በመደፈር የተወለደው ሕንዳዊ እናቱ ፍትህ እንድታገኝ እየታገለ ነው

ሕንዳዊቷ ሴት በሁለት ወንድማማቾች ለወራት በተደጋጋሚ የተደፈረችው ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ነበር፤ ከዚህ ጥቃት የተወለደው ልጅም ከእዚህ ዓመታት በኋላ እናቱ ፍትህ እንድታገኝ እየጣረ ነው።

እናቲቱም በመጨረሻ ፍትህ ለማግኘት ተስፋ አድርጋለች።

በሰሜናዊው የኡታር ፕራዴሽ ግዛት ነዋሪ የሆነችው እናት፣ ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለች ነው በሁለት ወንድማማቾች ከስድስት ወራት በላይ በተደጋጋሚ የተደፈረችው።

በጥቃቱ የተወለደው ልጅም ወዲያውኑ በአራስነቱ ለማደጎ የተሰጠ ቢሆንም ዕድሜው 13 ሲሆነው ወደ እናቱ ተመለሰ።

በአሁኑ ወቅትም ከጎኗ ሆኖ ጥቃቱን በፈጸሙባት ወንድማማቾች ላይ ክስ እንድትመሰርት በዋነኝነት አበረታትቷል። ከጎኗም ሆኖ ለመፋለም ዝግጁ ነው።

ከአስር ቀናት በፊት ፖሊስ ከተከሳሾቹ አንዱን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን፣ ተከትሎም ሁለተኛው ተፈላጊ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሏል።

“ድርጊቱ ከተፈጸመ በርካታ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ቁስሉ አልሻረም፣ ጠባሳው አልተቀረፈም” ስትል ግለሰቧ ተናግራለች።

“ሕይወቴን ቀጥ ያደረገ እና ሕይወት እንዳይኖረኝ ያደረገ ድርጊት ነው የተፈጸመብኝ። ሁልጊዜም ያንን ክስተት በማስታወስ ወደ ኋላ እንደተመለስኩ ነው” ብላለች።

በሕንድ ውስጥ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የሕጻናት ወሲባዊ ጥቃቶች ሪፖርት ይደረጋሉ።

በሕንድ የሕጻናትን ወሲባዊ ጥቃቶች የሚከላከለው ተቋም (ፒኦሲኤስኦ) መሰረት በአውሮፓውያኑ 2020፣ 47 ሺህ ሕጻናት ወሲባዊ ጥቃቶች ተፈጽመውባቸዋል።

የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ይህ አሃዝ በሕንድ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት እንደማያሳይና በርካታ በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ሪፖርት እንደማይደረጉ ተጠቅሷል።

ለዚህም በዋነኝነት የሚጠቅሱት ምክንያቶች ሕጻናቱ ምን እንደተፈጸመባቸው አለመረዳታቸው ወይም ደግሞ ለመናገር በጣም ስለሚፈሩ ነው።

ቤተሰቦቻቸውም ቢሆኑ መገለል ይደርስብናል በሚል ወይም ጥቃት አድራሾቹን የሚያውቋቸው በመሆናቸው እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን ሪፖርት አያደርጉም።

“ሕይወቴን በሽብር ሞልተውታል”

በሕንድ ሕግ መሠረት ስሟ የማይገለጸው ይህች ግለሰብ የተደፈረችው በአውሮፓውያኑ 1994 በሻሃጃንፑር ከተማ ነው።

ወንድማማቾቹ መሐመድ ራዚና ናቂ ሃሰን ጎረቤቶቿ ሲሆኑ፣ አጥር እየዘለሉ ወደግቢያቸው በመግባት ብቻዋን በሆነችበት ጊዜ ለወራት በተደጋጋሚ ደፍረዋታል።

ጤናዋ እያሽቆለቆለ ሲሄድም እህቷ ወደ ሐኪም ዘንድ በወሰደቻት ጊዜ ማርገዟ ታወቀ። የነበረችበት የጤና ሁኔታ ደካማ እና ዕድሜዋም ሕጻን በመሆኑ ዶክተሩ ፅንስ ማቋረጥ እንደማይቻል ተናገረ። ሕጻኑም ከተወለደ በኋላ ወዲያውኑ ለማደጎ ተሰጠ።

“በእርግዝናዬ ወቅት ለዚህ ልጅ ብዙ ስቃይ አይቻለሁ። ነገር ግን እንደተወለደ ፊቱን እንኳን ለማየት ዕድል አላገኘሁም። እናቴን ስጠይቃት እንደገና ለመኖር ሁለተኛ ዕድል ታገኛለሽ አለችኝ” ብላለች።

ጥቃት የደረሰባት ታዳጊም ሆነ ቤተሰቧ ስለጥቃቱ ለፖሊስ ሪፖርት አላደረጉም፣ ምክንያቱም ጥቃት አድራሾቹን በመፍራታቸው ነበር።

“ስለመደፈሬ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን እንደሚገድሉና እና ቤታችንን እንደሚያቃጥሉ አስፈራሩኝ” ትላለች።

“ሳድግ ፖሊስ የመሆን ህልም ነበረኝ። ነገር ግን በእነዚያ ሁለት ወንዶች ምክንያት ህልሜ ጨለመ። በትምህርቴም መቀጠል አልቻልኩም” በማለት ግለሰቦቹ ያደረሱባትን የማይሽር ቁስል ታስረዳለች።

ይህንን አሰቃቂ ሁኔታም ለመርሳት ታዳጊዋ ከቤተሰቦቿ ጋር ሆነው ራምፑር ወደሚባል ግዛት ሄዱ።

በአውሮፓውያኑ 2000 ደግሞ አግብታ ሁለተኛ ልጅ ወለደች። ይህ አዲስ ምዕራፍ ያለፈውን ለመርሳት ይረዳኛል ብላ ተስፋ ብታደርግም፣ ባሏ ስለመደፈሯ ከስድስት ዓመት የጋብቻ ሕይወት በኋላ በመስማቱ ነገሮችን ቀየረ።

ለመደፈሯ ጥፋተኛ አደረጋት፤ በዚህም አላበቃም ከልጇ ጋር ከቤት አባረራት። እሷም ከእህቷ እና ከቤተሰቧ ጋር ለመኖር አቀናች። 

ልጇ እውነትን ፍለጋ የጀመረው መንገድ

በማደጎ ተሰጥቶ የነበረው የመጀመሪያ ልጇ በማንነቱ ምክንያት በርካታ መገለሎችን እንዲሁም መድሎዎች ደርሰውበታል።

በልጅነቱ ለማደጎ በተሰጠበት ወቅት ጎረቤቶቹ የአሳዳጊ ወላጆቹ ልጅ አለመሆኑን በተደጋጋሚ በመናገራቸውም የማደጎ ልጅ መሆኑን ማወቁንም እናቱ ትናገራለች።

አሳዳጊዎቹም ከ13 ዓመት በኋላ ልጁን ለእናቱ መለሱላት።

ከታዳጊነቱም ጀምሮ የአባቱን ማንነት አጥብቆ ይጠይቅ ነበር። የአባት ስምም ስላልተሰጠው ትምህርት ቤት ውስጥ እኩዮቹ ያሾፉበት ነበር።

እናቱን ስለወላጅ አባቱ ያለማቋረጥ ቢጠይቅም መልስ ባለማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ ያበሳጨው ነበር። ያለአባት (ስም አልባ) ሆኖ ሕይወቱን እንደማይቀጥልና የአባቱን ስም ካልገለጸለችለት ራሱን እንደሚያጠፋ ያስፈራራት ጀመር።

መጀመሪያ ላይ ይህንን ጥያቄ በመጠየቁ ትወቅሰው የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ ግን ተጸጽታ እውነታውን አረዳችው።

ልጁም ከመደናገጥ ይልቅ በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፋት ጀመር “ይህንን መታገል እንዳለባትና እነዚህን ግሰቦች ለፈጸሙት ጥቃት ተገቢውን ትምህርት ማግኘት እንዳለባቸው” ይነግራትም ነበር።

“ስለደረሰብሽ ጥቃት ከተናገርሽ ሌሎችም ሊናገሩ ይችላሉ። ይህም ክሳችንን ያጠናክረዋል፤ ጥቃት አድራሾቹም ይቀጣሉ። ማንም ሰው ወንጀል ከሠራ በኋላ ነጻ አይሆንም የሚልም መልዕክት ለማኅበረሰቡ ያስተላልፋል” በማለት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንድትወስደው ይወተውታት ጀመር።

ለፍትህ የሚደረግ ትግል

በልጇ ማበረታቻ፣ ግለሰቧ ጥቃቱ የደረሰባትን ስፍራ ሻህጃሃንፑርን ከሁለት ዓመት በፊት በድጋሚ ጎበኘች። ነገር ግን በተከሳሾቹ ላይ ክስ መክፈት ቀላል አልሆነም።

ፖሊሶች ጥቃቱ ከደረሰ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ ቅሬታዋን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጠበቃ አነጋገረች።

ጠበቃውም ቢሆን ወደ ሦስት አስርት ዓመታት የሚጠጋውን ጥቃት መታገል ፈታኝ እንደሆነ በመግለጽ መጀመሪያ ፈቃደኛ አልነበረም።

ልጅነቷን ያሳለፈችበት አካባቢ በማይታወቅ ሁኔታ ተለውጧል። ይኖሩበት የነበረውን ቤት ማግኘት አልቻለችም እንዲሁም ጥቃት አደራሾቹም ሊገኙ አልቻሉም።

“ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የኖርሽበትን እና የተደፈርሽበትን ስፍራ እንዴት ልታረጋግጭ ትችያለሽ” የጠበቃው ጥያቄ ነበር።

“ማስረጃውን እናመጣልሃለን ጉዳያችንን ብቻ ያዝ አልኩት” ትላለች ።

ጠበቃውም በሁለቱ ጥቃት አድራሾች ላይ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2021 በሻህጃሃንፑር ክስ አቀረቡ።

ፖሊሶችም ጥቃት አድራሾቹን ፈልጋ እንድታገኝ ጠየቁዋት።

“አገኘኋቸው እና በስልክ አነጋገርኳቸው። አወቁኝና ለምን እስካሁን እንዳልሞትኩ ጠየቁኝ። እኔም፣ መሞት የእናንተ ተራ ነው አልኳቸው” በማለት ታስረዳለች።

ማስረጃ እና እስር

ጥቃት አድራሾቹ ተፈልገው ቢገኙም ከወንጀሉ ጋር የሚያያይዛቸው ምንም ማስረጃ አልተገኘም። ሆኖም ፖሊስ ከወራት በፊት በተደረገው የዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ ማስረጃ መገኘቱን አስታወቀ።

“ይህ ክስ በፍጹም ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን ይዞ መጥቷል። ግለሰቧ ስትከስ ተደንቀንና ተገርመን ነበር። ልጁም ቀረበ፤ ይህንን ዕድል በመጠቀም የልጁን የዲኤንኤ ናሙና ወሰድን” ሲሉ የሻሃጃሃንፑር የፖሊስ ኃላፊ ኤስ አናናድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ላለፈው አንድ ዓመት ይህንን ክስ በዋነኝነት ሲመረምሩ የነበሩት ኢንስፔክተር ዳርመንድራ ኩማር ጉፕታ እንደተናገሩት “ከተከሳሾቹ ላይ የዲኤንኤ ናሙናዎችን ወስደን ምርመራ አደረግን። የአንደኛው ግለሰብ ዲኤንኤ ናሙና ከልጁ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ተገኘ” ብለዋል።

ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ያዋለውም ከሳምንታት በፊት ነው። ተከሳሾቹ ስለቀረበባቸው ክስ እስካሁን የሰጡት አስተያየት የለም።

ግለሰቧ የእሷ ታሪክ ሌሎችን በማነሳሳት የተፈጸመባቸውን ወንጀሎች ሪፖርት እንዲያደርጉ ምክንያት እንዲሆናቸው እንደምትፈልግ ተናግራለች።

“በርካቶች በዝምታ ተሸብበዋል። እኔም በዝምታ ሁሉን ይዤ ዕጣ ፈንታዬ መስሎኝ ነበር። ነገር ግን እንደዚህ የሚባል ነገር የለም። ማንም እኛ ባለፍንበት መንገድ እንዳያልፍ ወደ ፖሊስ መሄድ አለብን” ብላለች።

ልጇ በበኩሉ ጥቃት አድራሾቹ መያዛቸው እንዳስደሰተው ተናግሯል።