ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቆጮ እንደ ኬክ ያሉ ምግቦችን መሥራት ይቻላል አለ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንሰት ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ከቆጮ እንደ ኬክ ያሉ ምግቦች መሥራት ይቻላል አለ።
በዩኒቨርሲቲው መምህር እና ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አዲሱ ፍቃዱ (ዶ/ር) ከቆጮ እንደ ኬክ እና ኩኪስ የመሳሰሉ ምግቦችን በማዘጋጀት አጠቃቀሙን እና የሚቀርብበትን መንገድ ማሻሻል እንደሚቻል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከቆጮ አዘገጃጀት ጋር በተያያዘ ያስተዋወቃቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለአገር ገቢ ከማስገኘቱ በተጨማሪ ቆጮ ለማምረት ሴቶች ያወጡት የነበረውን ጉልበት መቀነሱንም ተጠቃሚዎች ይገልጻሉ።
“ሁለት ሆነን አንድ እንሰት ፍቀን ለመጨረስ እስከ አራት ቀን ይወስድብን ነበር። አሁን ግን 30 ደቂቃ ብቻ ይበቃናል” ይላሉ የጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት እና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ውጤትን መጠቀም የጀመሩት ገበያነሽ አለታ።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት እንሰት የሚፍቅ፣ ቆጮው በፍጥነት እንዲብላላ የሚያደርግ እንዲሁም ቆጮ የሚፈጭን ጨምሮ አዳዲስ ፈጠራ አስተዋውቆ የአካባቢውን ማኅብረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
የዩኒቨርሲቲው እንሰት ፕሮጄክት አስተባባሪ የሆኑት አዲሱ ፍቃዱ (ዶ/ር) ባለፉት 10 ዓመታት እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እውነት ለማድረግ ጥናት እና ምርምር ሲደረግ መቆየቱን ይገልጻሉ።
“እንሰት ላይ የተሰሩት አብዛኞቹ ሥራዎች ጥናትን መሠረት ያደረጉ ናቸው። እንሰት የሚያመርቱ አርሶ አደሮች የመሚያጋጥማቸውን ችግር በጥናት በመለየት ነው የሠራነው” ይላሉ።
እንሰት ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት ሃብት ነው የሚሉት አዲሱ (ዶ/ር)፤ “በአንድ አርሶ አደር ግቢ ውስጥ ከ50 እስከ 100 የእንሰት ዛፍ ዝም ብሎ ነው የሚቀመጠው። ከቤት አልፎም ሌላ ጥቅም ላይ ሲውል አልታየም” ይላሉ።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቆጮ ማምረት ሂደትን ቀላል ከሚያደርጉ የቴክኖሎጂ አበርክቶዎቹ መካከል አንዱ ቆጮ የሚፍቀው ማሽን ነው።
“ቆጮን በባሕላዊ መንገድ መፋቅ ጉልበት እና ጊዜ ይፈጃል። ቆጮ ለመፋቅ ጥቅም ላይ የሚውለው መሳሪያም በጣም ኋላ ቀር ነው። አጥንት ወይም እንጨት ነው ለመፋቅ የሚጠቀሙት” ይላሉ አዲሱ (ዶ/ር)።
ሌላኛው ዩኒቨርሲቲው ያስተዋወቀው ማሽን ደግሞ ቆጮ በፍጥነት እንዲብላላ የሚያደርግ ዘዴ ነው።
“ቆጮ እስኪብላላ ድረስ ሁለት ወር እና ከዚያ በላይ ሊወስድ ይችላል። ይህ ማለት ግቢ ውስጥ ያለን እንሰት አንድ አርሶ አደር መብላት ቢፈልግ ሁለት ወር እና ከዚያ በላይ መጠበቅ ግድ ይላል። ይህን ለማስቀረት አዲስ እርሾ በላብራቶሪ ውስጥ አምርተናል” ይላሉ አዲሱ (ዶ/ር)።
ይህ እርሾ ቆጮ ከ7 አስከ 10 ባሉ ቀናት ውስጥ እንዲብላላ በማድረግ ለአገለግሎት እንዲበቃ ያደርጋል።
ቆጮ በባሕላዊ መንገድ እንዲብላላ የሚደረገው መሬት ውስጥ በመቅበር ሲሆን፣ ይህ ረዥም ጊዜ ከመውሰዱ በተጨማሪ ምርቱ ለብልሽት እና ለብክነት ይጋለጣል።
“ቆጮ ጉድጓድ ውስጥ ሲቀበር ጎርፍ ይገባበታል። ይህ እንዳይሆን ዘመናዊ ቆጮ ማስቀመጫ እና ማብላያ መሳሪያ አዘጋጅተን ለአርሶ አደሮች ለማስተዋወቅ እና ለማከፋፈል እየሠራን እንገኛለን” በማለት በዩኒቨርሲቲው መምህር እና ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አዲሱ ፍቃዱ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ቆጮ ፍቀን ስንቀብረው ትል ይገባበታል፣ ንጽሕናም አይኖረውም። በጣም አስቸጋሪ ነው” የሚሉት ገበያነሽ፤ ዩኒቨርሲቲው የሠራው ማሽን የቆጮውን ንጽሕና በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ነው ይላሉ።
ዩኒቨርሲቲው ሌላ ያስተዋወቀው የቴክኖሎጂ ውጤት የእንሰት ስር የሚፈጭ ማሽን ነው።
ቆጮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት ለምግብነት የሚውል ተክል ቢሆን በአብዛኛው በቂጣ እና በገንፎ መልክ እንጂ በተለያየ ዓይነት ማዘጋጀት የተለመደ አይደለም።
አዲሱ (ዶ/ር) በተለያየ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ዱቄት ከቆጮ ማምረት እንደሚቻል ይናገራሉ፤ “ከእንሰት ድፎ ዳቦ መጋገር ይቻላል፣ እንዲሁም ኬክ እና ኩኪስ ማዘጋጀትም ይቻላል” ብለዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አርሶ አደሮች እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲጠቀሙ የተለያዩ ማዕከላትን አደራጅቶ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ተመራማሪው ይገልጻሉ።
ዩኒቨርሲቲው ባቋቋማቸው ሦስት ማዕከላት ከ3ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆነ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ያስተዋወቃቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቃሚ የሆኑት ገበያነሽ አለታ፣ እንሰትን በባህላዊ መንገድ ስንፍቅ “እጃችን እስኪዝል ነበር የምንሰራው። ጉዳትም አለው። በጣም በጣም አድካሚ ነበር” ይላሉ።