ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መነኮሳት የወሲብ ቪዲዮ መመልከታቸው አግባብ አይደለም ሲሉ የሮማው ሊቀ ጳጳስ ተናገሩ
የሮማው የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የወሲብ ቪዲዮ ለሚመለከቱ መነኮሳት እና ቄሶች ''የቅስና ልባችሁን ያደክማል'' ሲሉ የማስጠንቀቂያ መልክት አስተላለፉ።
የ86 ዓመቱ ሊቀ ጳጳስ በቫቲካን በነበራቸው ጉባኤ የማሕበራዊ ሚዲያ እና የዲጂታሉ አለም እንዴት ለተሻለ ጥቅም ይዋል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት።
"የወሲብ ቪዲዮዎችን መመልከት በርካቶች የሚፈጽሙት ሃጥያት ነው፤ መነኮሳት እና ቄሶችን ጨምሮ" ሲሉም ጳጳሱ ተናግረዋል።
አክለውም ''ሰይጣን በዚያ አድርጎ ይገባል'' ሲሉም ፖፕ ፍራንሲስ ለቄሶች እና ቅስና ተማሪዎች ተናግረዋል።
የዲጂታሉን አለም እና የማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም አስፈላጊ ቢሆንም አብዛኛውን ግዜያቸውን በዛ እንዳያጠፉ መክረዋል።
''ያ ንጹህ ልብ፣ ያ ክርስቶስ በየዕለቱ የሚቀበለው ልብ የወሲብ ቪዲዮዎች የሚያስተላልፉትን መረጃ መቀበል አይችልም'' ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
''ይህንን ከስልካችሁ ላይ አጥፉ። ይህም እንዳትፈተኑ ያደርጋችኋል'' ሲሉም ፖፕ ፍራንሲስ ተናግረዋል።
ቤተ ክርስቲያኒቱ የወሲብ ቪዲዮዎችን መመልከት በቅድስና ላይ የሚፈጸም ጥፋት አድርጋ ትመለከተዋለች።