ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሕንድ የልጅነት ጓደኛሞች 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ አልማዝ አገኙ
በማዕከላዊ ሕንድ የማዕድን ከተማ በምትባለው ፓና ሁለት የልጅነት ጓደኛሞች ሕይወታቸውን ሊቀይር የሚችል የከበረ ድንጋይ አግኝተዋል።
ሳቲሽ ኻቲክ እና ሳጂድ ሞሐመድ የተከራዩት መሬት ላይ ግዙፍ የሚያብረቀርቅ ድንጋይ ሲመለከቱ ዓይናቸውን ማመን አልቻሉም።
ድንጋዩን ይዘው ወደ ከተማ ማዕከል ሲገቡ የያዙት 15.34 ካራት የሚመዝን ጥራቱ ላቅ ያለ አልማዝ መሆኑን ተረዱ።
"የአልማዙ የዋጋ ግምት ከአምስት እስከ ስድስት ሚሊዮን ሩጲ (ከ55 ሺህ እስከ 60 ሺህ ዶላር) ይሆናል። በቅርቡ ለጨረታ ይወጣል" ሲሉ የአልማዝ ዋጋ አውጪ የሆኑት አኑፓም ሲንግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአልማዙ ዋጋ አሁን ባለው የምንዛሪ ገበያ ወደ ብር ሲመነዘር 8.5 ሚሊዮን ገደማ ይሆናል።
በአካባቢው መንግሥት የሚያዘጋጀው በየሩብ ዓመቱ የሚካሄድ ጨረታ አለ።
ይህ ጨረታ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም ከውጭ የሚመጡ ገዢዎችን ከሻጮች ያገናኛል።
ኻቲክ እና ሞሐመድ ደስታቸው ወደር እንዴለለው ይናገራሉ። "አሁን እህቶቻችንን መዳር እንችላለን።"
የ24 ዓመቱ ኻቲክ አነስተኛ ሉካንዳ አለው። የ23 ዓመቱ ሞሐመድ ደግሞ ፍራፍሬ ሸጦ የሚተዳደር ሲሆን ሁለቱም ከድኃ ቤተሰብ የተገኙ የመጨረሻ ልጆች ናቸው።
ለዘመናት ወላጆቻቸው አልማዝ አግኝተው ሕይወታቸውን ለመቀየር ሲሞክሩ ቆይተዋል።
ይህ የፓና መንደር ነዋሪዎች ዕጣ ፈንታ ነው። አልማዝ ቆፍሮ አውጥቶ ሕይወትን መቀየር።
መንደሯ በሕንድ ካሉ ዕድገት ከራቃቸው አካባቢዎች አንዷ ስትሆን ነዋሪዎች በድኅነት የላሸቁ፣ የመጠጥ ውሀ እጥረት ያለባቸው እና ሥራ አጥነት የሚያጠቃቸው ናቸው።
ቢሆንም መንደሯ በሕንድ በርካታ አልማዝ የሚገኝባት በመሆኗ ይህን የከበረ ድንጋይ የሚያድኑ ሰዎች ያንዣብቧታል።
ሕንድ በዓለማችን ካሉ በርካታ የአልማዝ ክምችት ካለባቸው ሀገራት ተርታ ባትሰለፍም የሀገሪቱ አልማዝ ተፈላጊ ከሚባሉት መካከል ነው።
አብዛኛው የማዕድን ማውጣት ሥራ የሚከናወነው በመንግሥት ቢሆንም የአካባቢው ባለሥልጣናት ለነዋሪዎች በአነስተኛ ዋጋ መሬት ያከራያሉ።
በርካቶች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው መሬት ተከራይተው አልማዝ ያስሳሉ። የሚሳካላቸው ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።
ሞሐመድ እንደሚለው አባቱ እና አያቱ ይህን መሬት ለዘመናት ቢቆፍሩም ከአባሯና ጭቃ የተለየ ያተረፉት ነገር የለም።
አባቱ ናፊስ "አማልክት በስተመጨረሻም የዘመናት ድካማችንን እና ሥራችንን ከፈሉን" ይላሉ።
የልጅነት ጓደኛሞቹ መሬት ተከራይተው አልማዝ ለመፈለግ የወሰኑት ከሥራቸው የሚያገኙት ገቢ ተጣምሮ እንኳ ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ በቂ ባለመሆኑ እንደሆነ ሞሐመድ ለቢቢሲ ይናገራል።
አልማዝ መፈለግ ቀላል ሥራ ባይሆንም ጓደኛሞቹ ከቀን ሥራቸው በተረፈው ጊዜ ነበር ይህን ያደርጉ የነበረው።