ሁለት ጥቁር አሜሪካውያንን ከባልደረቦቹ ጋር ያሰቃየው የቀድሞ የፖሊስ አባል 40 ዓመት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, AP
በአሜሪካ ሚሲሲፒ ግዛት የፖሊስ አባል የነበረው ግለሰብ ከሌሎች አምስት ባልደረቦቹ ጋር ሆኖ ሁለት ጥቁር አሜሪካውያንን በቤት ውስጥ በማሳቃየቱ የ40 ዓመት እስር ተበይኖበታል።
ክርስቲያን ዴድሞን የተባለው የቀድሞ የፖሊስ መኮንንን ከባልደረቦቹ ጋር ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ለፈጸመው ወንጀል ነው ቅጣት የተጣለበት።
ሌሎች ሶስት የፖሊሰ መኮንኖች ደግሞ በድምሩ የ54 ዓመታት እስር ተፈርዶባቸዋል።
ማይክል ጄንኪንስ እና ኤዲ ፓርከር የተባሉት ጥቁር አሜሪካውያን በፖሊስ መኮንኖቹ በመሳሪያ ሰደፍ የተደበደቡ ሲሆን ወሲባዊ ጥቃትም ደርሶባቸዋል።
አንደኛው ተጠቂ ጄንክሰን ችሎት ላይ በጠበቃው አማካኝነት ባስነበበው ጽሁፍ 40 ዓመት የተፈረደበት የቀድሞ መኮንን ከፍተኛውን ስቃይ ያደረሰበት እንደሆነ ገልጿል።
“ዴድሞን በአሜሪካ ውስጥ የመጥፎ ፖሊስ መኮንኖች ምሳሌ ነው” ሲለም አክሏል።
የቀድሞው የፖሊስ መኮንን ተበዳዩ ላይ ከመግደል መለስ ያሉ ጥቃቶች ሲያደርስ አፉ አከባቢ ላይ ተኩሶበታል። በዚህም ምንክያት ጄንክስን እስካሁን ለመናገር ይቸገራል።
በአንዲት ነጭ ቤት ውስጥ ጥቁር አሜሪካዊ በመቆየቱ እና በነበሩ አጠራጣሪ ድርጊቶች የአከባቢው ነዋሪዎች ጉዳዩን ለፖሊስ አሳውቀዋል። ፖሊሶቹን ጥቃቱን እየፈጸሙም በስልክ ይነጋገሩ ነበር።
ለአንድ ሰዓት ከሰላሳ ደቂቃ ያህል ጄንኪንስ እና ፓርከር እጃቸው ታስሮ ሲደበደቡ እና የዘረኝነት ጥቃት ሲደርሰባቸው እንደነበር ተመላክቷል።
የአሜሪካ የአውራጃ ፍርድ ቤት ዳኛው ቶም ሊ ዲድሞን ሁለት ጥቁሮች እና ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ደግሞ አንድ ነጭ አሜሪካዊ ላይ “እጅግ አስደንጋጭ፣ አሰቃቂ እና ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት” ፈጽሟል ብለዋል።
ዴድሞን 40 ዓመት እንደተፈረደበት ከመታወቁ አስቀድሞ ሌላኛው ባልደረባው ኦፕዴክ 17 ዓመት ከ 6 ወር ተበይኖበታል።
ብሬት ማክአልፒን እና ጆሸዋ ሃርትፊልድ የተባሉት የቀድሞ የፖሊሰ መኮንኖች ደግሞ ዛሬ የብይን ውሳኔ እንደሚተላለፍባቸው ይጠበቃል።
ራሳቸውን “ጠባቂው ቡድን” እያሉ የሚጠሩት ስድስቱ የቀድሞ ፖሊስ መኮንኖች በሙሉ ነጭ ናቸው።
የፍርድ ውሳኔው ሲነበብ የዴድሞን ቤተሰቦች ችሎት ውስጥ እያለቀሱ ታይተዋል።
ዴድሞን ለፈጸመው ድርጊት ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን “ለራሴ መቼም ይቅርታ አላደርግም” በሚል ሌሎች ሶስት ባልደረቦቹ እንዳደረጉት ተጎጂዎቹን ፊት ለፊት እየተመለከተ ይቅርታ አልጠየቀም።
ሌላኛው ባልደረባው ኦፕዴክ ተበዳዮቹን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን “የፈጸምኩት ድርጊት ክብደት ያደረስኩት ጉዳት በየቀኑ ሲቀጣኝ ይኖራል” ብሏል።
የቀድሞ የፖሊስ መኮንኑ ኤልዋርድ የ20 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
የቡድኑ መሪ እንደሆነ የሚገለጸው ሚድልቶን ደግሞ 17 ዓመት ተበይኖታል።
አቋቁመናል የሚሉት ቡድን ደግሞ ባለፈው ነሐሴ የሲቪል መብቶችን በመጣስ ጥፋተኛ ተብሏል።
ቡድኑ መብቶችን ለማጣስ በማሴር፣ በቆዳ ቀለም ለይቶ በማጥቃት እና ፍትህን ለማዛባት በመሞከር የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የአካባቢያቸው የፖሊስ ኃላፊ ብራያን ቤሊይ የፖሊስ መኮንኖቹን በሚገባ አላሰለጠነም በሚል የ400 ሚሊዮን ዶላር ክስ ቀርቦበታል።












