የኢላን መስክ ኤክስ ፀረ-ሴማዊ ነው ሲል የወቀሰው ድርጅት ላይ ክስ መሠረተ

ኢላን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢላን መስክ ማሕበራዊ ሚድያ የሆነው ኤክስ ፀረ-ሴማዊ መልዕክቶች ከማስታወቂያዎች ጋር እንዲሄዱ አድርጓል ያለውን አንድ ግራ-ዘመም ድርጅት ከሷል።

የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ባቀረበው ክስ ‘ሚድያ ማተርስ ፎር አሜሪካ’ የተባለው ድርጅት “ሊያጠፋኝ” ተነስቷል ብሏል።

ግራ-ዘመሙ ድርጅት ጥናቱን ይፋ ካደረገ በኋላ እንደ አፕል፣ ዲዝኒ፣ አይቢኤም እና ኮምካስት ያሉ ግዙፍ ድርጅቶች ኤክስ ላይ ማስታወቂያ መለጠፍ አቁመዋል።

ኢላን መስክ ይህን ድርጅት እከሳለሁ ማለቱን ተከትሎ ሚድያ ማተርስ ሰውየው “የጉልበተኛ” ባሕሪ ማሳየት ይወዳል ብሏል።

ይህ የንቅናቄ ሥራ ላይ የተሰማራ ድርጅት እንደሚለው ኤክስ ላይ ከሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ጎን ለጎን ናዚን የሚደግፉ፤ ለምሳሌ የሂትለር ንግግሮች እና ሆሎኮስትን የሚክዱ መልዕክቶች ተለጥፈዋል።

አልፎም ባለፈው ሳምንት ኢላን መስክ ራሱ ፀረ-ሴማዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶችን አስተላልፏል ሲል ወቅሷል።

ኤክስ ሰኞ ዕለት ነው ቴክሳስ ውስጥ ክሱን ያቀረበው።

“ሚድያ ማተርስ እያወቀና በክፉ መንፈስ ተነሳስቶ ኤክስ ላይ የተለጠፉ ማስታወቂያዎች ጎን ለጎን የናዚና የነጭ የበላይነት አቀንቃኝ የሆኒኑ ምስሎችን በመደባለቅ ሰዎች ማሕበራዊ ሚድያ ላይ ሁሌም የሚገጥማቸው ይህ እንደሆነ ለማስመሰል ሞክሯል” ይላል ክሱ።

“ሚድያ ማተርስ እኒህን ምስሎች ያሰራጨው ሆነ ብሎ ማስታወቂያ የሚለጥፉ ሰዎች ከኤክስ እንዲርቁና ኮርፖሬሽኑ እንዲወድም በማሰብ ነው።”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤክስ ክስ እንደሚያመለክተው ኮምካስት፣ ኦራክል እና አይቢኤም የሰሯቸው ማስታወቂያዎች ሥር የጥላቻ መልዕክት የተላለፈው ለሚድያ ማተርስ እንጂ ለሌሎች ተጠቃሚዎች አይደለም።

የኤክስ ዋን ሥራ አስኪያጅ ሊንዳ ያካሪኖ “እውነታው ይህ ነው። የትኛውም ንፁሕ የኤክስ ተጠቃሚ ከአይቢኤም፣ ኮምካስት አሊያም አራክል ማስታወቂያ ሥር መሰል መልዕክቶች አልተመለከተም” ብለዋል።

ሚድያ ማተርስ ጥናቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን፣ ዋርነር ብሮስ ዲስከቨሪ፣ ፓራማውንት እና ላየንስጌት የተባሉ ተቋማትም ኤክስ ላይ ማስታወቂያ ማስተላለፋቸውን ገታ አድርገዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ኢላን መስክ ሚድያ ማተርስን እንደሚከስ ይፋ አድርጎ “በኩባንያችን ላይ ረብ የለሽ ወቀሳ ላይ ያቀረበ አይቀርለትም” ብሏል።

ለዚህ ምላሽ የሰጡት የሚድያ ማተርስ ፕሬዝደንት አንጀሎ ካሩሶን ድርጅታችን የትኛውንም ክስ ለመርታት ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 2004 የተቋቋመው ሚድያ ማተርስ ጽንፈኛ ሐሳብ ሰጪዎችንና ሚድያዎችን በመተቸት ይታወቃል።

ራሱን ለትርፍ ያልተቋቋመ “ተራማጅ የጥናትና መረጃ ማዕከል” ብሎ የሚጠራው ይህ ድርጅት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሕዝቡን በተሳሳተ መረጃ እንዳያደናግሩ እሠራለሁ ይላል።

ባለፈው ረቡዕ ኢላን መስክ ከአንድ “የአይሁድ ማሕበረሰብ ነጮች እንዲጠሉ እያደረገ ነው” ከሚል የሤራ ትንታኑ ሥር “ይሄማ እውነት ነው” የሚል ‘ኮሜንት’ ሰጥቷል።

ይህ ተከትሎ በርካቶች የኤክስን ባለቤት ሲያብጠለጥሉት ከርመዋል።

ቢሊየነሩ የቴስላ እና ስፔስኤክስ ፈጣሪ ቆይቶ ፀረ-ሴማዊ መልዕክት አለማስተላለፉን ገልጦ የሰጠው አስተያየት ሁሉንም አይሁዳውያን ሳይሆን የተወሰኑ ቡድኖች የሚመለከት እንደሆነ ተናግሯል።

በተያያዘ ዜና ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የኤክስ ተቀናቃኝ ሆኖ የመጣው የሜታውን ትሬድስ እንደሚቀላቀሉ ዋይት ሐውስ ገልጧል።

ፕሬዝደንት ባይደን ብቻ ሳይሆኑ ቀዳማዊ እመቤቷ፣ ምክትል ፕሬዝደንቷ እና ባለቤቷ ትሬድን ይቀላቀላሉ።