ቀነኒሳ በቀለ፣ ኬንያዊው ኪፕቾጌ እና ሆላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን ይደምቁበታል ተብሎ የሚጠበቀው የኒውዮርክ ማራቶን

ኬንያዊ ኢሉድ ኪፕቾጌ፣ ሆላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን እና ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ
የምስሉ መግለጫ, ኬንያዊ ኢሉድ ኪፕቾጌ፣ ሆላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን እና ቀነኒሳ በቀለ

ዛሬ እሁድ ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም. በወንዶች ማራቶን ስም ያላቸው የ40 ዓመቱ ኬንያዊ ኢሉድ ኪፕቾጌ እና የ43 ዓመቱ ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ ይወዳደራሉ።

በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ባለው በዚህ ለ55ኛ ጊዜ በሚካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ግምት ተሰጥቷቸዋል።

ዛሬ በሚደረገው የኒው ዮርክ ማራቶን አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ለአሸናፊነት ከኬንያዊው ኢልዩድ ኪፕቾጌ ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ተጠባቂ ነው።

በአትሌቲክስ አፍቃሪው ማኅበረሰብ ዘንድ በጉጉት የሚጠብቀው ሌላው ውድድር ሆላንዳዊቷ ሲፋን ሀሰን የምትሳተፍበት የሴቶች ማራቶን ነው።

በሴቶች ማራቶን የ2022 ኢዩጂን ዓለም ሻምፒዮና አሸናፊዋ ጎተይቶም ገ/ ሥላሴ ትጠበቃለች፡፡ ጎተይቶም በውድድሩ ከሚሳተፉት አትሌቶች የ5ኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት፡፡

2 ሰዓት 18፡11 ደቂቃ የግል ምርጥ ሰዓት ባለቤት የሆነችው ጎተይቶም ገ/ሥላሴ ከኬንያውያን እና ከሌሎች አትሌቶች ጋር ትልቅ ፉክክር እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡

በ2025 የኒውዮርክ ማራቶን የዓለም ሻምፒዮናዎች፣ ክብረ ወሰን ባለቤቶች እና የቀድሞ አሸናፊዎች በጋራ የሚሮጡበት ውድድር ነው።

የኦሎምፒክ አሸናፊዋ ሲፋን ሀሰን በሴቶች ማራቶን ታሸንፋለች ተብሎ ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ትገኛለች።

ሆላንዳዊቷ የማራቶን አትሌት በሲድኒ ርቀቱን 2:18:22 ያጠናቀቀች ሲሆን ባለፈው ዓመት በዚሁ ርቀት 2:13:44 ምርጥ ሰዓቷን ማስመዝገብ ችላለች።

ይህም በኒውዮርክ የሴቶች ማራቶን ላይ ከተሳተፉ ፈጣኗ አትሌት ያደርጋታል።

እአአ በ2003 የቦታውን የርቀት ክብረ ወሰን 2:22:31 በመግባት ማርጋሬት ኦካዮ ያስመዘገበች ሲሆን ይህንን ሲፋን ትሰብረዋለች ተብሎ ተገምቷል።

ይህንን ማድረግ ከቻለች የመጀመርያዋ አውሮፓዊት አትሌት በመሆን ስሟን ከሌሎች ስመ ጥር አትሌቶች ጎን ታስመዘግባለች።

ውድድሩን በድል ለማጠናቀቅ የከተማዋ ድልድዮች እና ዳገቶች መጋፈጥ የሚጠብቃት ሲፋን ሐሰን ያላት ፍጥነት እና ጫናን የመቋቋም ብቃት አሸናፊ ትሆናለች ተብላ እንድትገመት አድርጓታል።

ነገር ግን ከዚህ ቀደም ውድድሩን ያሸነፉ እና የኒውዮርክን ጎዳናዎች ጠንቅቀው የሚያውቁ አትሌቶች አብረዋት ይሰለፋሉ።

ባለፈው ዓመት በውድድሩ የተሳተፈችው እና ድንቅ ብቃቷን ያሳየችው ኬንያዊቷ ሺላ ቼፕኪሩኢ እንዲሁም አእአ በ2023 ያሸነፈችው ሄለን ኦቢሪ በውድድሩ ውስጥ ይሳተፋሉ። እአአ የ2022 ሻምፒዮናዋ ሻሮን ሎኬዲ እንዲሁ በውድድሩ ውስጥ ከሚሳተፉት መካከል ነች።

ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በኒውዮርክ ማራቶን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፉት እአአ በ2011 በጎተይቶም ገ/ሥላሴ ነው።

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ኢሉድ ኪፕቾጌ
የምስሉ መግለጫ, አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ኢሉድ ኪፕቾጌ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ ቀደም ማራቶንን 2:01:09 በመግባት ክብረ ወሰን የያዘው የኦሎምፒክ አሸናፊው ኢሉድ ኪፕቾጌ በኒውዮርክ ውድድር ላይ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ነው።

ቀነኒሳ በቀለ በርቀቱ የዓለማችን ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤት ሲሆን ባለፈው ዓመት በለንደን ማራቶን ርቀቱን ያጠናቀቀው 2:04:15 በሆነ ሰዓት ነው።

ከሁለቱ ስመ ጥር አትሌቶች በተጨማሪ የቦስተን፣ ቺካጎ እና ቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊው ቤንሶን ኪፕሩቶ እንዲሁም የለንደን ማራቶን አሸናፊው አሌክሳንደር ሙቲሶ ሌሎች ጠንካራ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡

ከእድሜያቸው ጋር ተያይዞ ከዘጠኝ ሳምንት በፊት በሲዲኒ ማራቶን የሮጠው ኪፕቾጌ ወይንም በፈረንጆቹ 2025 ምንም ሩጫ ላይ ተሳትፎ የማያውቀው ቀነኒሳ በአሸናፊዎቹ ሰንጠረዥ ላይ ከገቡ አስደናቂ ይሆናል።

43ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ቀነኒሳ በአውሮፓውያኑ 2025 ምንም ዓይነት ውድድር ያላደረገ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተወዳደረበት የለንደን ማራቶን 2ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ አትሌት ቀቀኒሳ በቀለ አገሩን በወከለበት ፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ከኪፕቾጌ ጋር ነበር የሮጠው።

በኒውዮርክ ማራቶን ከሚሮጡ አሜሪካውያን መካከል ባለፈው ዓመት በቫሌንሺያ 2፡06 የገባው ቢያ ሲምባሳ ይገኝበታል።

ኪፕቾጌ እአአ በ2013 በሃምቡርግ ማራቶን የመጀመሪያ ውድድሩን በማራቶን አድርጎ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ በመግባት አሸንፏል።

እአአ በ2022 በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ አንደኛ በመግባት የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን ጨብጧል።

እአአ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ እና እአአ በ2020 በቶሊዮ በተደረጉ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያዎች በማራቶን አግኝቷል።

በኦስትሪያ ቪዬና እ.አ.አ በ2019 በተደረገ ማራቶን 1 ሰዓት ከ59 ደቂቃ ከ40 ሴኮንድ በመሮጥ ከሁለት ሰዓት በታች ማራቶንን የሮጠ የመጀመሪያው አትሌት ቢሆንም፤ የዓለም አትሌቲክስ መስፈርቶችን ያላሟላ ውድድር በመሆኑ ውጤቱ ሳይጸድቅ ቀርቷል።