የኡጋንዳ ማረሚያ ቤት ፖሊስ ባልደረባ መንግሥትን ቲክቶክ ላይ በመተቸቱ ተባረረ

የፎቶው ባለመብት, Ampe/TikTok
የኡጋንዳ ማረሚያ ቤት ፖሊስ ባልደረባ ቲክ ቶክ ላይ መንግሥትን በመተቸቱ ከሥራ ሲባረር የአገሪቱ ባለስልጣናት ባልተለመደ መልኩ "ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ጥሰት" ፈጽሟል ሲሉ ወነጀሉት።
ላውረንስ አምፔ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን በሙስና፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባሉ የእስር ቤት ኃላፊዎች ላይ በፈጸሙት በደል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋራው መልዕክት የተነሳ ምርመራ እየተደረገበት ነበር።
"በሥራ ላይ ያሉት የአገሪቱ ሕጎች አንድ የፖሊስ ባልደረባ በፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፍ አይፈቅዱም፤ እርሱ ግን ያደረገው ያንን ነው" ሲሉ የእስር ቤቱ ቃል አቀባይ ፍራንክ ቤይን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አምፔ "በተሳሳተ መድረክ ላይ ፖለቲካዊ አስተያየቶችን በመስጠት" ከሥራ መባረሩን ተናግረዋል።
በአገሪቱ የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚ ፓርቲ የመንግሥትን እርምጃ አውግዟል።
በፀጥታ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ውስጥ ያለው "ሥልታዊ ጭቆና" እና "አድሏዊነትን" የሚያሳይ ማስረጃ ነው ሲል ገልጾታል።
ፖሊሱ በቲክቶክ አካውንቱ ላይ "በመጨረሻም እውነቱን ለመደገፍ ነፃ ነኝ" በማለት ከሥራ የተባረረበትን ደብዳቤ አጋርቷል።
በሌላ ቪዲዮ ላይ አምፔ ኡጋንዳውያን ያለ ሥራ እንዴት ይኖራል ብለው እንዳይጨነቁ አሳስቧል።
"እየሰራን ያለነው ስለ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን አገራችንን ነፃ ስለማውጣት ነው" ብሏል።
ከ100 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የቲክ ቶክ አካውንቱን በመጠቀም በሙስና የተሳተፉ እና ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን እያጋለጠ መሆኑን እና ኡጋንዳውያን አገራቸውን እንዴት መውደድ እንዳለባቸው ለማሳወቅ እየተጠቀመበት መሆኑን ተናግሯል።
የፖሊስ ባልደረባው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹን የተቃዋሚ መሪ ቦቢ ዋይንን የምርጫ ቅስቀሳ ቪዲዮዎችን ለማስተዋወቅም ይገለገልበታል።
ቦቢ ዋይን እአአ በጥር 15 በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ለ40 ዓመት በሥልጣን ላይ የቆዩትን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒንን ለማሸነፍ ይፎካከራል።
የማረሚያ ቤቶች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፣ አምፔ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ "ከሥራ ለማሰናበት መወሰኑን" እና በእጁ ያሉትን የመንግሥት ንብረቶች በሙሉ እንዲያስረክብ አዝዟል።
ዋይን የኡጋንዳ ሕጎች የመንግሥት ሠራተኞች በፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ አይፈቅዱም ብለዋል።
"ፖለቲካዊ ድርጊቱን እንዲቀጥልበት በትክክለኛው መድረክ ላይ አስቀምጠነዋል" ሲሉ የእስር ቤቱ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አምፔ በእስር ቤቶች ምክር ቤት ፊት በቀረበበት ወቅት በድርጊቱ መፀፀቱን አለማሳየቱን ጨምረው ተናግረዋል።
ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጥበት አምፔን አነጋግሮታል።
ባለፈው ወር የኡጋንዳ ማረሚያ ቤቶች አገልግሎት አምፔ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሰራቸውን የቲክ ቶክ ቪዲዮዎችን እየመረመረ መሆኑን ገልጾ፣ የፖሊስ ባልደረቦች የፖለቲካ አመለካከታቸውን ለመግለጽ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አስጠንቅቋል።
የመንግሥት ሠራተኞች ከኃላፊዎቻቸው ፈቃድ ውጭ "ከሥራ ወይም ከይፋዊ የፖሊስ ተግባራት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች" ላይ ለመገናኛ ብዙኃን አስተያየታቸውን እንዳይሰጡ የሚከለክሉ ሕጎችን ጠቅሷል።
የአገሪቱ ባልሥልጣናት ይህንን ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም አምፔ ግን የተለያዩ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ቪዲዮዎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማጋራቱን መቀጠሉ ተዘግቧል፤ በዚህም የተነሳ ተጨማሪ የሥነ ምግባር እርምጃዎች ተወስደውበታል።
ቦቢ ዋይን አምፔ ማኅበራዊ ሚዲያን የሚጠቀመው "በኡጋንዳ የእስር ቤት አገልግሎት ውስጥ ያለውን ሙስና፣ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸውን መኮንኖች ጭቆና እና ሌሎች ክፋትን ለማጋለጥ" ነው ሲል ተከላክሎለታል።
የፖሊስ መኮንኑ ከሥራ መባረሩ አድልኦ መኖሩን የሚያንፀባርቅ መሆኑን ጠቅሶ፤ በተለይም በአገሪቱ መከላከያ ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት ለፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ አመራር ድጋፍ እንደሚሰጡ በተደጋጋሚ በሚዲያ ቀርበው ሲናገሩ የሥነ ምግባር እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው ገልጿል።
የኡጋንዳ መንግሥት ከዚህ ቀደም ሕዝቡ የመንግሥትን ወይም የባለሥልጣናቱን ድርጊት እንዳይተቹ በመገደብ ተከሷል።
የመብት ተሟጋቾች የኡጋንዳ ባለሥልጣናትን በሰብዓዊ መብቶች እና ሀሳብን በነፃነት በመግለጽ ዙሪያ በተደጋጋሚ ያወግዛሉ።
ባለፈው ሐምሌ ወር፣ አንድ ግለሰብ በቲክ ቶክ ቪዲዮ ላይ ፕሬዝዳንቱን እና ቤተሰባቸውን በመሳደቡ የ24 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።
ግለሰቡ ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ ይቅርታ ጠይቋል።















