ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ ድንበሯን የተሻገረ አንድ የአሜሪካ ወታደርን በቁጥጥር ስር ማዋሏ ተገለጸ
ከምዕራባውያን ጋር ፍጥጫ ውስጥ ያለችው ሰሜን ኮሪያ ያለ ፍቃዷ ድንበሯን የተሻገረ አሜሪካዊ ወታደር በቁጥጥር ሥር ማዋሏ ተዘገበ።
የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ግለሰቡ ፍቃድ ሳይኖረው ወደ ሰሜን ኮሪያ ተሻግሯል ሲል የወታደር አባሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አረጋግጧል።
ፔንታጎን ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኮሪያ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ እምነቱ መሆኑን ገልጾ፣ ግለሰቡን ለማስቀለለቅ ከሰሜን ኮሪያ ጦር ጋር ንግግር እያደረኩ ነው ብሏል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሰሜን ኮሪያ የተሻገረው ወታደር ትራቪስ ኪንግ እንደሚባል የዘገቡ ሲሆን፣ ግለሰቡ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበትን ድንበር በፍቃዱ ተሻግሮ ከዓለም ወደተነጠለችው አገር ለመግባት ለምን እንደፈለገ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ይሁን እንጂ ይህ ወታደር በሥነ-ምግባር ጥሰት ምክንያት ወደ አሜሪካ እንዲመለስ እንደታዘዘ እና የዐይን እማኞች ድንበሩን ሲያቋርጥ እየሳቀ ነበር ማለታቸው ምናልባትም ትራቪስ ኪንግ ከአሜሪካ ሽሽት በሰሜን ኮሪያ ጥገኝነት ለመጠየቅ ድንበር ተሻግሯል የሚሉ መላ ምቶች እየተሰጡ ነው።
የአሜሪካ ዜጎች ከምዕራባውያን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደሌላት ሰሜን ኮሪያ ድንበር አቅራቢያ እንዳይጓዙ ይመከራሉ።
ይህ የአሜሪካ ጦር አባል የሰሜን ኮሪያን ድንበር የተሻገረው ከሌሎች ጎብኚዎች ጋር በመሆን፣ ደቡብ እና ሰሜን ኮሪያን የሚለየውን ድንበር እየጎበኘ ሳለ ነበር።
አንድ በስም ያልተጠቀሱ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሲቢኤስ ቴሌቪዥን ሲናገሩ፣ ወታደሩ ወደ አሜሪካ ለመመለስ የአየር ማረፊያ ፍተሻን ካለፈ በኋላ ግልጽ ባልሆነ መንገድ የቡድን ጉብኝቱን ተቀላቅሏል ብለዋል።
ይህንን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት የተሰማራባት ቦታን የሚያስተዳድረው የተባበሩት መንግሥታት አካል፣ ግለሰቡ ደንበር ለመሻገር የሚያስችለው ፍቃድ እንደሌለው ገልጾ ወታደሩን ለማስፈታት ከሰሜን ኮሪያ ጦር ጋር ድርድር መጀመሩን ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር።
“በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኮሪያ በእስር ላይ እንዳለ እናምናለን። ከሰሜን ኮሪያ ጦር አቻዎቻችን ጋር ለክስተቱ መፍትሄ ለመስጠት እየሠራን ነው” ብሏል።
ሰሜን እና ደቡብ ኮሪያን የሚለየው ድንበር በተቀበረ ፈንጅ የተሞላ፣ በአደገኛ የኤሌክትሪክ አጥር የታጠረ፣ በካሜራ ጠንካራ ክትትል የሚደረግበት፣ 24 ሰዓታት በንቃት በሚጠብቁ ወታደሮች የተከበበ ነው።
ሁለቱ ኮሪያዎች በ1950ዎቹ በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት ምክንያት በሰሜን እና በደቡብ ተከፍለው ቀርተዋል።
ከምዕራባውያን ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ደቡብ ኮሪያ በቴክኖሎጂ እና በዴሞክራሲ እንዲሁም በምጣኔ ሃብት እጅግ የበለጸገች አገር ስትሆን፣ በአንጻሩ ሰሜን ኮሪያ በአምባገነን ወታደራዊ አገዛዝ የምትመራ ዜጎቿ ለረሃብ የሚጋለጡባት አገር እንደሆነች ይነገራል።
እነዚህ ሁለት አገራት ቀጥተኛ ጦርነት ላይ ባይሆኑም አሁንም ድረስ ግን ጦርነት ውስጥ እንዳሉ ተደርጎ ይቆጠራል።
ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ በሚደረግበት ድንበር በኩል ሰሜን ኮሪያውያንን ወደ ደቡብ ኮሪያ ለማሻገር ጥረት ቢያደርጉም የሚሳካላቸው ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።
በቅርቡ በዚህ የደንበር አካባቢ በተሳካ ሁኔታ ከሰሜን ኮሪያ አምልጦ ደቡብ ኮሪያ መግባት የቻለው ሰሜን ኮሪያዊ እአአ 2017 ላይ ነበር።
እንደ ደቡብ ኮሪያ መንግሥት መረጃ ከሆነ ግለሰቡ ቅድሚያ በመኪና በፍጥነት ወደ ድንበር ከተጓዘ በኋላ ከዚያ በእግሩ ሮጦ ደቡብ ኮሪያ መግባት ችሏል። ግለሰቡ 40 ጊዜ ቢተኮስበትም መትረፍ ችሏል።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት እንደሚለው በየዓመቱ ከ1ሺህ የማያንሱ የሰሜን ኮሪያ ዜጎች ወደ ቻይና ይሻገራሉ።
ዛሬ ወደ ሰሜን ኮሪያ ከገባው አሜሪካዊ ውጪ በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኮሪያ በእስር ላይ የሚገኝ አሜሪካዊ የለም።
እአአ 2017 ላይ የፕሮፖጋንዳ ምልክት ሰርቋል ተብሎ ከታሰረ በኋላ ወደ አሜሪካ እንዲመለስ ተደርጎ ሕይወቱ ያለፈው አሜሪካዊ ጉዳይ የሁለቱን አገራት ግንኙነት እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶት ነበር።
በዶናልድት ትራምፕ አስተዳደር ወቅት ሦስት አሜሪካውያን ከሰሜን ኮሪያ እስር ቤቶች ነጻ ከወጡ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል የተሻለ ግንኙነት መፍጠር ተችሎ ነበር።