ቱርክ የታሰረውን የኤርዶዋን ተቀናቃኝን የኤክስ ገጽ አገደች

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በእስር ላይ የሚገኙት የኢስታንቡል የተቃዋሚ ከንቲባ ኢክሬም ኢማሞግሉ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንት በቱርክ ባለሥልጣናት ታግዷል።

የፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ዋነኛ ተቀናቃኝ የሆነው ኢማሞግሉ ከአሁን በኋላ ለ9.7 ሚሊዮን ተከታዮቻቸው በኤክስ ላይ መልዕክት መላክ አይችሉም። ገጹ አሁንም ከአገር ውጪ እየሠራ ይገኛል።

የማኅበራዊ ድረ-ገጹ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ለመነጋገር እና ከሕዝብ ጋር ለመገናኘት ዋና መሳሪያ ሆኖ ቆይቷል።

ፖለቲከኛው ከእስር ቤትም በጠበቆቻቸው በኩል መልዕክት በመላክ በየቀኑ ይለጥፉ ነበር። "ባለሥልጣናቱ እንዲጠፋ ለማድረግ የፈለጉት ይመስላል" ሲሉ አንድ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል።

በቱርክ ውስጥ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነው የኢማሞግሉ ሪፐብሊካን ፒፕለስ ፓርቲ (ሲኤችፒ) እገዳው "በመጋቢት የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ" ቀጣይ ክፍል መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል ።

የሲኤችፒ ዋና ፀሐፊ ሴሊን ሳይክ ቦክ "አሁን ሕዝቡን እንዲያነጋግር እንኳን አይፈቅዱለትም" ብለዋል። "ይህም በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ሥልጣን እናጣለን የሚለውን ስጋታቸውን በግልጽ ያሳያል። በሚቀጥለው የምርጫ ላይ የተደረገ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ለቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታምቡል ሦስት ጊዜ ከንቲባ ሆነው የተመረጡት ኢክሬም ኢማሞግሉ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መወዳደር ከቻሉ እንደሚያሸንፉ ከሕዝብ የተሰበሰበ አስተያየት ይጠቁማል።

የሚቀጥለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአውሮፓውያኑ 2028 ይካሄዳል።

በተቃዋሚው ፖለቲከኛ የኤክስ ገጽ ላይ የሚታየው መልዕክት ገጹ በቀረበበት ሕጋዊ ጥያቄ ምክንያት እንደታገደ ይገልጻል። ነገር ግን ገጹ በቪፒኤን ቱርክ ውስጥ እየሠራ ነው።

የታገደው የኤክስ ገጽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኤክስ ጠበቃ በበኩላቸው በማኅበራዊ ሚዲያው ጥያቄ መሠረት እገዳውን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል።

የኢስታንቡል ዐቃቢያን ሕጎች የኢማሞግሉ አካውንት ላይ የሚወጡት ልጥፎች ወንጀል እንዲፈጸም የሚያነሳሱ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ምርመራ እያደረገ ነው ሲል የፕሬዝዳንቱ የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ባለፈው ወር ከንቲባው በጽሑፋቸው እስራቸውን እና በተቃዋሚዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ አውግዘው ሕዝቡ ቅሬታ እንዲያሰማ እና "ድምጻችሁን ከፍ አድርጉ" ሲሉ ጠይቀዋል።

አንዳንድ የኤክስ ተጠቃሚዎች ምስላቸውን በከንቲባው ፎቶ ቀይረዋል። በዋሽንግተን የዊልሰን ማዕከል የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሮግራም ተንታኝ ዩሱፍ ካንም ይህንኑ አድርገዋል።

"ኢለን መስክ የታጋቹን ከንቲባ እና ፕሬዚዳንታዊ ዕጩውን ገጽ በኤርዶጋን ጥያቄ አግዷል። ይህም የአገሪቱን ታዋቂ የተቃዋሚ ድምጽ ዝም ለማሰኘት ነው። ሁላችንም ኢማሞግሉ ነን" ብለዋል።

ከንቲባው ከመጋቢት ወር ጀምሮ በሙስና ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ ይገኛሉ።

ኢክራም ኢማሙግሉ በተመረጠበት ከተማ ዳርቻ በሚገኘው በሲሊቪሪ የማርማራ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።