የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ‘ብቁ አይደሉም’ የተባሉትን ከፍተኛ ጀነራል አባረሩ

ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ‘ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል’ እንዲሁም ‘ብቃት የላቸውም’ በሚል ትችት የቀረበባቸውን የጦራቸውን ከፍተኛ ጀነራል ከሥራ አባረሩ።

ሌተናንት ጀነራል ዩሪይ ሶዶል ለዩክሬን ጥምር ኃይል አዛዥ ሆነው ከአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ጀምሮ እያገለገሉ ነበር።

አሁን ላይ በምትካቸው ብርጋዲየር ጀነራል አንድሪይ ህናቶቭ ተሹመዋል።

ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ውሳኔውን ባሳወቁበት የሰኞ ምሽት የቪዲዮ መልዕክታቸው ላይ ጀነራሉን ለማባረር ውሳኔ ላይ ያስደረሳቸውን ምክንያት አልገለጹም።

ሆኖም ከእርሳቸው ንግግር ከሰዓታት በፊት የአዞቭ ብርጌድ ኢታማዦር ሹም ሜጀር ጀነራል ቦህዳን ክሮቴቪች ፣ጀነራል ሶዶል ከሩሲያ ጀነራሎች በላይ በርካታ የዩክሬን ወታደሮች እንዲገደሉ አድርገዋል በሚል የቀረቡ ቅሬታዎችን ለምርመራ ቢሮ (ኤስቢአይ) አቅርበው ነበር።

ክሮቴቪች በቴሌግራም ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም ጀነራል ሶዶል ዩክሬን ግዛቶቿን ለማጣቷ እና በሺዎች ለሚቆጠሩ ወታደሮች ሞት ተጠያቂ ቢሆኑም ምርመራ አልተካሄደባቸውም ብለዋል።

“አንዳንዴ አንድ እንድንሆን ነው መሰል ዓለም እኛኑ የሚዋጋ አካል የሚልክብን ይመስለኛል።መላው ጦሩ ስለ ማን እንደማወራ ይገባዋል፤ምክንያቱም 99 በመቶ የሚሆነው የጦሩ ክፍል ጀነራሉን በሰሩት ሥራ ይጠላቸዋል።” ብለዋል።

ክሮቴቪች በቴሌግራም ያጋሩት ጽሑፍ ከ800 ሺህ በላይ ጊዜ ታይቷል።ከዚያም በኋላ ላይ ጀነራል ህናቶቭ በመተካታቸው “ይገባቸዋል” ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

እአአ የካቲት 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ሰፊ ወረራ ተከትሎ ጀነራል ሶዶል፣ ማሪዮፖል ከተማን ለመከላከል በተደረገው እና በምሥራቃዊ የዩክሬን ከተማ ቮልኖቫኻ አቅራቢያ በነበረው ውጊያ ላይ ተሳትፈዋል።አሁን ላይ ሁለቱም ቦታዎች በሩሲያ እጅ ይገኛሉ።

ጀነራል ሶዶል ከየካቲት 2024 ጀምሮ የጥምር ጦሩ አዛዥ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

የሩሲያ ኃይሎች በምሥራቃዊ ዩክሬን ክፍል ግስጋሴ እያሳዩ ባሉበት ወቅት በዩክሬን ጦር ውስጥ ሹም ሽሮች እየተካሄዱ ሲሆን ከ2024 መጀመሪያ አንስቶ በቂ ኃይል የሌለው የኪዬቭ ጦር ይዞታውን ጠብቆ ለመቆየት እየታገለ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ኃይሎችም በሩሲያ ግዛት ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው።

ኪዬቭ በሩሲያ የኃይል ማመንጫ ላይ በርካታ ጥቃቶችን የፈፀመች ሲሆን ይህም የሞስኮን ጦር አስቆጥቷል።

ሞስኮ እሑድ ዕለት በክሬሚያ ለተፈፀመው የሚሳኤል ጥቃት ዩክሬንን ተጠያቂ አድርጋለች።በዚህ ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን እና ከ100 በላይ መቁሰላቸውን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።