የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ጨዋታዎች ግምት፡ ዩናይትድ ከኒውካስል፤ አርሰናል ከብራይተን

ማቲያስ ኩኛ እና ብሩኖ ጉማሬዥ

አርሰናል የሊጉ አናት ላይ ሆኖ የፈረንጆቹን ገና አክብሯል። መድፈኞቹ በያዝነው የውድድር ዓመት የናፈቁትን ዋንጫ ያገኙ ይሆን?

ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ የአርሰናልን ዱካ መከተል ይዟል። ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲቲ ከአርሰናል ያለው የነጥብ ልዩነት ሁለት ነው።

ባለፈው ሳምንት ማንቸስተር ዩናይትድን የረታው አስተን ቪላ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

18ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች አርብ፣ ቅዳሜ እና እሑድ ይከናወናሉ። የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን የሊጉን ጨዋታዎች ግምቶች እንዲህ አስቀምጧል።

አርብ
የማንቸስተር ዩናይትድ እና ኒውካስል አርማ

ማንቸስተር ዩናይትድ ከኒውካስል

ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት በቪላ ቢረታም ተጫዋቾቹ ያሳዩት ብቃት አድናቆት ተችሮታል።

አሁን ለዩናይትድ ትልቁ ጥያቄ በጉዳት ከሜዳ ከራቀው ብሩኖ ፈርናንዴዝ ውጭ እንዴት መጫወት ይችላሉ የሚለው ነው።

የሩበን አሞሪም ቡድንን ሲመለከቱ ከብሩኖ ውጭ መሪ ሊሆን የሚችል ተጫዋች መኖሩ ያጠራጥራል።

ተከላካዩ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ የተከላካይ አማካይ ሆኖ ይጫወት ይሆን? ምክንያቱም ተጫዋቹ የመሪነት ብቃት ያለው ነው።

ኒውካስል ዩናይትድ ከቼልሲ ጋር በነበራቸው ጨዋታ የሁለት ጎል መሪነት ቢይዙም የኋላ ኋላ አቻ ተለያይተዋል። ከሜዳ ውጭ ያላቸው አቋም ደግሞ በጣም ደካማ የሚባል ነው።

ዩናይትድ አምበሉ ብሩኖን በጉዳት ሌሎች ወሳኝ የሚባሉ ተጫዋቾችን ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት አጥቷል። ኒውካስል ዩናይትድ የተሻለ ቡድን ይዞ ይመጣል።

በዚህ ምክንያት የኤዲ ሀው ቡድን እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ግምት፡ 0 - 1

ቅዳሜ

ኖቲንግሀም ፎረስት ከማንቸስተር ሲቲ

ኖቲንግሀም አሁንም ከወራጅ ቀጣናው አካባቢ አልራቁም። ባለፈው ሰኞ በፉልሀም መሸነፋቸው ደግሞ ሁኔታውን ከባድ አድርጎባቸዋል።

ይህ ጨዋታ ለሲቲ ቀላል የሚባል ባይሆንም አሁን ያላቸው አቋም ግን አስደናቂ ነው።

የውድድር ዘመኑ እየገፋ ሲመጣ ሲቲ የበለጠ እየተሻሻለ ነው። ራያን ቼርኪ እና ፊል ፎደን ብቃታቸው እየጎመራ ነው። ለኧርሊንግ ሀላንድ የሚያቀብሏቸው ኳሶች የሚደነቁ ናቸው። በሌላ በኩል ግብ እየተቆጠረባቸው አይደለም።

ግምት፡ 0 - 2

የአርሰናል እና ብራይተን አርማ

አርሰናል ከብራይተን

ሰዎች አርሰናል እየተንገዳገደ ነው ይላሉ። ነገር ግን እኔ ከዎልቭስ ጨዋታ በኋላ መንገዳገድ አላየሁም።

ከኤቨርተን ጋር ያደረጉትን ጨዋታ 1-0 ቢያጠናቅቁም የዴቪድ ሞየስ ቡድን ፈታኝ መሆኑ ግልፅ ነው።

ከብራይተን ጋር የሚያደርጉትም ጨዋታ ቀላል ይሆናል ብዬ አልገምትም። ነገር ግን ጨዋታውን እንደሚያሸንፉ እምነት አለኝ።

ብራይተን ለመገመት እጅግ ከባድ ከሆኑ ክለቦች መካከል ናቸው። ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንዱንም ባያሸንፉም ሊቨርፑልን እንዴት እንደፈተኑት ተመልክቻለሁ።

ከአርሰናል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም ተመሳሳይ እንደሚሆን እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 0

ብሬንትፈርድ ከቦርንመዝ

በሜዳቸው ጠንካራ የሆኑት ብሬንትፈርድ ከሜዳቸው ውጭ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ባለፈው ሳምንት አስመዝግበዋል።

ይህ ጨዋታ ብዙ ግቦች የምናይበት ይመስለኛል። ምክንያቱም ቦርንመዝ ጎል ቢያስቆጥርም የራሱን ድንበር አያስከብርም።

ቦርንመዝ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ነው ያጠናቀቁት። ይህም ጨዋታ ተመሳሳይ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 2

በርንሊ ከኤቨርተን

የበርንሊ አሠልጣኝ ስኮት ፓርከር ጫና እየበረታበት ይገኛል። ብዙዎች ለቡድኑ ትክክለኛ አሠልጣኝ ስለመሆኑ መጠራጠር ይዘዋል።

ኤቨርተን ወሳኝ የሚባሉ ተጫቾችን ቢያጣም ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ የሚያገኝ ይመስለኛል።

ግምት፡ 1 - 1

የሊቨርፑል እና ዎልቭስ አርማ

ሊቨርፑል ከዎልቭስ

ዕድለኛ ያልሆነው አሌክሳንደር ኢሳክ ሁኔታው ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖበታል። ከኒውካስል ከመጣ በኋላ ብዙ ያልተሳካለት ኤርትራዊ-ስዊድናዊው አጥቂ በጉዳት ምክንያት ለወራት ከሜዳ እንደሚርቅ ተሰምቷል።

ነገር ግን ሊቨርፑል ኡጎ ኤኪቲኬ እያለ የኢሳክ አለመኖር የሚያሳስበው አይመስለኝም።

ሞሐመድ ሳላህ ሀገሩ ግብፅን ወክሎ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ ሞሮኮ አቅንቷል። ዶሚኒክ ስቦዝላይ በቅጣት ምክንያት አይኖርም። ምናልባት ፍሎሪያን ሪትዝ የሚደምቅበት ጨዋታ ይሆናል።

የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ዎልቭስ ከዚህ ጨዋታ የሚያገኙት ነገር ይኖራል ብዬ አልጠብቅም።

ግምት፡ 2 - 0

ዌስት ሀም ከፉልሀም

ዌስት ሀም ከዚህ ጨዋታ 3 ነጥብ ማግኘት አለበት። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ነው ያገኙት።

ኑኖ ኤስፒሪቶ ሳንቶ በኅዳር ወር መጀመሪያ የተሻለ ነገር ቢያሳዩንም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ተመልሰው የቁልቁለት ጉዞ የያዙ ይመስላል።

ፉልሀም ባለፈው ሳምንት የተቀዳጀውን ድል ተከትሎ ከወራጅ ቀጣና ስጋት ወጥቷል።

በዚህኛውም ጨዋታ ፉልሀም ደስታን የሚጎናጸፍ ይመስለኛል።

ግምት፡ 1 - 2

የቼልሲ እና ቪላ አርማ

ቼልሲ ከአስተን ቪላ

ቪላ 10 ጨዋታዎችን አከታትለው ማሸነፍ ችለዋል። አርሰናል፣ ሲቲ እና ዩናይትድን በሜዳቸው ረትተዋል። ሞርጋን ሮጀርስ ድንቅ ብቃቱን እያሳየን ነው። የዋንጫ ተፎካካሪ የሚል የክብር ልንሰጣቸውም ይገባል።

ነገር ግን ቼልሲም አንድ ሰሞን ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የዋንጫ ተፎካካሪ ብለነው ነበር።

የሁለቱንም ክለቦች ደጋፊዎች አውቃቸዋለሁ። ምክንያቱም ለሁለቱም ክለቦች ተጫውቻለሁ። በዚህ ጨዋታ መጨረሻ የሚጨፍሩት ግን የቼልሲ ደጋፊዎች ናቸው።

ግምት፡ 2 - 1

እሑድ

ሰንደርላንድ ከሊድስ ዩናይትድ

ሊድስ በቅርብ ሳምንታት አስደናቂ የሚባሉ ውጤቶች ያስመዘግቡ ይዘዋል።

ሰንደርላንድ በርካታ ተጫዋቾች በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት አጥቷል። ነገር ግን ይህ ብዙም አያሳስባቸውም። ጥቋቁር ድመቶቹ ብዙ ግብ አያስቆጥሩም። ነገር ግን ጎላቸውን በመጠበቅ የሚታሙ አይደሉም።

ግምት፡ 1 - 0

ክሪስታል ፓላስ ከቶተንሀም

ሁለቱም ክለቦች በአሁኑ ወቅት የውጤት መዋዠቅ ላይ ናቸው።

ክሪስታል ፓላስ በጨዋታ መደራረብ ምክንያት ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው ቡድን ሆኗል።

በዚህ ምክንያት ቶተንሀም ከዚህ ጨዋታ የሆነ ነገር ያገኛል የሚል ግምት አለኝ። አልፎም ከአልሠጣኝ ቶማስ ፍራንክ ይህ ውጤት ያስፈልጋቸዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ደካማ አቋም ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ ግምቴ አቻ ይወጣሉ የሚል ነው።

ግምት፡ 0 - 0