“የመጨረሻ ውሳኔዬ ነው” የአሜሪካውን ኢንተር ማያሚ የተቀላቀለው ሊዮኔል ሜሲ

አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አርጀንቲናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ የአሜሪካውን ኢንተር ማያሚ ክለብ መቀላቀሉን ይፋ አድርጓል።

ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ ጋር የነበረውን ውል የጨረሰው ሜሲ ወደ ሜጀር ሊግ ሶከር ይሄዳል።

የ35 ዓመቱ ሜሲ ከሳዑዲ አራቢያው አል-ሂላል ምራቅ የሚያስውጥ ገንዘብ ቢቀርብለትም ወደ አሜሪካ መሄድን መርጧል።

ሜሲ፤ ወደ ባርሴሎና እንዳይመለስ ፍትሐዊ የገንዘብ አጠቃቀም አሊያም ኤፍኤፍፒ የተባለው ሕግ ደንቃራ ሆኖበታል።

“የመጨረሳ ወሳኔዬ ነው። ወደ ማያሚ ልሄድ ነው” ሲል ዲያሪዮ ስፖርትና ሙንዶ ዲፖርቲቮ ለተባሉ ጋዜጦች ተናግሯል።

“አውሮፓን ለመልቀቅ ወስኛለሁ።”

ሜሲ ጨምሮ “ሌላ የአውሮፓ ክለብ ላስፈርምህ ብሎኛል። ነገር ግን እኔ አውሮፓ የምቆይ ከሆነ ለባርሴሎና ብቻ ነበር መጫወት የምፈልገው” ብሏል።

“የዓለም ዋንጫን ካሸነፍሁ በኋላ ወደ ባርሴሎና መሄድ አለመቻሌ ወደ ኤምኤልኤስ መጥቼ እግር ኳስ ለየት ባለ መልኩ እንዳጣጥምና ዘና ብዬ ብዬ ሕይወቴን እንድገፋ ያስችለኛል።”

ሜሲ እንደሚለው “ኃላፊነቴ ተመሳሳይ ቢሆንም የማሸነፍ ፍላጎቴ ባይገታም ነገሮችን በረጋ ሁኔታ እንዳካሂድ ያግዘኛል።”

የቀድሞው የባርሴሎና ተጫዋች ወደ ካታላኑ ክለብ መመለስ ቢሻም ባርሴሎና በገባበት የገንዘብ ቀውስ ምክንያት ሁኔታዎች ተወሳስበዋል።

የስፔኑ ክለብ በ2021 ሜሲን ማቆየት ባለመቻሉ ተጫዋቹ እምባ እየተናነቀው ካምፑን ለቆ ወደ ፒኤስጂ አቅንቶ ነበር።

“ወደ ባርሴሎና ማቅናት ብችል በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን ባለፈው ጊዜ ስለቅ የገጠመኝን አስታውሼ እሱን መድገም አልፈልግም።”

አርጀንቲናው እግር ኳሰኛ ባርሴሎና እሱን ለመግዛት ተጫዋቾችን መሸጥ አሊያም ደመወዛቸውን መቀነስ እንዳለበት መስማቱን ገልጦ ይህን ማድረግ እንዳልሻተም ገልጧል።

ባርሴሎና በለቀቀው መግለጫ ሜሲ ከካታለኑ ክለብ ግብዣ ቢቀርብለትም ወደ ኢንተር ማያሚ ማቅናት መምረጡን አስታውቋል።

ሜሲ ከማያሚ ጋር የገባው ውል እንደ አዲዳስና አፕል ካሉ ትላልቅ ስሞች ጋር የሚያጣምረው ነው።

ሰባት ጊዜ የዓለም ምርጡ ተብሎ ባለን ደኦር የወሰደው ሜሲ ከዓለም ዋንጫ ስኬቱ በኋላ ስምንተኛ ሊደግም ይችላል የሚል ግምት አለ።

ሜሲ ከአውሮፓ ውጭ እግር ኳስ ሲጫወት ይህ በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ተጫዋቹ ወደ ሳዑዲ አራቢያ አቅንቶ ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ካሪም ቤንዜማን በረብጣ ብር ይቀላቀላል ተብሎ በሰፊው ቢወራም እሱ ግን ወደ አሜሪካ ማቅናትን መርጧል።

ሜሲ፤ ማያሚ ውስጥ የሚያከራው ቤት አለው።

“የገንዘብ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ወደ ሳዑዲ አራቢያ አሊያም ወደሌላ ቦታ አቀና ነበር።”