የፀጉር መርገፍ ሕክምና ወጪን ለመሸፈን የሚፈልጉት ፕሬዝዳንት

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የአገሪቱን ራሰ በራ ዜጎች ለመርዳት የሚያስችላቸውን ተልዕኮ ጀምረዋል።
አቋማቸው ደግሞ የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና መድህን ለፀጉር መርገፍ የሚያስፈልገውን የሕክምና ክፍያ መሸፈን እንዳለበት ይጠቁማል።
ፕሬዝዳንት ሊ ጃኤ ማዩንግ በተያዘው ሳምንት ሃሳቡን ለባለስልጣናት አቅርበዋል። ቀደም ሲል "ለውበት" ሲባል ይደረግ የነበረው የፀጉር መርገፍ ሕክምና አሁን ግን እንደ "የመኖር ጉዳይ" ሆኖ ይታያሉ ሲሉ ተከራክረዋል።
የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የጤና መድህን በሕክምና ምክንያት ለሚመጣ የፀጉር መርገፍ ሕክምና ወጪውን ይሸፍናል። የአንድን ሰው ሕይወት አደጋ ላይ የማይጥለውና በዘር የሚተላለፍ የፀጉር መርገፍ ያለበትን ሰው አያካትትም ሲሉ የጤና ሚኒስትሩ ጄንግ ኢዩን-ኪንግ ማክሰኞ ዕለት በተደረገው ስብሰባ ላይ ገልጸዋል።
"በዘር የሚተላለፍ በሽታን እንደ በሽታ መግለጽ ብቻ ነው?" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ጥያቄ አዘል ምላሽ ሰጠዋል።
የፕሬዝዳንቱ ሃሳብ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎላቸዋል። አንድ ተጠቃሚ "በታሪክ ውስጥ ምርጥ ፕሬዝዳንት" ሲል ጠርቷቸዋል።
ከሚኖረው ድጎማ የፀጉር መርገፍ ሕክምና ተጠቃሚ የሚሆኑትን ጨምሮ አንዳንዶች ሃሳቡ የተዋጠላቸው አይመስልም።
እርምጃው "የድምጽ ማግኛ ፖሊሲ ይመስላል" ሲል የፀጉር መርገፍ መድሃኒት የሚወስደው የ32 ዓመቱ ሶንግ ጂ-ሁን ገልጿል።
"ገንዘብ ለመቆጠብ ጥሩ ሃሳብ ቢመስልም በዓመት ከ200 ዶላር ያነሰ ነው የሚያስወጣው። ስለዚህ… ያን ያህል አስፈላጊ ነው?" ሲል አክሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የክርክሩ ክፍሎች
በጥብቅ የውበት ደረጃዎቿ በምትታወቀው በደቡብ ኮሪያ ራሰ በራነት በተለይ ለወጣቶች አሳሳቢ መገለልን ይዞ ይመጣል።
ባለፈው ዓመት በፀጉር መርገፍ ምክንያት ሆስፒታሎችን ከጎበኙት 240 ሺህ የአገሪቱ ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በ20ዎቹ ወይም በ30ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ ናቸው ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
"ፀጉር እየሸሸ በመሆኑ ፐርምም ሆነ ዋክስ በአግባቡ መጠቀም አልችልም" ሲል በሰሜን ቹንግቼንግ ግዛት የሚኖረው የ33 ዓመቱ ሊ ዎን-ዉ ገልጿል።
"ፀጉሬን እንደምፈልገው ማስዋብ ስላልቻልኩ ደግሞ የተዝረከረኩ እና ማራኪ ያለመሆን ስሜት ስለሚፈጥርብኝ በራስ መተማመኔን በእጅጉ ጎድቶታል።"
ለፀጉር መርገፍ ድጎማ እንዲኖር በመታሰቡ አመስግኖ "የጤና መድህን ፈንድ ፈተና እያጋጠመው እና በገንዘብ እየተቸገረ ነው" ሲል ገልጿል።
"ይህ ገንዘብ በቀላሉ ሊከፋፈል የሚችልበት ሁኔታ አይደለም" ብሏል።
ራሰ በራነት ደግሞ "የውበት ሐክምና" መሆኑን ጠቁሟል።
"የእርጅና ተፈጥሯዊ አካል እንጂ ሕመም ወይም በሽታ አይደለም። የስሜታዊ ሕመሙን ብረዳውም ግን እውነታውን አይለውጠውም" ብሏል።
ባለፈው ዓመት 7.7 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት ያጋጠመው የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ የጤና መድህን ፈንድ በእድሜ በገፉ የአገሪቱ ሕዝቦች ምክንያት የበለጠ ጫና ውስጥ እንደሚገባ ይጠበቃል።
ለፀጉር ሕክምና የሚወጣው ወጪ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ ባለሥልጣናት ገደቦችን ሊጥሉ እንደሚችሉ ፕሬዝዳንት ሊ ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
አንዳንድ ተቺዎች ግን ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የኅብረተሰብ አካላትን በመርዳት ላይ መተኮር እንዳለበት ይከራከራሉ።
የኮሪያ የሕክምና ማህበር ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የመንግሥት አቅጣጫ ከፀጉር መርገፍ በፊት ለከባድ በሽታዎች ቅድሚያ መስጠት አለበት ብሏል። የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም በተመሳሳይ በደቡብ ኮሪያ የተስፋፋውን እንደራስን የማጥፋት መጠን እና ሴቶች የሚያጋጥሟቸውን ጥላቻ የመሳሰሉ ትላልቅ ማህበራዊ ችግሮችን እንዲመለከት ጠይቀዋል።
"የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ፓዶችን ለመሸፈን ወይም በብሔራዊ የጤና መድህን ስር የጡት ካንሰር መድሃኒቶች ሲኖሩ ሰዎች በንዴት እና በድንጋጤ ምላሽ በሚሰጡበት አገር ውስጥ የፀጉር መርገፍ መድሃኒቶች በጤና መድን እንደሚሸፈኑ ማወጅ እንደ መጥፎ ቀልድ ይቆጠራል" ሲል አንድ ግለሰብ ኤክስ ላይ ጽፏል።
"የፀጉር መርገፍ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖርን ኅልውና የሚወስን ነገር ከሆነ ማኅበረሰቡን መቀየር ነው። ይህ ደግሞ የፖለቲከኞች ሚና መሆን አለበት" ሲል ሌላ ግለሰብ ጽፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሊ ሃሳብ ጥንስስ
የፀጉር መርገፍ ሕክምናን ለማረጋገጥ የቀረበውን ሃሳብ ሊ ማቅረብ የጀመሩት በ2022 ፕሬዚዳንታዊ ዘመቻ ወቅት ነበር።
በወቅቱ ሊ እና አጋሮቻቸው የፀጉር መርገፍ ካጋጠማቸው ሰዎች አስተያየት ከመሰብሰብ ባለፈ የፀጉር መርገፍ ማስታወቂያ ላይ ጭምር መሳተፋቸው በአንዳንድ መራጮች ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎላቸው ነበር።
ተቺዎች ግን ሊ ወጣት ወንድ መራጮችን ለመሳብ ተጠቅመውበታል ብለው ከሰዋቸዋል። እነዚህም ወጣት ወንድ መራጮች ተቀናቃኛቸው የሚያራምዱትን በፀረ-ፌምኒዝም በብዛት ይደግፉ ነበር።
ሊ እአአ በ2022 ምርጫ ተሸነፉ። በዚህ ዓመት እንደገና ተወዳድረው አሸነፉ። ስለፀጉር መርገፍ ሕክምና ያላቸው ሃሳብ ከቀደመው የምርጫ ቅስቀሳቸው የመጣ ነው።
"በቀደመው ቃላቸው የመገኘት ኃላፊነት የለባቸውም" ይላሉ በኮሪያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶን ኤስ ሊ። ፕሬዝዳንቱ በ2026 አጋማሽ ለሚካሄደው የአካባቢያዊ ምርጫ "የደጋፊዎቻቸውን መሰረት ለማስፋት" እየሞከሩ ሊሆን እንደሚችልም አክለዋል።
ሊ ፕሬዝዳንት ከሆኑ ጀምሮ በአገሪቱ ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገዋል። አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ወጣቶች ከፍተኛ ውድድር እና ተስፋ አስቆራጭ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይገጥማቸዋል።
ሊ ከዚህ ተጨማሪም የውፍረት መድሃኒቶችን ወደ ብሔራዊ የጤና መድህን መርሃ ግብር ለማስገባትም ሃሳብ አቅርበዋል። ጥቅሞቹ ለፍላጎታቸው ተስማሚ ባለመሆናቸው ምክንያት ወጣቶች ከመርሃ ግብሩ "ይበልጥ የመገለል ስሜት" ይሰማቸዋል።
የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ሊ ግን ፕሬዝዳንቱ የፀጉር መርገፍ ሕክምናን በብሔራዊ የጤና መድህን ሽፋን እንዲካተት ለማድረግ ከባድ በመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው።
"በግሌ ፕሬዝዳንት ሊ ይህንን ጉዳይ ቀጥለው እና ተጨማሪ እርምጃ ይወስዳሉ ለማለት እጠራጠራለሁ" ብለዋል።
"ወጣት ወንድ መራጮችን ዒላማ ያደረገ በጣም ስትራቴጂካዊ የሆነ 'እኔም ስለእናንተ አስባለሁ' የሚል ምልክት ነው።"















