ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሴት ሥራ ፈጣሪዎች መብዛታቸው ሴቶች ሥራ እንዲያገኙ ወሳኝ ይሆን?
በቅርብ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን መደገፍ በርካታ ሴቶች ሥራ እንዲያገኙ ዕድል እንደሚፈጥር ይፋ አድርጓል።
በሴቶች የሚመሩ ሥራዎች መብዛታቸው በርካታ ሴቶች የቅጥር ዕድል እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ኃብት እድገትም ላይ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም።
የዓለም ሕዘብ ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች የሚመሯቸው ቢዝነሶች በቁጥር ከወንዶቹ በአንድ አምስተኛ ያነሱ ናቸው።
የዓለም ባንክ ይህንን ይፋ ያደረገው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት በ138 አገራት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ነው።
ጥናቱ አክሎም በሴቶች ባለቤትነት የተያዙ ቢዝነሶች ሴቶችን በመቅጠር ብቻ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በማነቃቃት ረገድ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሷል።
ወንዶች በሚያስተዳድሯቸው ተቋማት ውስጥ ሴት ተቀጣሪዎች 23 በመቶ ብቻ ሲሆኑ፣ በሴት ባለቤትነት በሚተዳደሩ ድርጅቶች ደግሞ ከዚህ ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ተቀጥረው ተገኝተዋል።
በወንድ ባለቤትነት ከተያዙ ድርጅቶች ውስጥ ደግሞ 6.5 በመቶ ያህሉ ብቻ ሴት አስተዳዳሪዎች ሲኖሯቸው፣ በሴት ባለቤትነት የተያዙ ተቋማት ውስጥ ግን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አለቆች ሴቶች ናቸው።
በሕንድ የሴቶች የጉልበት ተሳትፎ እና ሥራ ፈጠራ ዝቅተኛ ሲሆን፣ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በአጠቃላይ በሥራ ኃይል ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እምብዛም አልተለወጠም።
ነገር ግን ከሥራ ፈጠራ አንጻር ከታየ ያለው ሁኔታ በጥቂቱም ቢሆን የተሻለ ነው።
በሕንድ ሴቶች 14 በመቶ ያህሉ ሥራ ፈጣሪዎች ሲሆኑ በመካከለኛ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የጎላ ድርሻ አላቸው።
በአውሮፓውያኑ 2023 ይፋ በተደረገው የሕንድ የኑሮ ሁኔታ ሪፖርት መሠረት ሴቶች ለኢንዱስትሪ ምርት በተለይም ከፍተኛ የሰው ኃይል አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
ለመንግሥት የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን የሚያቀርበው ኒቲ አዮግ ያወጣው መረጃ በሕንድ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ መካከለኛ፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በሴቶች ባለቤትነት የተያዙ መሆናቸውን ያሳያል።
አንዳንድ በሴቶች ባለቤትነት የተያዙ ኢንተርፕራይዞች በብዛት ሠራተኞች ቢቀጥሩም፣ ብዙሃኑ የሚሠሩት ግን በጣም ጥቂት በሆኑ ሠራተኞች ነው።
ስለዚህ የሕንድ ሴቶች በሥራ ፈጣሪነት ዝቅተኛ ውክልና ነው ያላቸው ማለት ነው።
ከወንዶች ጋር ሲነጻጸሩም፣ በተለይም መደበኛ ባልሆነው ዘርፍ በጣም ያነሱ ድርጅቶችን ይመራሉ።
ይህ ከግምት ከገባ በሕንድ የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት የሴቶች አስተዋፅኦ 17 በመቶ ብቻ መሆኑ አያስደንቅም።
በፈረንጆቹ 2021 በወጣው የዓለም የሥራ ፈጠራ ማሳያ ሪፖርት መሰረት ሕንድ በሴቶች ሥራ ፈጣሪነት ከ65 አገራት 57ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በጋውራቭ ቺፕሉንካር (የቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ) እና ፒኔሎፒ ጎልድበርግ (ያሌ ዩኒቨርሲቲ) የተሰራ ጥናት የሴቶችን ሥራ ፈጣሪነት ማሳደግ የሴቶችን የሰው ኃይል ተሳትፎ በእጅጉ እንደሚያሳድግ ይሞግታል።
በሴት የሚመሩ የንግድ ሥራዎች ለሌሎች ሴቶች ብዙ ዕድል መፍጠራቸው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
ተመራማሪዎቹ በሕንድ ያሉ ሴቶች ወደ ሥራ ሲገቡ እና ሥራ ፈጣሪ በሚሆኑበት ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመለካት መስፈርቶችን አዘጋጅተዋል።
ሴት ሠራተኞች ሲቀጠሩ፣ እንዲሁም ንግዳቸውን ሠራተኛ በመቅጠር ሲያስፋፉ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠብቃቸው ደርሰውበታል።
የምርምር ሥራቸው ለሚታትሩ ሴቶች እንቅፋቶችን ማስወገድ በሴቶች ባለቤትነት ስር ያሉ የንግድ ስራዎችን እንዲሁም የሴቶችን የሥራ ተሳትፎ እንደሚያሳድግ እና ምጣኔ ኃብታዊ ትርፍን፣ ከፍተኛ ደሞዝ እንድያገኙ እንደሚያደርግ ጠቅሷል።
በወንድ ባለቤትነት የተያዙ እና አነስተኛ ትርፍ የሚያስገኙ ንግዶችን ውጤታማ በሆኑ የሴቶች ተቋማት በመተካት ለውጥ ማሳየት ማቻሉን ጥናቱ ያትታል።
ስለዚህ የሴት ሥራ ፈጣሪነትን የሚደግፉ ፖሊሲዎች ወሳኝ ናቸው ሲሉ የጥናት አቅራቢዎቹ ይከራከራሉ።
ሥራ ፈጣሪነትን እና የሰው ጉልበት ፍላጎትን የሚያሳድጉ ፖሊሲዎች፣ ብዙ ሴቶች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ መፍቀድ፣ የረዥም ጊዜ የማህበራዊ ደንቦችን ከመቀየር የበለጠ ውጤታማ እና ፈጣን ሊሆን ይችላል ይላሉ ቺፕሉንካር።
የአሾካ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት አሽዊኒ ዴሽፓንዴ “በታሪክ የኖሩ የማኅበረሰብ ደንቦች ጥብቅ መሆናቸውን ይነግረናል” ይላሉ።
ሴቶች አሁንም አብዛኛውን የቤት ውስጥ ኃላፊነቶች ምግብ ማብሰል፣ ጽዳት፣ ልብስ ማጠብ፣ የሕጻናት እና የአረጋውያን እንክብካቤ በጫንቃቸው ላይ እንደወደቁ ናቸው።
ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ የመጓጓዣ አገልግሎት አለመኖር እና የሕጻናት እንክብካቤ ራቅ ብለው ሄደው ሰርተው ለመምጣት አሁንም እንቅፋት እንደሆኑባቸው ነው።
በቅርቡ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሮሊ ካፑር የተመራው ጥናት እንደሚያሳየው ሴቶች ራሳቸውን ችለው ያለ ስጋት የመንቀሳቀስ አቅማቸው ውስን መሆኑ በሥራ ገበያ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የሚገድብ ቁልፍ ነገር ነው።
በሕንድ ሴቶች በሥራ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢያድግም ዴሽፓንዴ በጥናታቸው ላይ እንዳስቀመጡት ያን ያህል ተስፋ ሰጪ አይደለም ።
ምሁሩ በተጨማሪ ያገኙት ቢኖር፣ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው የሚሠሩ ሴቶች መጨመራቸውን፣ ፈጥጦ ያልወጣ ሥራ አጥነት መጨመሩን፣ ለአንድ ሥራ ከሚያስፈልገው በላይ ብዙ ሰዎች ተቀጥረው የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩን፣ ይህም ዝቅተኛ ምርታማነት እንዲኖር ማድረጉን ነው።
"ከሥራ ውሎች እና ከማኅበራዊ ዋስትና ጥቅማ ጥቅሞች ጋር መደበኛ ደመወዝ በሚከፈላቸው ሥራዎች ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ አስቸኳይና አስፈላጊ ነው። ይህ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጎልበት ብቸኛው ባይሆንም በጣም አስፈላጊው እርምጃ ነው" ሲሉ ዴሽፓንዴ ተናግረዋል።
ብዙ ሴቶች ሥራ ፈጣሪ መሆን ፈለጉም አልፈለጉም ከቤተሰብ እና ከማህበረሰቡ አሁንም እንቅፋት ይገጥማቸዋል።
በዚህ የተነሳ ብዙ ሴቶች ወደ ሠራተኛው ኃይል ቢቀላቀሉ እንኳ፣ በቂ ስራ ከሌለ፣ አሁንም የራሳቸውን የንግድ ሥራ ለመጀመር እንቅፋቶች በመኖራቸው የሚያገኙት ገቢ ሊቀንስ ይችላል።
በሕንድ ውስጥ ያሉ ሴቶች ሁኔታዎች ሲመቻቹላቸው ተግተው እንደሚሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ፤ ስለዚህ የሰው ኃይል ተሳትፎ መጠን እየቀነሰ የመጣው በቂ የሥራ እድል እና የሴቶች ጉልበት ፍላጎት በመቀነሱ ነው።
በቅርቡ ይፋ የሆነ የበርክሌይ አንድ ጥናት ሕንድ በ2030 ከአዲሱ የሰው ኃይል ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን ሴቶች እንዲሆኑ በማረጋገጥ ብቻ የአገር ውስጥ ምርቷን ዕድገት 8 በመቶ ልታደርስ ትችላለች።
የሴት ሥራ ፈጣሪነትን ማሳደግ መውጫ መንገድ ሊሆናት ይችላል።