አሜሪካ ለታይዋን የ1.1 ቢሊየን ዶላር የጦር መሣሪያ ሽያጭ ማጽደቋ ቻይናን አስቆጣ

በታይዋን በኤፍ-16 ሚሳይሎች ሲጫኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ፣ ቻይና እንደግዛቷ ለምትመለከታት ታይዋን 1.1 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ ለመሸጥ መስማማቷ ቻይናን አስቆጣ።

የጦር መሣሪያ ሽያጭ ስምምነቱ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአየር ጥቃቶችን የሚከታተል መቆጣጠሪያ (ራዳር)፣ ፀረ- መርከብ እና ፀረ- አየር ሚሳይልን ያካትታል።

አሜሪካ ይህንን ስምምነት ያጸደቀችው፣ ባለፈው ወር የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ከ25 ዓመታት በኋላ ታይፔይን የጎበኙ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆኑ በኋላ ነው።

በአሜሪካ ዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ አሜሪካ ስምምነቱን እንድትሰርዝ የጠየቀ ሲሆን፣ ካልሆነ ግን የአጸፋ እርምጃ ይጠብቃታል ብሏል።

ቃል አቀባዩ ሊዩ ፔንግዩ፣ ስምምነቱ “በዋሽንግተን እና በቤይጂንግ መካከል ያለውን ግንኙነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ብለዋል።

“እየታዩ ካሉ ሁኔታዎች አንጻር ቻይና ሕጋዊ እና አስፈላጊ የሆኑ የአጸፋ እርምጃዎችን በቆራጥነት ትወስዳለች” ሲሉም ቃል አቀባዩ አስጠንቅቀዋል።

ቤይጂንግ ራስ ገዝ የሆነችዋን ደሴት የምታያት የራሷ አካል እንደሆነች ግዛት ሲሆን፣ ካስፈለገ በኃይልም ቢሆን ከዋናው መሬት ጋር አንድ መሆን እንዳለባት ደጋግማ ገልጻለች።

ባለፈው ወርም የአሜሪካ ልዑካን የታይዋን ጉብኝትን ተከትሎ ቻይና በታይዋን አቅራቢያ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ልምምድ አካሂዳለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሣሪያ ለመሸጥ የተስማማችው አርብ ዕለት ቢሆንም፣ በስምምነቱ ላይ የታይዋን ደጋፊ የሆነው የአሜሪካ ኮንግረስ ድምጽ መስጠት ይኖርበታል።

እንደ አሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት (ፔንታጎን) የመከላከያ ደኅንነት ትብብር ክፍል ከሆነ፣ ጥቅል የጦር መሣሪያ ሽያጩ 655 ሚሊየን ዶላር የራዳር መቆጣጠሪያ ሥርዓት እና 355 ሚሊየን ዶላር ደግሞ የጦር መርከቦችን ሊያሰምጥ የሚችል 60 ሃርፑን የተባሉ ሚሳይሎችን ያካትታል።

ከዚህም በተጨማሪ 85.6 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ከመሬት ወደ አየር እና ከአየር ወደ አየር የሚተኮሱ ሚሳይሎችንም ይዟል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ስምምነቱ “ለታይዋን ደኅንነት አስፈላጊ ነው” ያሉ ሲሆን፣ ቤይጂንግ በታይዋን ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንድታቆም በምትኩ ትርጉም ያለው ውይይት እንድታደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

“እነዚህ የታቀዱ የጦር መሣሪያ ሽያጮች ታይዋን ጦሯን ለማዘመን እና አስተማማኝ የመከላከል አቅምን ለማጠናከር የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ የተደረገ የተለመደ ድጋፍ ነው” ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ባለፈው ወር ፔንታጎን የአሜሪካ የጦር መሣሪያን ለውጭ አጋሮች የሚደረግ ሽያጭን ለማቀላጠፍ የሚረዳ ግብረ ኃይል ማቋቋሟን ዎል ስትሪት ጆርናል አርብ ዕለት ዘግቧል።

የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ታይዋን የጦር መሣሪያዎቹን ለመግዛት ትዕዛዙን ያቀረበችው ከዓመታት በፊት ቢሆንም በተሟላ መልኩ ሳይፈፀሙላት ቆይተዋል ብለዋል።

እንደ 'ድፌንስ ኒውስ' ከሆነ ሽያጩ ሳይፈፀም የቆዩባት መሣሪያዎች የጦር መርከብ ማስመጥ የሚያስችለው ሃርፑን እና ሰቲንገር ሚሳይሎች ሲሆኑ እነዚህ መሣሪያዎች በምትኩ ለዩክሬን ተልከዋል።

የጦር መሣሪያ ሽያጭ ስምምነቱ ብቻም ሳይሆን ቻይናን ሊያስቆጣ የሚችል ሌላ እርምጃ ከባይደን አስተዳደር ተሰምቷል።

ይህም የባይደን አስተዳዳር በቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ጊዜ ተግባራዊ በሆነውና ከቻይና በገቡ ምርቶች ላይ የተጣለው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ታሪፍ ባለበት እንደሚቆይ መግለጹ ነው።

የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መሥሪያ ቤትም የ2018/2019 ከንግድ ድርጅቶች እና ሌሎች ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር የነበሩ ግዴታዎችን ባለበት እንዲጠብቅ ጥያቄ እንደቀረበለት አሳውቋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በአገሪቷ ውስጥ የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለማቃለል ታሪፉን ለማንሳትም እያሰቡ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አርብ ዕለት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን የ13.7 ቢሊየን ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ ለማድረግ ኮንግረሱ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል።

ፔንታጎን አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን ያደረገችው አጠቃላይ የጦር ድጋፍ ከ13 ቢሊየን ዶላር በላይ መሆኑን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።