የአሜሪካ እና የኢራን ከፍተኛ መሪዎች ሊወያዩ ነው

የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ እና የኢራን ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ በኦማን ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መቃረቡን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ወታደራዊ ግጭት ይነሳል የሚለው ውጥረት አሁንም እንዳለ ነው።

የሁለቱ አገራት ከፍተኛ መሪዎች የት ተገናኝተው፣ በምን ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ግልጽ አለመሆኑ ጥርጣሬ አጭሮ ነበር።

የቀጣናቸው አገራት ውጥረቱን ለማርገብ እየሞከሩ ሲሆን፤ ኢራን እና አሜሪካ እያራመዱ ያሉት አቋም ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑ ስጋቱን አባብሷል።

የዛሬው ውይይት ስኬታማ ከሆነ አገራቱ መደራደር የሚችሉባቸው ነጥቦች ላይ ይስማማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን እንድታቋርጥ የምትፈልገው አሜሪካ፤ አገሪቱ ያከማቸችውን ዩራንየም እንድታስወግድም ጠይቃለች።

የኢራን ባለስቲክ ሚሳዔል እና ለቀጣናው ታጣቂዎች የምታደርገው ድጋፍ የውይይቱ አካል እንዲሆን አሜሪካ ትፈልጋለች።

ኢራን የኃይል እርምጃ ከተወሰደ አጸፋውን እንደምትመልስ አስጠንቅቃለች። በመካከለኛው ምሥራቅ እና እስራኤል የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫዎች ላይ ጥቃት ልታደርስም ትችላለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ ጋር በሚደረገውን ውይይት የሚሳተፉ ልዑካንን ይመራሉ።

የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ ልጅ ባለቤት ጃሬድ ኩሽነር የአሜሪካ ልዑካንን ይመራሉ።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ወታደሮቻችን ቃታ ለመሳብ በተጠንቀቅ ቆመዋል" ብለዋል።

አምና እስራኤል እና ኢራን መዋጋታቸውን ተከትሎ የኢራን እና የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልናት ሲወያዩ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ያለፈው ሰኔ አሜሪካ የኢራን ሦስት የኒውክሌር ማብላያዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ኢራን ዩራንየም ማበልጸግ ማቆሟን አስታውቃለች።

የዛሬው ውይይት አሜሪካ ኢራን ላይ የቃጣችውን ጥቃት የምትቀለብስብት የመጨረሻ ዕድል ተደርጎ ተወስዷል።

የኢራን መንግሥት እንደ አውሮፓውያኑ በ1979 ሥልጣን ከያዘ ወዲህ እንደ አሁኑ ተዳክሞ እንደማያውቅ ተንታኞች ይገልጻሉ።

በምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ መንግሥት እንዲለወጥ ወደ መጠየቅ መሻገሩን ተለትሎ የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ መውሰዱ አይዘነጋም።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 6,883 እንደሆነ እና ከ50,000 በላይ ሰዎች እንደታሰሩ አስታውቀዋል።

ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለሰላማዊ ዓላማ እንደምታውል ብትገልጽም አሜሪካ እና እስራኤል የጦር መሣሪያ ግንባታ እንደሚከናወን በመግለጽ ተቃውሞ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ኢራን በግዛቷ ዩራንየም የማበልጸግ መብት እንዳላት እና ወደ 400 ኪሎግራም የሚመዝን የዩራንየም ክምችቷን ወደ ሦስተኛ አገር እንደማታዘዋውር ተናግራለች።

ቀጣናዊ የዩራንየም ማበልጸግ ስምምነት እንዲደረግ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል።

ኢራን በጋዛ ሐማስን፣ በሊባኖስ ሔዝቦላህን እንዲሁም የኢራቅ ታጣቂዎችንም ትደግፋለች። ይህንንም አሜሪካ እና እስራኤል ይቃወማሉ።