ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይናንስ፡ የዓለማችን ግዙፉ ክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ኃላፊ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ጥፋተኛ ነኝ አሉ
የባይናንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቻንግፔንግ ዣዎ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ማስመለስ በሚል በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኝነታቸውን አምነው ከሥልጣናቸው ተነሱ።
“ስህተት ፈፅሚያለሁ፤ ኃላፊነትም ልወስድ ይገባኛል። ይህ ለባይናንስ፣ ለራሴም ይሁን ለመላው ማሕበረሰብ ትክክለኛው እርምጃ ነው” ኢሰሉ ኤክስ ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዓለማችን ትልቁ የክሪፕቶከረንሲ መለዋወጫ የሆነው ባይንስ ለፈፀመው ወንጀል 4.3 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል የአሜሪካው ፍትሕ ቢሮ ጠይቋል።
ፍትሕ ቢሮ እንደሚለው ባይናንስ በመላው ዓለም ያሉ ተጠቃሚዎች በሕገ-ወጥ መልኩ ገንዘብ እንዲያስተላልፉ አስችሏል።
“ባይናንስ በአሜሪካዊያን እና በኢራናዊያን ተጠቃሚዎች መካከል ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንዲዘዋወር አድርጓል። በአሜሪካዊያን እና ሶሪያዊያን፣ በሩሲያ በተያዙት የዩክሬን ክሬሚያ፣ ዶኔትስክ እና ሉሃንስክ ግዛቶችም እንዲሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲዘዋወር አስችሏል።”
በኬይሜን ደሴቶች ተመዝግቦ የሚንቀሳቀሰው ባይናንስ የተለያዩ ክሪፕቶከረንሲዎችን እንዲሁም ዲጂታል ሃብቶችን ለመግዛትና ለመሸጥ ሰዎች የሚጠቀሙበት የዓለማችን ትልቁ መድረክ ነው።
የአሜሪካ የፍትሕ ቢሮ አክሎ እንደሚለው በርካታ ወንጀለኞችና አሸባሪዎች ባይናንስን ተጠቅመው ገንዘብ አስተላልፈዋል።
በአውሮፓውያኑ "በ2017 እና 2022 መካከል ሂድራ የተባለው ድርጅት 106 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን ወደ ባይናንስ ኮሮጆ አስገብቷል” ይላል የአሜሪካ የፍትሕ ቢሮ።
“ሂድራ ታዋቂ የሩሲያ የጨለማው መረብ [ዳርክኔት] መገበያያ ሥፍራ ነው። ወንጀለኞች ሕጋዊ ያልሆኑ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚጠቀሙበት ነው።”
ከዚህ በኋላ ባይናንስ አጠራጣሪ የሆኑ ዝውውሮችን ሲመለከት ለፌዴራል ባለሥልጣናት ማሳወቅ አለበት።
“ይህ ሂደት እንደ ሐማስ ያሉ ቡድኖች በክሪፕቶከረንሲ ገንዘብ እንደያዘዋውሩ ለማድረግና የወንጀል ምርመራችንን ለማቀላጠፍ ይረዳናል” ይላል ፍትሕ ቢሮው።
የኩባንያው ቀጣናዊ ገበያ ኃላፊ የነበሩት ሪቻርድ ቴንግ አዲሱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተቀጥረዋል።
መንበራቸውን የለቀቁት ቻንግፔንግ በክሪፕቶ ዓለም እጅግ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ ናቸው።
ባለፈው መጋቢት የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች ባይናንስ በሃገሪቱ በሕገ-ወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ስለሆነ እንዲታገድ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
ኩባንያው በርካታ የአሜሪካ የፋይናንስ ሕግጋትን ጥሷል፤ የሕገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ሂደቱን ለመደበቅ ሞክራል ሲሉ ወቅሰዋል።
ኩባንያው በወቅቱ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲል ወቀሳውን አስተባብሎ ነበር።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት የተለያዩ ሕግጋትን ተጠቅመው በክሪፕቶ ኢንደስትሪ ውስጥ የሚከናወኑ ሕጋዊ ያልሆኑ ዝውውሮችን ለመግታት ቃል ገብተዋል።
የባይናንስ ተቀናቃኝ የነበረው ኤፍቲኤክስ የተባለው ድርጅት በሕገ-ወጥ ዝውውር ተከሶ ከገበያ ውጭ ከሆነ በኋላ ነው ምርመራዎች የተጠናከሩት።
በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር መባቻ የኤፍቲኤክስ መሥራች የነበረው ሳም ባንክማን-ፍራይድ በማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።