“እንደ መንግሥት አጋቾች ሲወስዱኝ ምንም ያላደረግክልኝ፤ እንድመርጥህ ትፈልጋለህ?”

ለበርካታ የሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ ነዋሪዎች ዋነኛ ፍራቻቸው መታገት፣ መጠለፍ ነው።
በዚህ አካባቢ ብዙዎች ታግተው ካሳ ተጠይቆባቸው፣ ያልከፈሉ ሕይወታቸው ተቀጥፏል።
ለዚያም ነው በታጠቁ ሰዎች መታገት የየዕለት ፍራቻቸው የሆነው።
በዚያ ፍራቻ መኖር የታከታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጨርቄን፣ ማቄን ሳይሉ ቀያቸውን ለቀው ተሰደዋል።
አካባቢው አገሪቷ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በምታደርገው ምርጫ ከፍተኛ መራጭ የተመዘገገበት ቢሆንም፣ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መራጮች እንደማይሳተፉ ይጠበቃል።
በሰሜን ናይጄሪያ ከሚገኙ የገጠር አካባቢዎች መካከል ካትሲና አንዷ ናት።
መንገድ በትክክል ያልተነጠፈላት የዚህች አካባቢ ማኅበረሰብ አብዛኛው አርሶ አደር ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በናይጄሪያ ውስጥ ትርፋማ ከሚባሉት እና ገንዘብ ለማግኘት የማገትና የመጥለፍ ወንጀል ይፈጠራል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።
ነገር ግን ከጥቂት ወራት በፊት በሞተር ሳይክል የተጫኑ ታጣቂዎች 57 የአካባቢውን ነዋሪዎች አገቱ።
“ባለቤቴን ለ38 ቀናት ያህል አገቷት” በማለት አብዱልጃባራ መሐመድ ይናገራል።
አብዱልጃባራ የመንግሥት ሠራተኛ እና በገንዘብም ጥሩ አቅም አላቸው ከሚባሉ ነዋሪዎች አንዱ ሲሆን፣ ሚስቱንም ለማስለቀቅ 1 ሚሊዮን ናይራ [የናይጄሪያ ገንዘብ] ወይም 2 ሺህ 100 ዶላር ማስለቀቂያ መክፈል ነበረበት።
“ያለኝን ገንዘብ፣ ሞተር ሳይክሌን ሰጥቼ እንዳይወስዱኝ ተማጸንኳቸው” ስትል የ30 ዓመቷ ዛራዲን ሙሳ ተናግራለች።
የታጠቁት ሽፍቶች ቤቷ የመጡት ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ነበር፤ ፖሊስ ቢጠራም ለሰዓታት ሊደርስላቸው አልቻሉም።
ሌላኛዋ ግለሰብ ማሪያ ሳኒ በታጣቂዎቹ ብትያዝም ታጋቾቹን ወደ ጫካ እየወሰዷቸው በነበረበት ወቅት ልታመልጥ ችላለች።
ዕድለኛ ሆና ባታመልጥ ኖሮ እንደ ሌሎች ታጋቾች ማስለቀቂያ ክፈይ ብትባል ምን ይውጣት እንደነበር ማሰብ ይከብዳታል።
የታገቱት ግለሰቦች ለወራት ያህል ድርድር ተደርጎ ሞተር ሳይክል፣ ውድ ጌጦች ወይም ያለቻቸውን ገንዘብ ከፍለው ነው የተለቀቀቁት።
ይህም እገታ እና ጠለፋ በናይጄሪያ ምን ያህል እንደተስፋፋ፣ የድሃ ድሃም እንኳን ቢኮን ከእገታው እንደማይተረፍ ፍንትው አድርጎ ያሳየ እውነታ ነው።
በባኪያዋ መንደር ያሉ ታጋቾች ዕድለኞች ነበሩ፤ ምክንያቱም በርካቶች ሕይወታቸውን ስለሚያጡ። ከአንድ ሳምንት በፊት በካትሲና ግዛት ሌላኛዋ ክፍል 100 ያህል አርሶ አደሮች በታጣቂዎች ተገድለዋል።
በሰሜን ምዕራብ ያሉ ታጣቂዎች እና በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ የሚገኙ ተገንጣዮች አገሪቷ ልታደርገው ያሰበችው ምርጫ ስጋት እንደደቀነ ተንታኞች ይናገራሉ።
አገሪቷ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2019 በነበረው ምርጫ ላይ በምርጫ ኮሚሽን ቢሮዎች ላይ በደረሰው ጥቃት ምርጫው ለአንድ ሳምንት እንዲራዘም ምክንያት ሆኗል።
በቅርቡም በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የኮሚሽኑ አንደኛው ቢሮ መቃጠሉን ተከትሎ ምርጫው ሊራዘም ይችላል የሚል ስጋት ቢፈጠርም ባለሥልጣናቱ ግን እንደማይዘገይ በአጽንኦት አረጋግጧል።
ኮሚሽኑ በታኅሣሥ ወር ላይ በካትሲና ግዛት በአንዳንድ አካባቢዎች ምርጫውን ማካሄድ አደገኛ መሆኑን ቢያሳውቅም እስካሁን ውሳኔ አላገኘም።
የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ቺዲ ኦዲንካሉ በግዛቶቹ ያለው የፀጥታ ችግር ምርጫውን የሚያደናቅፍ ከሆነ ሌላ አደጋ እንደሆነ ያምናሉ።
ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደ ኢሞ፣ አናምብራ፣ ሌጎስ እና ሪቨርስ ባሉ የአገሪቷ ደቡባዊ ግዛቶች ሁከት ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት በርካቶ ከምርጫ ጣቢያዎች ይርቁ ነበር።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተንሰራፋው የታጣቂዎች እገታ መጨመር ለበርካቶች ምርጫው ላይ ያላቸው ተስፋ የመነመነ እና እርባና ቢስ አድርጎታል።
“አጋቾች ሲወስዱኝ ምንም አላደረክልኝም፤ አሁን ደግሞ እንድመርጥህ ትፈልጋለህ” ስትል ሳኒ ትጠይቃለች።
ከዚህ ቀደም አገሪቷ እየመሩ ላሉት ሙሐማዱ ቡሃሪ ብትመርጥም በዘንድሮው ምርጫ ግን አትሳተፍም።
የሁለተኛ የምርጫ ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት ፕሬዚዳንት ቡሃሪ በዘንድሮው ምርጫ አይወዳደሩም፤ ከሥልጣናቸውም ይለቃሉ።
ገዢውን ፓርቲ ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ (ኤፒሲ) ፓርቲን በመወከል ቦላ ኢኒዩ ይወዳደራሉ።
“እነዚህን ሁሉ ሰቆቃዎች እና ጭቆናዎች አይተን ለገዢው ፓርቲ ኤፒሲ ድምጽ መስጠት ይቻላል?” በማለት የቀድሞ የፓርቲው አባል እና በአሁኑ ወቅት በመንደሪቷ ሌበር ፓርቲን ወክለው የሚወደዳሩት ተወካይ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩት ላዋል ሱሌይማን ተናግረዋል።
በባኪያዋ ውስጥ ያሉ በርካቶች ድምጻቸውን ከሰጡ ለዋናው ተቃዋሚ ፒፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ፒዲፒን) እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል።
“ፕሬዚዳንት ቡሃሪ የዚህችን አገር ችግር መፍታት ካልቻለ ሌላ ማንም አይችልም” በማለት ከሦስት ዓመታት በፊት በታጣቂ ቡድኖች በደረሰ ጥቃት መንደሯን የለቀቀችው ናና ሳማኢላ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሴት ልጇ አይሻ ማማ እንዲሁ በቅርብ ጊዜ ከባለቤቷ ጋር ከዳንግያ መንደር ሸሽታ የሄደችው በምሽት የሚፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ለሳምንታት በእርሻቸው ውስጥ እንዲደበቁ ካስገደዳቸው በኋላ ነው።
የቀድሞው ወታደራዊ ገዢ እና ትውልዳቸው ከዚሁ አካባቢ የሆኑት ፕሬዚዳንት ቡሃሪ በርካታ ችግሮችን ይፈታሉ በሚል እንደመረጠቻቸው የምትናገረው ሳማይላ በበኩሉ፣ በዚህ መንግሥት ውድቀት ተስፋ መቁረጧን ትናገራለች።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ተማሪዎች ታግተው የተለቀቁ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት የግዛቲቷ አስተዳር ራሳቸውን ከሽፍቶች ለመከላከል ለነዋሪዎች ታጠቁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምርጫው ተፎካካሪ የሆኑት ዕጩዎች በአካባቢው ካለው የፀጥታ ችግር በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ፈተና የሆነውን የምግብ ዋጋ ንረት እና የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩን ተረድተዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው የፖሊስ እና ፀጥታ፣ የደኅንነቱ እና ወታደራዊ ማሻሻያዎች እንዲሁም ሌሎች ማሻሻያዎች በማቅረብ ላይ ናቸው።
ሆኖም ተቃዋሚዎቹ እየገቡት ያለው ቃል በሰሜን ምሥራቅ እስላማዊ ቡድኖችን አጠፋለሁ በሚለው ቅስቀሳቸው ከተመረጡት ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ጋር ተመሳሳይ ነው። ፕሬዚዳንቱ በባለፉት ዓመታት ስኬታማ አልሆኑም።
በርካቶችም አገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ከተዋታል እንዲሁም አለመረጋጋቱም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ሲሉ ይከሷቸዋል።
ካኖ፣ ካትሲና እና ካዱና የተባሉት የናይጄሪያ ግዛቶች በናይጄሪያ ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ቁልፍ ስፍራ አላቸው።
ለዚህም ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና መራጭ ቁጥር ስላላቸው ነው።
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ በሦስት ግዛቶች ያሉ መራጮችም ናቸው በሁለቱ ምርጫዎች እንዲያሸንፉ የረዷቸው።
በግዛቶቹ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ገዢውን ፓርቲ ቢደግፉም፣ በርካቶች ግን ለፓርቲው ያላቸውን ተቃውሞ በግልጽ እያሳዩ ነው።
ለዚህም ማሳያው ከሁለት ሳምንታት በፊት ፕሬዝዳንቱ የካኖ ግዛትን በጎበኙበት ወቅት በሄሊኮፕተራቸው ላይ ድንጋይ ተወርውሮባቸዋል።
በእነዚህም ግዛቶች ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ድጋፍ እያገኙ ነው። በተለይም የኒው ናይጄሪያ ፒፕልስ ፓርቲ መሪው ራቢዩ ኳንሰን ዋነኛው ነው።
በተለይም ግዛቶቹን የሚያገናኘው እና በቅርቡ እንደገና የተከፈተው የካዱና አቡካ ባቡር ጣቢያ ታጣቂዎች መንገደኞችን ማገትና መግደላቸውን ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች ገዢውን ፓርቲ እያማረሩ ይገኛል።
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ይህንን መንገድ መርቀው ሲከፍቱ በሰሜናዊቷ የአገሪቱ ክፍል የብልጽግና እና የልማት ምልክት ተደርጎ ቢወሰድም በአሁኑ ወቅት እሱ ሁሉ ተቀይሮ የሁከት ተምሳሌት ሆኗል።












