“ከትግራይ በኩል በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው” - መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት

ዶ/ር ለገሰ ቱሉ
የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ለገሰ ቱሉ

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ላይ ከሰሞኑ “በትግራይ ክልል በኩል የሚታየው አዝማሚያ”፤ “ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ” እንደሆነ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ።

ዶ/ር ለገሰ፤ “ወሰንን በኃይል እናስከብራለን” የሚል አካሄድ “የትግራይ ሕዝብን ለሌላኛው ዙር ስቃይ እና እንግልት የሚዳርግ ነው” ሲሉም አሳስበዋል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 26/2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

የዶ/ር ለገሰ ጋዜጣዊ መግለጫ “ባለፉት ስድስት ዓመታት የለውጥ ጉዞዎች”፣ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የበጋ ልማት ሥራዎችን የተመለከተ ነበር።

የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮችን ባነሱበት የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ላይ ከሰሞኑ “በትግራይ ክልል በኩል በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች” ታይቷል ያሉትን “አዝማሚያ” ጠቅሰዋል።

የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት “የትግራይ ክልል ወደ ተሟላ የሰላም ሁኔታ እንዲመለስ እና የትግራይ ሕዝብ መብቶች እንዲከበሩ ፅኑ ፍላጎት” እንዳለው የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ሥራዎችን ማከናወኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

“የፌደራል መንግሥት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተሻገሩ በርካታ ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስዷል። ይህ ይበልጥ እንዲጎለብት እና ሰላም እንዲፀና አሁንም ሁሉንም ዓይነት ጥረቶች እና እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል” ሲሉ የፌደራል መንግሥቱን ጥረቶች አብራርተዋል።

ይሁንና ከሰሞኑ “የአማራ አዋሳኝ” በሆኑ አካባቢዎች ይህንን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ያስቆመውን ስምምነት የሚጥስ “አዝማሚያ” መታየቱን ተናግረዋል።

ዶ/ር ለገሰ፤ “ታይቷል” ያሉት አዝማሚያ ምን እንደሆነ በግልፅ ባይጠቅሱም የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን ከሚያወዛግቡ አካባቢዎች መካከል በሆኑት በራያ ወረዳዎች ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ የተኩስ ልውውጦች ተደርገዋል።

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ በአማራ ክልል ስር መሆኑት እነዚህን አካባቢዎች የሚያስተዳድሩ አካላት “ከትግራይ ክልል መጥተዋል” የሚሏቸው ታጣቂዎች ተኩስ እንደከፈቱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰንብተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአማራ ክልል ባለፈው ሳምንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “ከነበረበት አካባቢ በመንቀሳቀስ የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል” ሲል ተመሳሳይነት ያለው ክስ አቅርቦ ነበር።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ከክልሉ ተነስተው ጥቃት የከፈቱ ታጣቂዎች እንደሌሉ በመግለጽ የቀረበውን ክስ አስተባብሏል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ በዛሬው መግለጫቸው፤ “የሚነሱ ጥያቄዎች እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ወሰንን በኃይል እናስከብራለን የሚል አካሄድ ካለፈው ስህተት አለመማርን ያመለክታል” ብለዋል።

ዶ/ር ለገሰ፤ “[ድርጊቱ] በአሁኑ ወቅት ሰላሙን እያፀና የሚገኘውን የትግራይ ሕዝብን ለሌላ ዙር ስቃይ እና እንግልት የሚዳርግ ነው” ሲሉም ከሰሞኑ ለተፈጠረው ችግር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ተጠያቂ አድርገዋል።

ከፌደራል መንግሥት እንዲሁም ሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራር የተወጣጣ ዐቢይ ኮሚቴ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ለገሰ፤ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝው በሕዝበ ውሳኔ ነው የሚለውን የፌደራሉን መንግሥት አቋም ገልጸዋል። “ነገሩን የቀያየረው የፌደራል መንግሥት እንዳልሆነ መረሳት የለበትም። ነገሩ እንዲቀያየር ያደረገው አካል መልሶ ከሳሽ መሆንም አይችልም” ሲሉም በመፍትሔነት የያዘውን አቋም አለመቀየሩን ጠቅሰዋል።

ዶ/ር ለገሰ፤ በዚህ ዓይነት መልኩ “ጉዳዩ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ የፌደራል መንግሥት ማለትም የመከላከያ ሠራዊታችን ሰላም እና ደኅንነት ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በትብብር ይቆጣጠራል፣ ይጠብቃል” ብለዋል። ተፈናቃዮችም “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ” ወደ ቅየቸው መመለስ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የአካባቢው ሕዝብ በምርጫው የአካባቢ አስተዳደሮችን መመሥረት እንዳለባቸው ያነሱት የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሩ፤ “ሁኔታው ሲረጋጋ” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “በገለልተኝነት” ሕዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂድ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ይህንን “አቅጣጫ አክብረው” በአካባቢው ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው እና በመከላከያ ሠራዊቱም ላይ እምነት ሊጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የወሰን እና የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን እነዚህ አካባቢዎች በተመለከተ ችግሮች ካጋጠሙ “በመግለጫ እርስ በእርስ ከመወቃቀስ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እና በድርድር” መፍታት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

በሁለቱ ክልሎች “ሰላም እና መረጋጋት እንዳይመጣ በፅንፈኛ እና ፀረ ሰላም ኃይሎች” የተዘረጋ “ሕገወጥ መሳሪያ ዝውውር እና ንግድ ኔትወርክ” መኖሩን ዶ/ር ለገሰ በመግለጫው ላይ አንስተዋል።

አማራ እና ትግራይ ክልሎች ይህንን ለመቆጣጠር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ “ሕዝቡ መብቱን ተጠቅሞ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ቢደረስ እንኳ ይህ ሕገወጥ የመሳሪያ ንግድ እና ዝውውር ኔትዎርክ መፍትሔ ካላገኘ በአካባቢው ዘላዊ ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም” ብለዋል።