ዶናልድ ትራምፕ ስማርትስልኮችን እና ኮምፒውተሮችን ከአዲሱ ታሪፍ ነጻ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስማርት ልኮችን፣ ኮምፒውተሮችን እና አንዳንድ የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎችን ቻይና ላይ ከተጣለው 125 በመቶ ታሪፍ ነጻ አደረጉ።
የአሜሪካ ጉምሩክ እና የድንበር ጠባቂ በመግለጫው ላይ እንዳለው የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ትራምፕ በአብዛኛዎቹ አገራት ላይ ከጣሉት የ10 በመቶ ታሪፍ እና በጣም ትልቅ ከሆነው ቻይና ላይ የተጣለው ታሪፍ ላይ አይካተቱም።
ይህ ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሏቸው ታሪፎች ላይ የታየ ትልቅ ለውጥ ሲሆን፣ ውሳኔውን አንድ የምጣኔ ኃብት ተንታኝ "ማርሽ ቀያሪ የሆነ" ሲሉ ገልፀውታል።
ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ወደ ማያሚ ሲጓዙ፣ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ስለ ተነሱት ታሪፎች ተጨማሪ ዝርዝሮችን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ወደ ሚሳፈሩት አውሮፕላን እያመሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "በጣም ቁጥብ እንሆናለን። ነገር ግን ብዙ ገንዘብ እያገኘን ነው። እንደ አገር ብዙ ገንዘብ እያገኘን ነው" ብለዋል
ይህ የፕሬዝዳንቱ ርምጃ የመጣው በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ዋጋ፣ የሚመረቱት ቻይና በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል የሚስ ስጋት ማሳደራቸውን ተከትሎ ነው።
የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች እና መለዋወጫዎቻቸው ከመጋቢት 27 ጀምሮ ከታሪፍ ነጻ እንዲሆኑ ነው የተወሰነው።
በዌድቡሽ ሴኩሪቲስ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ምርምር ኃላፊ የሆኑት ዳን ኢቭስ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ይህ ለቴክኖሎጂ ባለሀብቶች ያልታሰበ ነው" ሲሉ ለጥፈዋል።
"ቻይና ላይ የተጣለውን ታሪፍ ስናይ ስማርትስልኮች እና ቺፕሶች ነጻ እንዲሆኑ መደረጉ ጨዋታ ቀያሪ ለውጥ ነው።"
ይህንን ውሳኔ ተከትሎ እንደ አፕል፣ ኒቪዲ፣ ማይክሮሶፍት እና ሌሎች ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ እፎይታ ይሰማቸዋል ሲሉ አክለዋል።
ኋይት ሀውስ በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ታሪፍ እንዲነሳ የተደረገው ኩባንያዎች የሚያመርቱትን ወደ አሜሪካ ለማዘዋወር በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግ በሚል ነው ብሏል።
የኋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት "ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ እንደ ሰሚኮንዳክተሮች፣ ቺፕስ፣ ስማርት ስልኮች እና ላፕቶፖች ያሉ ወሳኝ ቴክኖሎጂዎችን ለማምረት በቻይና ላይ መተማመን እንደማትችል ግልፅ አድርገዋል" ሲሉ በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል።
"በፕሬዚዳንቱ መመሪያ መሰረት እነዚህ ኩባንያዎች በተቻለ ፍጥነት ምርታቸውን በአገር ውስጥ ለማድረግ እየተጣደፉ ነው።"
ቅዳሜና እሁድን ፍሎሪዳ በሚገኘው ቤታቸው የሚያሳልፉት ዶናልድ ትራምፕ በቻይና ላይ በተጣለው ከፍተኛ ታሪፍ ደስተኛ መሆናቸውን አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማንሳትም "ከዚያም ቢሆን አዎንታዊ ነገር የሚገኝ ይመስለኛል" ብለዋል።
በኋይት ሀውስ ምክትል የጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ስቴፈን ሚለር በኤክስ ገጻቸው ላይ እነዚህ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አሁንም ከፌንታኒል ጋር ተያይዞ በቻይና ላይ የተጣለው 20 በመቶ ታሪፍ ይመለከታቸዋል ብለዋል።
አንዳንድ መላምቶች እንደሚያሳዩት የተጣለው ታሪፍ ወደ ተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚተላለፍ ከሆነ በአሜሪካ ውስጥ የአይፎን ዋጋ በሦስት እጥፍ ሊጨምር ይችላል።
አሜሪካ የአይፎን ትልቁ ገበያ ስትሆን፣ አፕል ባለፈው ዓመት ከነበረው የስማርት ስልኮቹ ሽያጭ ውስጥ ከግማሽ በላይ በአሜሪካ ማካሄዱን ካውንተር ፖይንት የተሰኘ ጥናት አመልክቷል።
ይህ ጥናት በአሜሪካ ለሽያጭ ከቀረቡት የአፕል አይፎኖች 80 በመቶ የሚሆነው በቻይና የተሰራ ሲሆን ቀሪው 20 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በሕንድ የተመረተ ነው ብሏል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልክ እንደ ግዙፉ የስማርትፎን ኩባንያ ሳምሰንግ ሁሉ አፕልም፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን በቻይና ላይ ብቻ ላለማድረግ እየጣረ ነው።
ሕንድ እና ቬትናም ተጨማሪ የማምረቻ ማዕከላት በመሆን በአማራጭነት እያገለገሉ ይገኛሉ።












