ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩኬ የስለላ ተቋም ሩሲያ ተጨባጭ አደጋ ደቅናለች ሲል አስጠነቀቀ
አዲሷ የኤምአይ ሲክስ ኃላፊ ብሌዝ ሜትሬዌሊ ዛሬ በሚያደርጉት ንግግር "ሩሲያ ስለደቀነችው ተጨባጭ ስጋት" እንደሚያስጠነቅቁ ተገለፀ።
የሩሲያ ወኪሎች ስለደቀኑት እና ወሳኝ የሚባሉ መሠረተ ልማቶች ላይ የሳይበር ጥቃትን እና የድሮን ጥቃትን ስለቀላቀለው ቅይጥ ውጊያቸው አጽንኦት ሰጥተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ሜትሬዌሊ "ሩሲያ ተስፋፊ፣ የቀድሞውን ናፋቂ እና ጠበኛ፣ ተጨባጭ ከባድ ስጋት የደቀነች" በማለት ይገልጿታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት በመጥቀስም ብሪታኒያ ከዩክሬን ጎን በመቆም ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሏል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመረጃ አገልግሎት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ሜትሬዌሊ የብሪታንያን የውጭ አገር የስለላ ኤጀንሲ የሚመሩ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው።
ከጥቅምት 1 ጀምሮ ከሰር ሪቻርድ ሙር ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል።
ሰኞ ዕለት የሚያደርጉት ንግግር በቅርቡ የመረጃ ጦርነት በመክፈት የተከሰሱትን በሩሲያ እንዲሁም በቻይና የሚገኙ ሁለት ኩባንያዎችን የሚጠቅስ ይሆናል።
በዚህም የተነሳ በኩባንያዎቹ ላይ "በዩኬ እና በአጋሮቿ ላይ ያለ ልዩነት የሳይበር እንቅስቃሴ ላይ በፈጠሩት ማወክ" ምክንያት ማዕቀብ እንደተጣለባቸው የሚያመለክት ነው።
የምዕራባውያን ማዕቀቦች የሩሲያን ኢኮኖሚ ያሽመደመዱ ሲሆን ወደ ውጪ የምትልካቸውን ምርቶች ከምዕራባውያን አገራት ይልቅ ወደ ቻይና እና ሕንድ እንድታዞር አድርጓታል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ ፕሬዚዳንት ፑቲን ዩክሬን ላይ የከፈቱትን ጦርነት እንዲያቆሙ ማድረግ አልቻለም።
ከዚያ ይልቅ በቁጥጥራቸው ስር ማስገባት የሚፈልጓቸውን የዩክሬን ግዛቶች እስኪያገኙ ድረስ ጦርነቱን ለመቀጠል ዝተዋል።
ሜትሬዌሊ በሚያደርጉት ንግግር ለአዲሱ የስለላ ኃላፊ ልዩ ትኩረት የሚሰጡት የቴክኖሎጂ ጉዳዮች እንደሚሆኑ ተገልጿል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1999 የምስጢራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤቱን የተቀላቀሉት ብሌዝ ሜትሬዌሊ፤ የድርጅቱ 18ኛ ኃላፊ ሆነው ከሰር ሪቻርድ ሙር ኃላፊነታቸውን ተረክበዋል።
በደኅንነት መስሪያ ቤቱ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ ቢሮ ውስጥ በኃላፊነት እየሰሩ የነበሩት ኃላፊዋ ተቋሙን እንዲመሩ ሲጠየቁ የተሰማቸውን ኩራት እና ክብር ገልጸው ነበር።
ኃላፊዋ በኋላ ላይ በሚያደርጉት ንግግር ላይ ሁሉም የደኅንነት ተቋሙ ባልደረቦች ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ብቁ እንዲያደርጉ ጥሪ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
"በላቦራቶሪዎቻችን ብቻ ሳይሆን በመስክም ሆነ በመረጃ ልውውጥ ስራችን. . . የሰው የመረጃ ምንጮችን እንደምንጠቀም ሁሉ፣ በኮምፒውተር የኮድ ቋንቋዎችንም እንዲሁ እንደ ፓይተን አቀላጥፈን መናገር አለብን።"
ኤም አይ ሲክስ የዩናይትድ ኪንግደምን ደኅንነት ለማረጋገጥ በሌላ አገር የስለላ ስራዎችን የማካሄድ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ዋና ዓላማው ሽብርተኝነትን ማስቆም፣ የጠላት አገራትን እንቅስቃሴ ማወክ እና የሳይበር ደኅንነትን ማጠናከር ናቸው።
በተለምዶ ዋና ኃላፊው "ሲ" በመባል የሚጠራ ሲሆን ብቸኛው በይፋ ማንነቱ የሚገለጽ የደኅንነት መስርያ ቤቱ አባል ነው።
የ47 ዓመቷ ሜትሬዌሊ የ "Q" ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።
ኪው "Q" ሚስጥራዊ የስለላ አባላትን ማንነት ለመጠበቅ ያለመ ወሳኙ የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ክፍል ነው።
ይህ ክፍል ቻይና በአሻራ ላይ (ባዮሜትሪክስ ሰርቨይላንስ) በመመስረት የምታደርገውን ክትትል ለማለፍ አዳዲስ መንገዶችን ይጠቀማል።