የኢትዮጵያ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ ለሚካሄደው ድርድር የቀረበለትን ጥሪ ተቀበለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለሚካሄደው የሰላም ድርድር የቀረበለትን ግብዣ መቀበሉን አስታወቀ።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃት እንዲቻል የአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የትግራይ ኃይሎችን ድርድር እንዲጀምሩ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ነበር ጥሪ ያቀረበው።
መንግሥት በኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኩል የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ንግግሩን የሚመሩ አካላትን፣ ቀንና ስፍራን አሳውቆ የሰላም ውይይቱ እንዲጀመር ይፋዊ ጥሪ ማቅረቡን አረጋግጧል።
የአፍሪካ ኅብረት ግብዣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በፊት ያቀረባቸውን አቋሞች የጠበቁ ናቸው በማለት፤ ንግግሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲሆን እና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ መንግሥት አቋሙን ሲገልጽ መቆየቱን አመልክቷል።
ስለዚህም መንግሥት ግጭቱን ለመፍታት ሲወስዳቸው የቆዩትን ሁሉንም ዓይነት የመፍትሔ እርምጃዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ንግግር ጥሪውን መቀበሉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የድርድር ጥሪውን የተቀበለው “ግጭቱን በሰላም ለማብቃት እና ካለቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ካለው አቋም ጋር የሚጣጣም” በመሆኑ ነው ብለዋል።
በኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ተፈርሞ ቅዳሜ መስከረም 21/2015 ዓ.ም. በተጻፈው የንግግር የግብዣ ጥሪ ላይ የመጀመሪያ ደረጃው ንግግር በመጪው ቅዳሜ ወይም እሁድ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንደሚጀመር ይጠበቃል።
ቢቢሲ የተመለከተው ከአፍሪካ ኅብረት ተጽፏል የተባለው ደብዳቤ ድርድሩ የሚጀመርበት ቀንን በተመለከተ ስህተት እንዳለ ያሳያል። ደብዳቤው እሁድ መስከረም 28 የሚል ቢሆንም እሁድ ግን መስከረም 29 ነው።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በበኩሉ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች አረጋገጥኩ እንዳለው፣ የአፍሪካ ኅብረት ለህወሓት ሊቀ መንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የግብዣ ደብዳቤ መጻፉን ዘግቧል።
የዜና ወኪሉ ስለ ግባዣው የህወሓት ቃል አቀባይ ከሆኑት ከአቶ ጌታቸው ረዳ ማረጋገጫ ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ፣ በቅርቡ ይካሄዳል ስለሚባለው ንግግር የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል ብሏል።
በኅብረቱ ተጻፈ የተባለው ደብዳቤ እንደሚለው በሁለቱ ወገኖች መካከል ከቀናት በኋላ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ንግግር ለቀጣይ ድርድር አስፈላጊ በሆኑ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አመልክቷል።
የጦርነቱ መባባስን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካዩ አድርጎ ሰላም ለማውረድ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።
ከቀናት በኋላ ለማድረግ የታሰበው ይህ የሰላም ንግግር በኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የሚመራ ሲሆን፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ ሌሎች አሸማጋዮች እንደሚሳተፉበት ተነግሯል።
የአሜሪካ መልዕክተኛ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር ከሰኞ መስከረም 23/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አፍሪካ በመምጣት ሰላም እንዲወርድ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጹ ይታወሳል።
ልዩ መልዕክተኛው ከሚጎበኟቸው አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ስትሆን፣ ከሰኞ መስከረም 23 አስከ ጥቅምት 08/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ በሚኖራቸው ቆይታ ከየአገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።
ባለፈው መጋቢት ወር የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ጦርነት ፈርሶ በበርካታ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ውጊያዎች ከተቀሰቀሱ በኋላ፣ የአሁኑ የማይክ ሐመር ጉዞ ሁለተኛው ነው።
ከአንድ ወር በኋላ ሁለት ዓመት የሚሞላው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኝነት የሰየመቻቸው ሦስተኛው ዲፕሎማት የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ባለፉት አራት ወራት በአዲስ አበባ እና በመቀለ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር ተገናኝተዋል።
ከአንድ ወር በኋላ ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት
ግብ ብሎ የነበረው ጦርነት ማገርሸቱን ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ ጠይቀው፣ ውጥረቱን በማርገብ በተለይ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሁሉ እንዲደርስ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ይህ ጦርነት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱበት የሚታመን ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈጸሙ በተደጋጋሚ ሲከሰሱ የነበረ ሲሆን፣ በተጨማሪም ቁሳዊ ውድመትን ባስከተለው በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ነዋሪዎች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።
አስተማማኝ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ አሁንም ጦርነቶች እንደሚካሄዱ ከተለያዩ ምንጮች የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ከገለጹ ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ አስካሁን በይፋ ንግግር ጀምረው ተጨባጭ እርምጃዎች አልታዩም።
ይልቁንም ጋብ እያለ የሚቀሰቀሰው ጦርነት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን አለመረጋጋት በማባባስ ለነዋሪዎች መፈናቀል እና ለእንቅስቃሴዎች መስተጓጎል ምክንያት ሆኗል።












