ዩኬ እና ፈረንሳይ በሶሪያ በሚገኝ የአይኤስ የመሬት ውስጥ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ላይ ጥቃት ፈጸሙ

የጦር ጄት

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

የዩናይትድ ኪንግደም የሮያል አየር ኃይል ታይፎን ጄቶች ከፈረንሳይ አውሮፕላኖች ጋር በመጣመር ሶሪያ ውስጥ በሚገኝ እና በኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድን ጥቅም ላይ የሚውል የመሬት ውስጥ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ "ጥንቃቄ በተሞላበት" ሁኔታ የተካሄደ የስለላ ትንተና፤ ባለስልጣናት ስፍራው የጦር መሳሪያዎችን እና ፈንጂዎችን ለማከማቸት ይውላል የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው ገልጿል።

ጥቃቱ የተፈጸመው በመካከለኛው ሶሪያ በምትገኘው ጥንታዊቷ ፓልሚራ ከተማ በስተሰሜን በሚገኙ ተራሮች ላይ እንደሆነም መግለጫው ጠቅሷል።

መከላከያ ሚኒስቴር፤ "አውሮፕላኖቻችን ወደ ስፍራው የሚወስዱ በርካታ የመግቢያ ዋሻዎችን ለመምታት በ'ፔቭዌይ IV' የሚመሩ ቦምቦችን ተጠቅመዋል... የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎች ዒላማው በተሳካ ሁኔታ መመታቱን ያሳያሉ" ብሏል።

ቅዳሜ ምሽት በተፈጸመው ጥቃት በሲቪሎች ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት ስለመኖሩ ምልክት እንዳልታየ እና ሁሉም አውሮፕላኖች ያለጉዳት መመለሳቸውንም ሚኒስቴሩ አክሏል።

ጥቃቱ ስላደረሰው ጉዳት ዝርዝር ግምገማ እየተካሄደ ቢሆንም ባለሥልጣናት "ዒላማው በተሳካ ሁኔታ ተመትቷል" የሚል እምነት አላቸው። ጥቃቱን የፈጸሙት 'ታይፎን FGR4፤' አውሮፕላኖች ነዳጅ ጫኝ አውሮፕላን ድጋፍ እንተደረገላቸው ተገልጿል።

አይኤስ እስከ የአውሮፓውያኑ 2019 ድረስ በሶሪያ እና በኢራቅ አንዳንድ ክፍሎችን የጂሃዲስት አገዛዝ ሲመራ ነበር።

የዩኬ የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሊ፤ "ይህ እርምጃ የዩናይትድ ኪንግደምን መሪነት እና የትኛውንም የዳኢሽ ዳግም ማንሰራራት እንዲሁም አደገኛ የአመጽ ርዕዮተ ዓለማቸውን ከመካከለኛው ምስራቅ ለማጥፋት ከአጋሮቻችን ጋር ጎን ለጎን ለመቆም ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል" ብለዋል።

በ2019 በባጉዝ በተካሄደው ጦርነት የተሸፈው አይኤስ፤ ሊያደርግ የሚችለውን "ማንኛውንም ዳግም የማንሰራራት ሙከራ ለመከላከል" ሲባል የዩናይትድ ኪንግደም የሮያል አየር ኃይል አውሮፕላኖች በሶሪያ ሰማይ ላይ ቅኝት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ሚኒስትሯ ሄሊ አክለውም፤ "በዚህ ኦፕሬሽን ላይ ለተሳተፉት የመከላከያ ሠራዊታችን አባላት በሙሉ ላሳዩት ሙያዊ ብቃት እና ጀግንነት ላመሰግናቸው እወዳለሁ" ብለዋል።

የሮያል አየር ኃይል፤ አይኤስ ላይ ዘመቻ የሚያካሂደው የዓለም አቀፍ ጥምረት አካል በመሆን ከ2014 ጀምሮ የቡድኑ ተዋጊዎች እና ዒላማዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሰው አልባ ድሮኖችን እና በሰው የሚበርሩ አውሮፕላኖችን ሲጠቀም ቆይቷል

የተባበሩት መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው፤ አይኤስ አሁንም ሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ ከ5,000 እስከ 7,000 የሚደርሱ ተዋጊዎች አሉት። በአዲሱ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ የምትመራ ሶሪያ ባለፈው ህዳር አሜሪካ የሚመራውን ቡድኑን ለመዋጋት የተመሰረተ ጥምረት የተቀላቀለች 90ኛዋ አገር ሆናለች።

የጥምረቱ መሪዎች እንደሚናገሩት፤ ይህ ስብስብ ዓላማው ቀሪዎቹን የኢስላሚክ ስቴት አካላት ማጥፋት እና የውጭ ታጣቂዎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚያደርጉትን ፍሰት መግታት ነው።

ባለፈው ወር በፓልሚራ ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች እና አንድ ሲቪል አስተርጓሚ የተገደሉበት ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የአሜሪካ ጦር በሶሪያ በሚገኙ የአይኤስ ዒላማዎች ላይ "ከባድ ጥቃት" ሲል የጠራውን እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።