ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአውስትራሊያ አይሁዶች ላይ ጥቃት የፈጸመውን ታጣቂ መሳሪያውን የነጠቀው ሙስሊም
"ጀግናው" ግለሰብ የ43 ዓመቱ አሕመድ አል አሕመድ ይባላል። በአውስትራሊያው በጦር መሳሪያ ጥቃት ከፈጸሙት ሁለት ግለሰቦች መካከል ከአንዱ ጋር ሲታገል አይተው የተገረሙ ብዙዎች ናቸው።
ቢቢሲ ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምሥል እንደሚያሳየው አሕመድ ወደ ጥቃት አድራሹ ሮጦ በመሄድ መሳሪያውን ነጥቆ ያነጣጥርበታል። ጥቃት አድራሹም ይሸሻል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነው አሕመድ የፍራፍሬ ሱቅ አለው። እጁ እና ክርኑ ላይ በጥይት በመመታቱ የሕክምና እርዳታ እያገኘ እንደሆነ ቤተሰቦቹ ለ7ኒውስ አውስትራሊያ ተናግረዋል።
እሑድ አመሻሹን በደረሰው ጥቃት 15 ሰዎች ሲገደሉ ከአርባ በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
የጥቃቱ ዒላማ የሆኑት አንድ ሺህ ገደማ ሰዎች ሀነካህ የተሰኘውን የአይሁዶች በዓልን ለማክበር ነበር በአውስትራሊያዋ ቦንዲ የባሕር ዳርቻ የተገኙ ሰዎች ናቸው።
ፖሊስ ድርጊቱ የአይሁድ ማኅበረሰብ ላይ የተቃጣ የሽብር ድርጊት ነው ብሎታል።
የአሕመድ ዘመድ የሆነው ሙስጠፋ ለ7ኒውስ አውስትራሊያ ሲናገር "እሱ ጀግና ነው። መቶ በመቶ ጀግና። ሁለት ቦታ በጥይት ተመቷል። እጁ እና ክርኑ ላይ" ብሏል።
ሙስጠፋ ሰኞ በሰጠው ቃለ ምልልስ "ደኅና እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ማታ አይቸው ነበር። ደኅና ነው፤ ነገር ግን ዶክተሮቹ ምን እንደሚሉ ለመስማት እየጠበቅን ነው" ብሏል።
ፖሊስ እንደገለፀው ጥቃት አድራሾቹ የ50 እና የ24 ዓመት አባት እና ልጅ ናቸው።
የ50 ዓመቱ አባት በጥቃቱ ስፍራ ሲገደል መሳሪያውን በአሕመድ የተነጠቀው የ24 ዓመቱ ልጅ ደግሞ ሆስፒታል ውስጥ በሞት እና በሕይወት መካከል ይገኛል።
አሕመድ ከጥቃት አድራሹ ጋር ትግል ሲገጥም የሚታይበት ምሥል በማኅበራዊ ሚድያ ላይ በሰፊው ተጋርቷል።
ከጥቃቱ አድራሾቹ መካከል አንደኛው ከአንድ አነስተኛ የእግረኛ ድልድይ አጠገብ ከሚገኝ ዛፍ ስር ሆኖ ሲተኩስ ይታያል።
ከቆመ መኪና ጀርባ ተደብቆ የነበረው አሕመድ ከጥቃት አድራሹ ጀርባ መጥቶ በመታገል የጦር መሳሪውን ከነጠቀው በኋላ ወደ መሬት ገፍትሮ ጥሎት መሳሪውን ይደግንበታል። ጥቃት አድራሹ በማፈግፈግ ወደ ድልድዩ ይሸሻል።
አሕመድ መሳሪውን ዝቅ ያደርግና እሱ ጥቃት አድራሽ አለመሆኑን ለመጠቆም አንድ እጁን ከፍ አድርጎ ለፖሊስ ጥቆማ ይሰጣል።
'አደጋን መጋፈጥ'
ይህ ጥቃት አድራሽ ወደ ድልድዩ ካፈገፈገ በኋላ ሌላ መሳሪያ አንስቶ የተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ሲተኩስ ታይቷል።
ሌላኛውም ጥቃት አድራሽ ከድልድዩ ላይ ሆኖ ሲተኩስ ነበር። ሁለቱ ግለሰቦች ማን እንደሆኑ ወይም ምን ላይ የጦር እንደሚተኩሱ ምሥሉ ላይ በግልፅ አይታይም።
ሰኞ ምሽት መግለጫ የሰጡት የኒው ሳውዝ ዌልስ ሀገረ ገዢ ክሪስ ሚንስ ለአሕመድ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።
"ይህ ግለሰብ የሚገርም ጀግና ነው። በእሱ ጀግንነት ምክንያት በርካታ ሰዎች በሕይወት መቆየታቸው ግልፅ ነው።"
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንተኒ አልባኒዝ "አውስትራሊያውን አደጋን ተጋፍጠው ሌሎች ለመርዳት ሲሯሯጡ ተመልክተናል" ብለዋል።
"እኒህ አውስትራሊያውን ጀግኖች ናቸው። የእነሱ ጀግንነት የብዙዎችን ሕይወት ታድጓል።"
በዋይት ሐውስ በተዘጋጀ የገና አከባበር ላይ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አሕመድን ያደነቁት ሲሆን ለእሱ "ትልቅ ክብር" እንዳላቸው ተናግረዋል።
"በጣም በጣም ጀግና ሰው ነው። ከጥቃት አድራሾቹ አንዱን ፊት ለፊት ተጋፍጦ የብዙዎችን ሕይወት አድኗል" ብለዋል።