አሜሪካ በአፍሪካ ግዙፍ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ ከቻይና የበለጠችው እንዴት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Trinity Metals
ይህን ጽሑፍ የምታነቡበት መሳሪያ ደኅና እስከሆነ እና እስካልተበላሸ ድረስ ከምን እንደተሠራ ቅንጣት ሀሳብ ላይገባችሁ ይችላል።
ነገር ግን መሣሪያውን ኃይል የሚሰጠው እና እንዲሰራ የሚያደርገው ቁስ በዓለማችን ሁለት ግዙፍ የምጣኔ ኃብት ባለቤቶች፣ አሜሪካ እና ቻይና እየተባባሰ ላለ ትግል ዋና መንስኤ ነው። የአፍሪካ አገራት ደግሞ መወዛገቢያዎቹ ናቸው።
የአፍሪካ አህጉር በማዕድን የበለፀገ ሲሆን፤ ለግል ጥቅም የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመሥራት መሠረታዊ የሆኑትን እንደ ሊቲየም፣ ኮቦልት እና ተንግስተን የመሰሉ ልዩ የብረት ማዕድናት ባለቤት ነው።
እነዚህ ቁሶች ደግሞ ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጀምሮ የኤአይ የመረጃ ቋት ማዕከላት እና የጦር መሳሪያ ስርዓቶችን ለመገንባት ወሳኝ ናቸው።
ቻይና ለረዥም ዘመናት የወሳኝ ማዕድናት እና ብረቶች ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ወሳኝ ናት። በተለይም በአፍሪካ ያፈሰሰችው ግዙፍ መዋዕለ ነዋይ በአገር ውስጥ ያላትን ክምችት ጠብቃ እንደትቆይ እና ከውጭ አገር በምታገኘው ማዕድን ፋብሪካዎቿን እንድታንቀሳቅስ አግዟታል።
በዓለም ቁሳቁሶች አቅርቦትም ቢሆን ቤጂንግ ትልቅ አቅም መገንባት የቻለች ሲሆን፤ ይህም የውጭ ንግዷን ለመገደብ አሜሪካ እንድትዝት አድርጓል።
ከዚህ ባሻገር አሜሪካ ወሳኝ የማዕድናትን እና ብረቶች ተደራሽነትን ለመጨመር የአፍሪካ ክምችት ላይ ዓይኗን ጥላለች።
በቅርብ የወጡ ዓመታዊ አሀዞች እንደሚያሳዩት አሜሪካ ድምጿን አጥፍታ በአፍሪካ ትልቋ መዋዕለ ነዋይ አፍሳሽ የነበረችውን ቻይናን በልጣለች።
እ.አ.አ በ2023 አሜሪካ 7.8 ቢሊዮን ዶላር በመላው አፍሪካ አፍስሳለች። ቻይና ደግሞ 4 ቢሊዮን ዶላር ማፍሰሷን በጆን ሀፒኪንስ ዩኒቨርስቲ የቻይና አፍሪካ ምርምር ተቋም መረጃ ያመላክታል።
አሜሪካ እ.አ.አ ከ2012 ወዲህ የመሪነት ሚናን ስትይዝ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ይህ የአሜሪካ መዋዕለ ነዋይ 'የአሜሪካ ኢንተርናሽናል ዴቬሎፕመንት ፋይናንስ ኮኦፖሬሽን' (ዲኤፍሲ) በተባለ የመንግሥት ተቋም የሚመራ ነው።
በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በ2019 ይፋ የሆነው ተቋሙ፤ ተልዕኮው ቤጂንግን መቅደም መሆኑን ከመግለፅ ወደ ኋላ አይልም። ድርጅቱ በድረ ገፁ የተመሰረተው "በስልታዊ ቀጠናዎች የቻይናን እንቅስቃሴ ለመመከት" እንደሆነ ያትታል።
ይህ መዋዕለ ነዋይ ለአፍሪካ ተቋማት ምን ማለት ነው? ተጠቃሚዎቹ አገራትስ እነማን ናቸው?
ባለፈው ዓመት የሩዋንዳው የማዕድን ኩባንያ 'ትሪኒቲ ሜታልስ' በአገሪቱ ያሉትን ሦስት የማዕድን ማውጫዎችን እንዲያለማ ከዲኤፍሲ የ3.9 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ወስዷል። ኩባንያው ቆርቆሮ፣ ታንታለም እና ተንግስተን ማዕድናትን ያመርታል።
የኩባንያው ሊቀ መንበር ሿን ማክኮርሚክ "የአሜሪካ መንግሥት ወደ አሜሪካ ቀጥታ የአቅርቦት ሰንሰለት ለመፍጠር እየሰራነው ያለውን ስራ በጣም እየደገፈን ነው" ይላሉ።
ትሪኒቲ አሁን ከሩዋንዳ በቀጥታ ተንገስተን የተባለውን ማዕድን ለማቀነባበሪያ ፋብሪካ ወደ ፔንሴቬንያ ይልካል። ከዚህ ባሻገርም ቆርቆሮን ከሩዋንዳ ለፔንሴቬንያ አቅላጮች ለመላክ ስምምነት ፈርሟል።
የትሪኒቲ ኩባንያ ሊቀ መንበር ከዋሽንግተን የተቀበሉት እርዳታ ኩባንያው ወደ አሜሪካ ማዕድናትን እንዲሉክ ተፅዕኖ አሳድሮበታል የሚለውን ሀሳብ ያስተባብላሉ።
"ዋና ስራ አስፈፃሚውን እና እኔን 'ተንገስተን ወደ አሜሪካ ልትልኩ ትችላላችሁ?' ያለን የአሜሪካ መንግሥት አይደለም። እንደ ንግድ ገበያው ተጨዋችነታችን የራሳችን ውሳኔ ነው።"
ትሪኒቲ አምስት በመቶው በሩዋንዳ መንግሥት ባለቤትነት የተያዘ ሲሆን፤ ቴክሜት የተባለው የአየርላንድ የወሳኝ ማዕድናት ኩባንያም ድርሻ አለው።
የትሪኒቲ ኩባንያ ሊቀ መንበር ሿን ማክኮርሚክ በአፍሪካ የማዕድን ማውጫዎች ያልሰለጠኑ ሠራተኞችን በአደጋ ሁኔታ ውስጥ ቢጠቀሙም ኩባንያቸው ግን ከፍተኛውን ደረጃ ይከተላል ብለዋል።
"ከግጭት ነፃ፣ ከሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ውጭ፣ በሙያዊ ክህሎት እና ታክስ በመክፈል እና ማኅበረሰቡን እና መንግሥትን በማክበር፣ ሥራ እና ዕድል በመፍጠር ማዕድናትን ማምረት እንደሚቻል አሳይተናል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ስፎ ሃማምቦ በናምቢያ የኤፍኤንቢ የባንክ ቡድን የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ናቸው። የአፍሪካ አገራት ከአሜሪካ ድርጅቶች ጋር ሲደራደሩ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ቆራጥ መሆን እንዳለባቸው እና ውለታ እንዳይጠብቁ ምክራቸውን ይሰጣሉ።
"[አሜሪካውያኖች] በአፍሪካውያን ስም ለአፍሪካ ጥቅም ተደራድረው እና ምክረ ሀሳብ ያቀርባሉ ብሎ መጠበቅ ከእውነታው ያፈነገጠ ነው" የሚሉት ባለሙያዋ፤ "ስለዚህ አፍሪካ ለእነዚህ ንግግሮች ራሷን ማዘጋጀት አለባት እና ምን እንደምትፈልግ በግልፅ ማሳወቅ አለባት" ይላሉ።
የአፍሪካ መንግሥታት ለማዕድናት ስምምነት አነስተኛ ጥሬ ገንዘብ ከመቀበል መሻገር አለባቸውም ይላሉ። "በአንፃሩ የተለያዩ ማዕቀፎች ለማማተር ዕድሎች አሉ" ሲሉ ያክላሉ።
"የማምረት አጋርነት ስምምነቶችን፣ የሽርክና፣ የሀብት ተሳትፎ ልትመለከት ትችላለህ። በስተመጨረሻም ለአፍሪካ አገራት ምናልባት ትምህርት እና ጤና ልማት ላይ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለመፍጠር እድል ይሰጣል" ይላሉ።
ባለሙያዋ ወደ ውጭ በቀላሉ ከመላክ ይልቅ በአፍሪካ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ የማዕድናት ማቀነባበሪያዎችን ከዚህ በላይ ማየት እንደሚሹ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Sepo Haimambo
በአፍሪካ የወሳኝ ማዕድናት እና ብረት ማጣሪያ ፋብሪካ እየገነባ ያለው የአሜሪካ ኩባንያ 'ሪኢለመንት አፍሪካ' ነው። ኩባንያው በደቡብ አፍሪካ ጉተንግ ግዛት ማቀነባበሪያ እየገነባ ነው።
የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቤን ኪንኬድ "ከማዕድን ማውጫ ፕሮጄክቱ ጎን ለጎን ማቀነባበሪያ ለመገንባት ከአፍሪካ አገራት ጋር በአጋርነት መስራት እንደምንችል መገንዘባችን ደስ የሚል ነው። ስለዚህ ትልቅ ዋጋ ለማግኘት፣ ሠራተኞችን ለማሰልጠን፣ በአካባቢው ምጣኔ ሐብት ለመገንባት እና ለቀጣይ የኢንዱስትሪ ልማት መሠረቱን ለመጣል" ብለዋል።
ፒትስበርግ በሚገኘው ካኒጊ ሜለን ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሐብት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሊ ባርነስተር አሜሪካ ዕድሏ አምልጧታል ይላሉ።
ከሳህራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የቻይና መዋዕለ ነዋይ መሬት ላይ ያለውን ሕዝብ አይጠቅምም የሚል ቅሬታ ባላበት ወቅት የፕሬዝዳንት ትራምፕ የጣሉት የንግድ ታሪፍ አሜሪካ በአህጉሪቱ እንድትንቀሳቀስ መነሳሳቱን ቀንሷል ሲሉ ይከራከራሉ።
"የአሁኑ አስተዳደር ማንንም ሳይለይ በርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ ያለ ምክንያት ታሪፍ ባይጥል ኖሮ አሜሪካ ምናልባትም በቻይና ፕሮጄክቶች ቅር የተሰኙ አፍሪካዊያንን ለመጠቀም የተሻለ አቋም ይኖራት ነበር" ይላሉ።
ከዚህ በኋላ አሜሪካ እና ቻይና በአፍሪካ ከሌሎች ፉክክር ሊገጥማቸው እንደሚችል የምጣኔ ሐብት ባለሙያዋ ስፎ ሃማምቦ ይናገራሉ። ብራዚል፣ ሕንድ እና ጃፓን በአፍሪካ ያላቸው ፍላጎት መጨመሩን ለአብነት ያነሳሉ።















