቬዝ ትልቅ ምሳሌ ነበሩ። ወደ ፖለቲካው የገቡት ሳይታወቁ ቢሆንም በቬንዙዌላ የነበረውን የሁለት ፓርቲ ሥርዓት ቀይረው እስከ ዕለተ ሞታቸው በሥልጣን ላይ ቆይተዋል።”

“ሕዝበኛነት ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው” ይላሉ ሞፊት። ትራምፕን ደግሞ “የቀኝ ክንፍ ሕዝበኛ ድንቅ ምሳሌ” በማለት ይጠቅሷቸዋል።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን እና ሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን እና ሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ

ሞፊ አክለውም “በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በጣም የተሳካላቸው ሕዝበኛ እና ቢያንስ በምርጫ ሥልጣንን በመያዝ እየመሩ የሚገኙት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ናቸው።

“በሕንድ ያለው ፖለቲካ ሁሉ በሞዲ ዙሪያ የሚሽከረከረው ነው። በዜጎች እና በልሂቃን መካከል ልዩነት ለመፍጠር ችለዋል። ሂንዱዎችን 'እውነተኛ ሰዎች' በማለት በነባር ዜጎች ዘንድ ስሜቱን እያራገቡ ነው” ብለዋል።

የቱርክ ሬሲፕ ጣይብ ኤርዋጋንም ሕዝበኛ ፖለቲከኛ በመባል ይታወቃሉ።

“ራሳቸውን ዝቅተኛ ግምት እንደተሰጣቸው አድርገው ያቀርባሉ። ከአስቸጋሪው የኢስታንቡል መንደር በመነሳት የቆየውን የቱርክ የከማሊስ ሪፐብሊክን በድፍረት እንደተጋፈጡ ያቀርባሉ” ሲሉ የዘራይዝ ኤንደ ራይዝ ኦፍ ፖፑላሪዝም ጸሐፊው ፕሮፌሰር ሙለር ጽፈዋል።

የኔዘርላንዱ ጌርት ዋይልደርስ፣ የሃንጋሪው ቪክቶር ኦርባን፣ የፈረንሳይዋ ማሪን ለፔን፣ የቬንዙዌላው ኒኮላስ ማዱሮ እና የብሪታኒያው ቦሪስ ጆንሰን በብዙዎች ዘንድ ሕዝበኛ ተብለው ይጠቀሳሉ።

ካስ ሙዲ፣ የብራዚሉን ጃየር ቦልሶናሮን ሕዝበኛ አድርገው አይመለከቷቸውም። ብራዚላዊው የግራ ክንፉን ብቻ ውድቅ ያደርጉታል እንጂ ስለቀኙ ክንፍ ምንም አለማለታቸውን በምክያትነት ያነሳሉ።

በላቲን አሜሪካ በህዝበኛ በመሆን የሚጠቀሱት ሁጎ ቻቬዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሕዝበኝነት ለዲሞክራሲ ጠንቅ ነውን?

ሙዲ ጠበብ ተደርጎ ከታየ ሕዝባዊ ሕዝበኝነት ዲሞክራሲያዊ ነው። ምክንያቱም ፖለቲካው “የሕዝብ ፍላጎት” እንዲያንጸባርቅ ይፈለጋል።

“ነገር ግን በመሠረቱ ከሊበራል ዲሞክራሲ ዋና ሀሳብ ጋር ይጋጫል። ሕዝበኝነት ሕብረተሰቡ የተለየ ፍላጎት እና እሴት ያላቸው በሙሉ ሕጋዊ ናቸው የሚል ሃሳብን ያቀፈ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ፕሮፌሰር ሙለር ሕዝበኞች በቂ ሥልጣን ቢያገኙ ትክክለኛ “ሰዎች” ብለው የማይቆጥሯቸውን በሙሉ የሚያገል ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ይፈጥራሉ ሲሉ ይከራከራሉ።

“የአካባቢ ቀውስ፣ የቀጠለው የኢኮኖሚ ችግር . . . ዘልቆ መግባት እና ቀላል መፍትሄዎችን በመናገር፣ በከባድ ቀውስ ወቅት ጠላት ላይ ማነጣጠር መቻል አስፈላጊ ነው” ይላሉ።

“ፖፑሊስቶች ዳኞችን፣ ሚዲያዎችን እና የመሳሰሉት ገለልተኛ ተቋማት የሕዝብን ድምጽ ለማደናቀፍ መንገድ የዘጉ አድርገው ማቅረብ ይቀናቸዋል። ይህ መንገድ ለዴሞክራሲ ጠንቅ ነው። ነገር ግን አንድ እና ብቸኛ ስጋት አድርጎ መቁጠርም ፍሬያማ አይሆንም። ሰዎችን የሚስብበት ምክንያት አለው” ሲሉ ያክላሉ።

“አሁን ሕዝበኝነት የዋናው ፖለቲካ አካል መሆኑን መካድ ከባድ ነው። በቀላሉም አይጠፋም። በግሌ ይህ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዋነኛ የፖለቲካ ክስተት ይመስለኛል።”