በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የመመሥረቱ ሂደት የዘገየው ለምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በተደረሰው ስምምነት መሠረት በምርጫ ተካሂዶ መደበኛ አስተዳደር እስኪመሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት በሚያካሂዱት ፖለቲካዊ ውይይት ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ይገልጻል።
የጊዜያዊ መንግሥት መቋቋም ትግራይ ውስጥ ያለውን ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት እና ሁኔታዎችን ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑ ይነገራል።
በክልሉ የሚገኙ ከሁለት ዓመት በላይ ደሞዝ ያልተከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞችም ደመወዛቸውን ለማግኘት ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙን በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በአካል ተገናኝነተው መወያየታቸውን ተከትሎ፣ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ አስተዳደር ሲቋቋም በጀት አንደሚለቀቅ መግለጻቸውን ተናግረዋል።
የፕሪቶሪያው ውል አራት ወራ ቢያልፈውም እስካሁን በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አልተቋቋመም። ነገር ግን የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊው መንግሥት ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መሰየሙ ተገልጿል።
ይህም በክልሉ ጊዜያዊ መንግሥት ለማቋቋም የተመሠረተውና የተለያዩ አካላት እንደተካተቱበት የሚነገረውን ስብስብ እና የፌደራል መንግሥቱን ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል።
“ራሳችሁ አቋቁሙት”
ከየካቲት 22/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በመቀለ በተካሄደ ሕዝባዊ ውይይት ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጄኔራል ተክላይ አሸብር፤ የትግራይ ኃይሎችን በመወከል የምሥረታውን ሂደት የሚመራው ኮሚቲ አባል ናቸው።
የፕሪቶሪያ ውል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት ተወያይተው ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚመሠርቱ ይገልጻል። "ራሳችሁ አቋቁሙት እና ሐሳብ እንሰጣለን እንጂ የምንልከው ሰው አይኖርም። ራሳችሁ ጨርሱት ተብለናል” ሲሉ በክልሉ ለሚገኙ መገናኝ ብዙኃን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቢደረግላቸውም ሳይሳተፉበት ቀርተዋል።
ሳውት፣ ውናት እና ባይቶና የተሰኙት ፓርቲዎች ሂደቱ ከጀምሩ "የአሳታፊነት እና የፍትሃዊነት ችግር አለበት" በሚል ነው ከጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታው እራሳቸውን ያገለሉት።
አዲስ የተቋቋመው ካቢኔ 28 አባላት አሉት። የህወሓት፣ የትግራይ ኃይሎች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ምሑራን እና ሲቪክ ማኅበራት እንደተካተቱበት ተነግሯል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ግን በየካቲት ወር መጨረሻ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባጋሩት ጽሑፍ “ያለ ማዕካዊ መንግሥት ተሳትፎ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሟል የሚባለው ሐሰት ነው። ትግራይ ድርሻዋን ለመወጣት ብቻ ነው የምትጥረው” ማለታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታ እስካሁን የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።
በእንጥልጥል ያሉ ጉዳዮች
ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ካሳ፤ በመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል የሕገ መንግሥት እና ፌዴራሊዝም መምህር ናቸው።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ህወሓት ሠራዊቱን ከውጊያ አካባቢዎች በማራቅ እና የጦር መሣሪያ በማስረከብ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማስጀመር የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መፈፀማቸውን ይናገራሉ።
ሆኖም ጊዜያዊ አስተዳደር በመመሥረት ጉዳይ ግን መጓታት አለ ይላሉ።
ውሉ፤ እንደሚገልፀው "ህወሓት በአገሪቱ ፓርላማ ከሽብርተኝነት ዝርዝር ከወጣ ከሰባት ቀናት በኋላ ጊዜያዊ አስተዳደር ይመሠረታል" እንደሚል የሚናገሩት ምሑሩ ለጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታው መጓተት ፌዴራል መንግሥቱን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
ነገር ግን ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዶ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱን እንደሰሙ የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ “አደገና የድብብቆሽ ጨዋታ እየተካሄደ ነው” በማለት ስጋታቸውን ለቢቢሲ ይገልጻሉ።
“ሂደቱ ትክክለኛ ነው ተብሎ አስተዳደር እንዲቋቋም አልተደረገም። አሊያም የፌዴራል መንግሥቱ ተቀብሎ አላፀደቀውም። ወይ ደግሞ በግልፅ ያሉት ችግሮች አልተነገሩም። ህወሓትም ከሽብርተኝነት መዝገብ አንሱኝ ሲል አልሰማንም።”
ምሑሩ አክለው “ህወሓት ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲሰረዝ አለመጠየቁ የሥልጣኑ ጉዳይ ብቻ እንደሚያስጨንቀው ማሳያ ነው” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, tigray tv
“የሥልጣን ሽኩቻ”
በትግራይ ያለውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታትል እና በመተንተን የሚታወቀው ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ፤ ከተኩስ አቁሙ በኋላ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ወታደራዊ ማስተካከያዎች ስለነበሩ ነው የጊዜያዊ አስተዳደር መሥረተው የዘገየው ይላል።
ሆኖም የህወሓት አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከተገናኙ በኋላ በራሳቸው አካታች የሆነ አስተዳደር እንዲመሠርቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቃድ መስጠታቸውን የሚገልጽ መረጃ እንዳለው ጋዜጠኛው ይገልጻል።
“መንግሥት ‘ከብልጽግናም ሆነ ከሌላ ኃይል ተሳታፊ ለመላክ ፍላጎት የለኝም። ትግራይ ውስጥ ባሉት አካላት አሳታፊ እና አቃፊ በሆነ መንገድ አቋቁሙ። ስትጨርሱ እንነጋገራለን” መባሉን ጌታቸው አረጋዊ ይናገራል።
አክሎም በዚህ ውስጥ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በተለይም በፖሊት ቢሮ ውስጥ የነበሩ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ባይሆኑ በማለት የራሳቸውን ምክንያት እንደሰጡ መገለጹን እንደሚያውቅ ገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሁንታ ተከትሎ በህወሓት እና በሠራዊቱ አመራሮች መካከል ረዥም ጊዜ የወሰደ ውይይት መካሄዱን የሚጠቅሰው ጌታቸው፣ “በሠራዊቱ አመራሮች መካከል መግባባት ቢደረስም በፓርቲው ውስጥ ግን ለውጥ እና ሥልጣንን በሚመለከት ልዩነት እንደተፈጠረ መረጃ አለኝ” ይላል።
“ወደ ሥልጣን ሽኩቻ በመግባታቸው ምክንያት ነው ጊዜ የወሰደው። በፌዴራል መንግሥት በኩል የምትፈልጉትን ወደ ሥልጣን አምጡ የሚል ፈቃድ ይኖራል።
“በህወሓት በኩል ግን የሥልጣን ሽኩቻ በግልፅ የሚታይ ነገር ነው። በሌላ በኩል ሥልጣን መቆጣጠር የሚፈልግ ኃይል ይኖራል። በእነዚህ ምክንያቶች ጊዜ ወስዷል ብዬ አስባለሁ።”
የሕገ-መንግሥት እና ፌዴራሊዝም መምህሩ የማነ ካሳም በተመሳሳይ፤ በሥልጣን ክፍፍሉ ዙሪያ ህወሓት ውስጥ ልዩነት ስለመኖሩ ይናገራሉ።
ተቃዋሚዎች ያልተቀበሉት የሽግግር ካቢኔ
ትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አራት ተቃዋሚ ድርጅቶች በተጠራው የጊዜያዊ አስተዳደር ምሥረታ ጉባዔ 15 በመቶ ድርሻ ይዘው እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን፤ ሂደቱ ከጅምሩ አሳታፊ አልነበረም በማለት ሦስቱ ፓርቲዎች ሳይገኙ ቀርተዋል።
ተወካዮቹን የላከው ብቸኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የአሲምባ ዲሞክራስያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ነው።
ተመሠረተ የተባለው ጊዜያዊ አስተዳደር “አካታች አልነበረም” ብለው የሚተቹት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የማነ ካሳ፤ ለዚህም ህወሓትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
“አስመራጭ ኮሚቲውን በተመለከተ ጄኔራል ታደሰ ወረደ እንደተናገሩት፤ መጀመሪያ ማንንም ሳያሳትፉ ህወሓት እና የትግራይ ኃይሎች ናቸው የመሠረቱት።
“አባላት ናቸው የተባሉት ምሑራን እና የሠራዊት አመራሮችም በህወሓት የተመረጡ እንጂ በሚወክሉት ማኅበር የተመረጡ አይደሉም። ሂደቱንም እንዲያስተካክሉ በፓርቲዎች የተሰጣቸውን አስተያየትም ውድቅ አድርገውታል” ይላል።
ሂደቱ “ግልጽ፣ ዲሞክራሲያዊ እና አካታች አልነበረም” የሚል እምነት ያለው ጋዜጠኛ ጌታቸውም፤ የሚመለከታቸው አካላት በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይሳተፉ የሚያደርግ መንገድ ተከትሏል ሲል ይወቅሳል።
“ይህ የሆነበት ምክንያት ወደ ግልጽ እና አካታች ሂደት ከተገባ ሌላ ሰው ሥልጣን ይይዛል የሚል ስጋት ስላላቸው ይመስለኛል” ይላል።
ጊዜያዊ አስተዳደር መዘግየት ያስከተለው ጫና
ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ያዋቀሩትን ጊዜያዊ አስተዳደር በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውን የሚገልጸው ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸውን ካቢኔ እንዳልተቀበሉት መረጃ እንዳለው ይናገራል።
“የህወሓት ፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት አምስት ሰዎች ለፕሬዝዳንትነት እንዳይወዳደሩ ይፈልጋሉ። የጉባኤው አካሄድ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውን፣ ህወሓት ፍጹም የበላይ ሆኖ የመሪነቱን ድርሻ ይዞ መሄዱን አለመደገፋቸውን፣ በካቢኔው ብዛት ጥያቄ ማንሳታቸው እና ለውጥ እንዲደረግ መናገራቸውን ሰምቻለሁ።”
የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ህወሓት ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ባለፈው ሳምንት አካሄዱት ስለተባለው ስብሰባ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰጠ ስለተባለው አስተያየት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ሆኖም ባለፈው ሳምንት በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝቶ መነጋገሩን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸውን የካቢኔ አወቃቀር ውድቅ ማድረጋቸውን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የህወሓት አመራር ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ውስጥ አዋቂው እንደሚሉት ደብረጽዮን የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ የቀረበው ሐሳብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀባይነት አለማግኘቱን ጠቅሰው፤ ፓርቲው በቅርቡ ስብሰባ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለመመሥረቱ በጦርነቱ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠው ሕዝብ ስቃዩ እንዲቀጥል አድርጎታል ያላሉ አስተያየት ሰጪዎቹ።
“በሚልዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ጉዳይ ፖለቲካዊ ውይይት ተከትሎ መፈታት ያለበት ተደርጎ ተወስዷል” የሚለው ጋዜጠኛ ጌታቸው አረጋዊ፤ በትግራይ ቅቡልነት ያለው አስተዳደር ባለመመሥረቱ ተፈናቃዮቹ ወደቤታቸው መመለስ እንዳልቻሉ ይገልጻል።
መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር ከመመሥረቱ በፊት የክልሉ በጀት ለመልቀቅ ፍቃደኛ ባለመሆኑ፤ ሕዝቡን ቀጥታ ተጠቂ አድርጎታል ባይ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ “በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩ እና በፖለቲካ የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች፤ አሁንም እሥር ቤት ነው ያሉት። በፖለቲካዊ ውይይት መፈታት የነበረባቸው ናቸው” ይላል።
በጋዜጠኛው ሐሳብ የሚስማሙት ተባባሪ ፕሮፌሰር የማነ ካሳ “በክልሎች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ላደራድር የሚል አካል እንኳን ቢመጣ፤ የትግራይ ሕዝብ እና መንግሥትን ወክሎ ሊደራደር የሚችል ኃይል የለም። የመንግሥት ክፍተት አለ፤ ይህ ደግሞ ለብዙ ችግሮች ምክንያት ነው” ይላሉ።












