የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዚደንት ከቀብር አፈፃፀም ጋር በተያያዘ አለመግባባት በደቡብ አፍሪካ ሊቀበሩ ነው

ከቀብር አፈፃፀም ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከመንግሥት ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የቀድሞው የዛምቢያ ፕሬዚደንት ኤድጋር ሉንጉ ቀብር በደቡብ አፍሪካ እንደሚፈፀም ቤተሰቦቻቸው ገለጹ።

ቤተሰቦቻቸው የቀድሞው ፕሬዚደንት አስክሬን ከደቡብ አፍሪካ ወደ ዛምቢያ እንዲሄድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ባለፈው ማክሰኞ ፕሬዚደንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ የታወጀውን ብሔራዊ የሃዘን ቀን አሳጥረዋል።

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በዛምቢያ መዲና ሉሳካ እሁድ ይፈፀማል ተብሎ ታቅዶ ነበር።

ሆኖም በኋላ ላይ ቤተሰቦቻቸው ሉንጉ በጆሃንስበርግ "በክብር" እና "በሰላም" እንደሚቀበሩ አስታውቀዋል።

የሌላ አገር የቀድሞ መሪ የቀብር ሥነ ሥርዓት በደቡብ አፍሪካ ሲፈፀም ይህ የመጀመሪያው ይሆናል።

ሉንጉ የረጅም ጊዜ ተቀናቃኛቸው የሆኑት ሂቺሌማ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ላይ መገኘት እንደሌለባቸው ተናግረው የነበረ ቢሆንም መንግሥት እና ቤተሰቦቻቸው ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲፈፀምላቸው ተስማምተው ነበር።

ሆኖም በኋላ ላይ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ መርሃ ግብር ላይ አለመግባባት ተፈጥሯል።

የቤተሰቦቻቸው ቃል አቀባይ ማኬቢ ዙሉ " የምንወደው ዶክተር ኤዲጋር ቻግዋ ሉንጉ የቀብር ሥነ ሥርዓት በቤተሰቡ ፍላጎት መንግሥታዊ ባልሆነ ሥነ ሥርዓት በደቡብ አፍሪካ እንደሚፈፀም መግለፅ እንፈልጋለን" ብለዋል።

ዙሉ ጨምረውም በዚህ የሃዘን ጊዜ "የቤተሰቦቻቸውን ውሳኔ" እና "ፍላጎት በማክበር" እንዲሁም "ጣልቃ ባለመግባት" የደቡብ አፍሪካን መንግሥት አመሰግነዋል።

ፕሬዚደንት ሂቺሌማም ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ "የቀድሞው ፕሬዚደንት ሉንጉ የዛምቢያ ናቸው፤ አስክሬናቸው በክብር ማረፍ ያለበትም በሌላ አገር ሳይሆን ዛምቢያ ነው" ብለዋል።

ሆኖም የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ "አገሪቷ ወደ መደበኛ ሕይወቷ መመለስ አለባት" ሲሉ የታወጀው ብሔራዊ የሃዘን ጊዜ ማብቃቱን አስታውቀዋል።

"መንግሥት በሕይወት ከተለዩን ስድስተኛው ፕሬዚደንት ቤተሰቦች ጋር ለመነጋገር የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል" ብለዋል ሂቺሌማ።

የታወጀው ብሔራዊ የሃዘን ቀን መጀመሪያ ላይ ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 8 እስከ 14 የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ እስከ ሰኔ 23 እንዲቆይና ሰንደቅ ዓላማም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ እንዲሁም የራዲዮ ጣቢያዎችም ረቂቅ ሙዚቃዎች እንዲያሰሙ ተደርጎ ነበር።

ፕሬዚደንት ሂቺሌማ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናትም የሉንጉን አስክሬን በወታደራዊ የክብር ሥነ ሥርዓት ረቡዕ ዕለት ለመቀበል ተዘጋጅተው ነበር።

ሆኖም የሉንጉ ቤተሰቦች የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በተመለከተ መንግሥት የገባውን ቃል አጥፏል በማለት በመጨረሻ ሰዓት አስክሬናቸው ወደ ዛምቢያ እንዲወሰድ ሳይፈቅዱ ቀርተዋል።

ሉንጉ ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ ሲመሩት የነበረው ተቃዋሚው ፓትሪዎቲክ ፓርቲ (ፒኤፍ) የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በተመለከተ የቤተሰቦቻቸውን አቋም ደግፏል።

አሁን ላይ የፓርቲውን ፕሬዚደንት ተክተው እየሰሩ ያሉት ጊቭን ሉቢንዳ " መንግሥት ይህንን አሳዛኝ ክስተት ወደ ፖለቲካ ለውጦታል። ለቀድሞ የአገር መሪ የምንሰጠው ክብር እንዲህ መሆን አልነበረበትም" ብለዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖችም አለመግባባቱ በአስቸኳይ እንዲፈታ የጠየቁ ሲሆን የሃይማኖት አባቶችም "የተያዘው አቋም የአገራችንን ክብር እየጎዳ ነው" ብለዋል።

ሉንጉ ዛምቢያን ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2021 ድረስ የመሩ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ባልታወቀ ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሕይወታቸው አልፏል።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱ አገራቸውን ለ6 ዓመታት ከመሩ በኋላ በ2021 በተካሄደው ምርጫ በከፍተኛ ልዩነት በሂቺሌማ ተሸንፈዋል። ከዚያም ከፖለቲካ ወጥተው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ወደ ትግሉ ተመልሰው ነበር።

በድጋሜ ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደርም ፍላጎት ነበራቸው፤ ነገር ግን ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ ሕጉ የሚፈቅደውን ሁለት የሥልጣን ዘመን አገልግለዋል በሚል በምርጫ ከመወዳደር አግዷቸዋል።

ምንም እንኳን ከፕሬዚደንታዊ ምርጫ ቢገለሉም ሉንጉ በዛምቢያ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበሩ። በተተኪያቸው ላይ ትችት ከመሰንዘርም ወደ ኋላ የሚሉ አልነበሩም።