ድብቁ የወሲብ ንግድ በሶማሊያ

በጨለማ ውስጥ ከጀርባ የምትታይ ሴት

የፎቶው ባለመብት, LEYLA JEYTE

የምስሉ መግለጫ, በሞቃዲሾ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ተደራራቢ በደሎች የሚደርስባቸው ሲሆን የሚሰማቸው ግን የለም

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ነዋሪ የሆኑ ሁለት ሴቶች እንዴት ምስጢራዊ ወደሆነው የወሲብ ንግድ እንደተሳቡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የግለሰቦቹን ማንነት ለመጠበቅ ስማቸውን ቀይረናል።

ለዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስትናወጥ በነበረችው ሶማሊያ ውስጥ ጦርነቱ ጋብ ቢልም፣ አሁንም ሁከቶችን ማስተናገዷ አልቀረም።

ደማቅ እና ግርግር የበዛባት የሞቃዲሾዋ ሊዶ የባሕር ዳርቻ ጦርነቱን ለመርሳት እየሞከረች ያለች ይመስላል።

የባሕር ዳርቻዋ መዝናኛዎች በሰዎች ተሞልተዋል።

የገበያ ማዕከሏቿ፣ ሆቴሎች እና ጣፋጭ ምግቦቿ ለጎብኚዎች የሚታወቁ መስህቦች ናቸው።

ሆኖም በአቅራቢያው ደግሞ ሌላ አማራጭ ትዕይንት አለ።

ጭፍራ፣ የአደንዛዥ ዕፅ እንዲሁም የወሲብ ንግድ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህች ድብቅ እና ምስጢራዊ በሆነችው የከተማዋ ክፍል ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ሴቶች እና ወጣቶች ችግረኛ ናቸው።

የ22 ዓመቷ ፊርዶሳ ለሦስት ዓመታት በወሲብ ንግድ ስትተደዳር ቆይታለች።

በሞቃዲሾ ዋርዲግሌይ ወረዳ በጥይት በተበሳሳ የመኖሪያ ህንጻ ውስጥ በቀይ መጋረጃዎች በተሸፈነ ጨለማ ክፍል ውስጥ ተቀምጣለች።

ለስላሳ ድምጽ ያላትን ቀጠን ያለችው ፊርዶሳ ምድጃዋን እያየች ምን እንደደረሰባት ትናገራለች።

ፊርዶሳ ከቤተሰቦቿ የተለየችው በ19 ዓመቷ ነው።

በሶማሌ ማኅበረሰብ ውስጥ ወጣት ሴቶች ከማግባታቸው በፊት የቤተሰባቸውን ቤት ለቆ መውጣት ያልተለመደ ክስተት ነው።

ነገር ግን በቤት ውስጥ በሚፈጸም ጥቃት ወይም ከሌሎች የቤተሰብ አባላት ጋር ባለ ጥል አንዳንዶች ቤታቸውን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ።

“መጀመሪያ ላይ ትቻቸው ለመሄድ አላሰብኩም ነበር፤ ነገር ግን ከእንጀራ እናቴ ጋር መኖርን መታገስ አልቻልኩም” ትላለች ፊርዶሳ።

“እናቴ በህጻንነቴ ከሞተች በኋላ አባቴ ሌላ ሴት አገባ። በከፍተኛ ሁኔታ ትበድለኝ እና ታሰቃየኝ ነበር። ይህም ቢሆን አባቴ ሁልጊዜም ከእሷ ጎን እንደቆመ ነው” በማለት ታስረዳለች።

ፊርዶሳ ከቤት ከወጣች በኋላ ከቦታ ወደ ቦታ እየተንቀሳቀሰች አዳዲስ ጓደኞችን አፈራች።

እነዚህ አዳዲስ ጓደኞቿም የሚያስቡላት መስሏት ነበር።

ነገር ግን አሁን ሁኔታዎችን መለስ ብላ ስትቃኝ እውነተኛ ጓደኞች እንዳልሆኑ ተረዳች።

እንደ ሞርፊን፣ ትራማዶል እና ፔቲዲን የተባሉ አደንዛዥ እና አነቃቂ ዕጾች ሱሰኛ ሆነች።

ለዚህም ምከንያቱ እነዚህ ጓደኞቿ ነበሩ።

በሊዶ የባሕር ዳርቻ የመዝናኛ ስፍራ ያለውን የድብቅ ፓርቲ ትዕይንት መቀላቀል ብቻ ሳይሆን፣ የወሲብ ንግድ ሥራንም ተዋወቀች።

ፊርዶሳ ብዙም ሳትቆይ በወሲብ ንግድ ውስጥ ጠልቃ ገባችበት።

በሆቴሎች፣ በማታውቃቸው ሰዎች ቤቶች፣ ሰወር ባሉ ቦታዎች ራሷን ታገኘው ጀመር።

በአሁኑ ወቅት በቂ ደንበኞችን ያፈራች ሲሆን፣ የሚያገኟትም በስልኳ ነው።

“ስልኬ እስኪጠራ ድረስ እጠብቃለሁ። ከዚያም ከሰዎቹ ጋር ለወሲብ እወጣለሁ። አንዳንድ ጊዜም ሴት ጓደኞቼን ወንዶች ሲጠይቋቸው ይደውሉልኛል” ትላለች።

የሞቃዲሾው ሊዶ የባሕር ዳርቻ

የፎቶው ባለመብት, LEYLA JEYTE

የምስሉ መግለጫ, ሞቅ ካለው ከሞቃዲሾው ሊዶ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በርካታ ሴቶች በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ

“ለሱሴ ገንዘብ ያስፈልገኛል”

ደንበኞቿ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ናቸው።

“እነዚህ መካከል በርካቶቹ መጀመሪያ ላይ የሴት ጓደኞቼ ወንድ ወዳጆች ነበሩ፤ ከዚያም ከማላውቃቸው ወንዶች ጋር ወሲብ ወደ መፈጸም ተቀየረ። ለሱሴ የሚሆን ገንዘብ ስለሚያስፈልገኝ ተጋላጭ ሆንኩኝ” ትላለች ፊርዶሳ።

በወሲብ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎችን በተመለከተ ምንም ዓይነት ይፋዊ መረጃ ባይኖርም እነ ፊርዶሳ እና ሌሎች በሰጡት ምስክርነት ይህ አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች የገቡበትን አደገኛ ሕይወት ፍንጭ የሚሰጥ ነው።

ሌላኛዋ በወሲብ የንግድ ሥራ የምትተዳደረው ሆዳን ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል በዚህ ሥራ ላይ ቆይታለች። እንደ ፊርዶሳ፣ ሆዳንም ከቤቷ ሸሽታ ነው በሞቃዲሾ ድብቅ የወሲብ ንግድ ውስጥ የገባችው።

ልክ እንደ ሆዳን እና ፊርዶሳ በአካባቢው በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ወጣቶች ራሳቸውን ለመደጎም አቅሙ የሌላቸው ናቸው።

“አብዛኛውን ምሽቶች የማሳልፈው በሆቴሎች ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን በዚህ ንግድ የተሰማሩት በርካታ ወጣት ሴቶችም በተመሳሳይ መልኩ ነው የሚያሳልፉት። ሁሉንም አይነት ወንዶች እናገኛለን። እነዚህን ወንዶች ተከትለን ስንሄድ ወደ ከፋ ደረጃ የሚያመራበት ብዙ አጋጣሚ አለ” ትላለች ሆዳን።

በሶማሊያ የወሲብ ንግድ ሕገወጥ በመሆኑ እነዚህ ወጣት ሴቶች ጥቃት ቢደርስባቸው ከባለሥልጣናት ምንም ዓይነት ምላሽ አያገኙም።

በጽሁፉ ላይ በተነሱት ጉዳዮች ዙሪያ ፖሊስ እና የሴቶች እና የሰብዓዊ መብት ልማት ሚኒስቴር ባለሥልጣናትን ቢቢሲ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

“ሴቶቹ ከወንዶች ጋር አድረው ሲመጡ አብዛኛዎቹ ሰውነታቸው አባብጦ እና ቆስሎ ነው” በማለት ሆዳን ትናገራለች።

ፊርዶሳም ተመሳሳይ ጥቃት አጋጥሟታል።

“ከዚህ ቀደም ወንዶች በመረጡት ቦታ ሄጄ ወሲብ እንፈጽም ነበር። ነገር ግን አንድ ምሽት አንድ ሰው ደበደበኝ፣ ደም በደም ሆንኩኝ፤ ፊቴም ቆሳሰለ። ይህ ሁሉ በዋጋ ስላልተስማማን ነበር” ስትል የደረሰባትን ታስረዳለች።

“ከዚያን ወቅት ጀምሮ ምንም ያህል ቢከፍሉኝ ከወንዶች ጋር ወደማላውቃቸው ወይም ወደተገለሉ ቦታዎች አልሄድም። በጣም አደገኛ ነው። ምንም ጉዳት እንዳይደርስብኝ ሆቴሎችን እመርጣለሁ። የሆነ ነገር ከደረሰብኝም ወዲያውኑ እጮሃለሁ። እናም እርዳታም አገኛለሁ” ትላለች።

“በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ በርካታ ሴቶች ዕድለኞች አይደሉም። ወንዶችን ተከትለው ወደእነሱ ቤት እና ወደ ሰዋራ ስፍራ የሚሄዱ ሴቶች ጥቃት ይደርስባቸዋል። አልፎ ተርፎም ይደፈራሉ። አንዳንድ ጊዜም በቡድን ነው የሚደፈሩት” በማለት ታስረዳለች።

ሴቶቹ በሚደፈሩበት ወቅት በቪዲዮ ይቀርጿቸውና ለማስፈራሪያነት እንደሚጠቀሙበት ትናገራለች።

“በማስፈራራትም ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል” ትላለች ሆዳን።

ሞባይል የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, LEYLA JEYTE

የምስሉ መግለጫ, አንዳንዶቹ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ደንበኞቻቸው በስልክ ነው የሚጠሯቸው

“የምንወዳቸውን ሰዎች መጋፈጥ አንችልም”

ሆዳን እንደምትለው ሴቶቹን በአደንዛዥ ዕፅ ካደነዘዟቸው በኋላ ቪዲዮ እንደሚቀርጿቸው እና የሚያገኙትንም ገንዘብ እንዲያካፍሏቸው ያስገድዷቸዋል።

“ገንዘብ አንሰጥም ቢሉ ቪዲዮዎቹን እንደ ማስፈራሪያ ይጠቀሙበታል፤ ድብደባ እና አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። አንዳንዶቹም ሴቶቹን በበለጠ ለማሰቃየት ቪዲዮዎቹን ያጋሩታል” ትላለች።

የብሪታንያው የቴሌቭዥን ኔትወርክ ቻናል 4 በቅርቡ ባወጣው ዘገባ መሠረት፣ ከወሲብ ንግድ ውጭ ያሉ ሶማሌ ሴቶች ላይም ቢሆኑ እንደነዚህ አይነት ቪዲዮዎች ለማስፈራሪያነት ይወጣባቸዋል።

“በርካታ የማውቃቸው ወጣት ሴቶች ይህ ያጋጥማቸዋል። ይህንን ለመናገር በጣም ስለሚያፍሩም ዝምታን ይመርጣሉ። በዚህ ሕይወት ላይ ብዙ ስለቆየን ምን እንደሚያጋጥም እናውቃለን” ትላለች።

በግጭት ቀጠናዎችም ሆነ ሁከቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ወሲባዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚባባስ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ያሳያል።

“በአገሪቱ ያለው ደካማ ሕግ ጥቃት የፈጸሙ ወንጀለኞች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ተጎጂዎችም ድጋፍ አያገኙም” ይላል የተመድ ሪፖርት።

በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች በሶማሌ ሕብረተሰብ ውስጥ በጣም ተጋላጭ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ፤ ሥቸው እንደ ነውር የሚታይ ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታም የተገለሉ ናቸው።

“በሶማሊያ እንደ እኛ ያሉ ሴቶች ምንም አይነት ድጋፍ የላቸውም። የትኛውንም አካል ልንጠይቅ አንችልም። ሕብረተሰቡ የሚያደርግብን ጫና ሁሉንም ነገር ያባብሰበዋል። ለዚያም ነው ተጋላጭ የሆኑት በርካታ ሴቶች እርዳታን የማይሹት፣ በተለይም የሱስ ችግር ያለባቸው” ስትል ፊርዶሳ አክላለች።

በሶማሊያ ውስጥ ብዙ የሴቶች ድርጅቶች ቢኖሩም ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠይቃቸውም ፈቃደኞች አልሆኑም።

ሆዳን እና ፊርዶሳ አጽንጾት ሰጥተው የሚናገሩት ጉዳይ፣ እነሱን የሚደግፏቸው መዋቅሮች ተዘርግተው ቢሆን ኖሮ ወደዚህ አደገኛ ሥራ እንደማይገቡ ነው። በዚህም ሁኔታ በርካቶቹ ለጥቃት እና ለብዝበዛ በተጋለጠ ሁኔታ ለመኖር ተገደዋል።

“በርካታ ታዳጊዎች ከሱስ ጋር እየታገሉ ነው፤ ይህም የበለጠ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። ብዙዎቹ በምሽት የሚያድሩበት ቤት እንኳን የላቸውም” ትላለች ፊርዶሳ።

“እነዚህ ሴቶች የሚያድሩበት ቤትም ስለሌላቸው በሊዶ የባሕር ዳርቻ አካባቢ እና በሌሎች የከተማዋ ክፍሎች ጎዳናዎች ላይ መተኛት ጀምረዋል። ሌሎች ደግሞ መኝታ ለማግኘት ሲሉ ከወንዶች ጋር ይሄዳሉ። በዚህም ሁኔታ ለበለጠ የወሲብ ብዝበዛ ይጋለጣሉ” ብለዋል።

ቢቢሲ ፊርዶሳን በሚያናግርበት ወቅት ከኋላዋ አንድ ህፃን ልጅ የያዘች ሴት ተቀምጣለች። ግለሰቧ አሚና የምትባል ሲሆን፣ ቀድሞም በወሲብ ንግድ ትተዳደር የነበረች ናት። ካረገዘች በኋላም ሥራውን ማቆሟን ትናገራለች።

“አሚና ከዚህ ሕይወት እንድወጣና ወደ ቤት እንድመለስ ሁልጊዜ ትነግረኛለች። ነገር ግን ያን ያህል ቀላል አይደለም። የምትወዷቸውን ሰዎች መጋፈጥ ከባድ ነው። ለሦስት ዓመታት ቤተሰቤን አላየሁም” ብላለች ፊርዶሳ።