ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ፡ አርሰናል በፍፁም ቅጣት ፖርቶን አሸንፎ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቀለ
ትናንት ማክሰኞ ምሽት በተከናወኑ የቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፈ ጨዋታዎች አርሰናል እና ባርሴሎና ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀሉ።
ከሦስት ሳምንት በፊት በነበረው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ፖርቶ በሜዳው ባለቀ ሰዓት ጎል አስቆጥሮ አርሰናልን 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።
ትናንት በተደረገው የመልስ ጨዋታ መድፈኞቹ በደጋፊዎቻቸው ፊት በዘጠና ደቂቃ 1 - 0 ማሸነፍ ችለዋል።
ማርቲን ኦዴጋርድ በድንቅ ሁኔታ ያሻገራትን ኳስ ሊያንድሮ ትሮሳርድ ከመረብ አገናኝቷል። በጨዋታው የተቆጠረው ብቸኛ ግብም ይህ ሆኗል።
ትሮሳርድ ከእረፍት በፊት ያስቆጠራት 1 ጎል አርሰናልን ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማስገባት በቂ አልነበረችም።
አርሰናል በኢሚሬትስ ከፖርቶ ባደረገው ጨዋታ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 90 ደቂቃው 1 አቻ በመጠናቀቁ 30 ደቂቃ ተጨምሮ ቡድኖቹ ለ120 ደቂቃ ቢፋለሙም አሸናፊውን መለየት አልተቻለም።
አሸናፊውን ለማወቅ ተፋላሚዎቹን በፍጹም ቅጣት ምት መለየት የግድ ሆኖ ነበር። በዚህም ኮከብ ሆኖ የወጣው የአርሰናል ግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ ነው።
ራያ ከተመቱበት 4 ፍጹም ቅጣት ምቶች ሁለቱን ማዳን ችሏል። በተቃራኒው ፍጹም ቅጣት ምት የመቱት አራቱም የአርሰናል ተጫዋቾች ማስቆጠር ችለው መድፈኞቹ 4 - 2 በሆነ ውጤት በፍጹም ቅጣት ምት ፖርቶን አሸንፎ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
ከጫወታው በኋላ የቢቢሲ እግር ኳስ ጸሐፊ ክሪስ ዊቲ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠውን ዴቪድ ራያን “እጅግ ወሳኝ በሆነ ሰዓት ለአርሰናል ጀግና ሆኖ ተገኝቷል” ሲል ገልጾታል።
ትናንት ምሽት በተካሄደ ሌላኛው ጨዋታ ባርሴሎና የጣሊያኑን ናፖሊን አሸንፎ ከሩብ ፍጻሜው ደርሷል። ባርሴሎና በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ከናፖሊ ጋር 1 አቻ ነበር የተለያየው።
ትናንት በኑካምፕ በሎፔዝ፣ ካንሴሎ እና ሌቫንዶቭስኪ ጎሎች 3-1 ያሸነፈ ሲሆን በድምር ውጤት 4 ለ 2 ናፖሊን አሸንፏል።
ከትናንት ምሽቱ ጨዋታ በኋላ እስካሁን ድረስ 6 ቡድኖችን ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።
ማንችስተር ሲቲ፣ ባየርን ሙኒክ፣ ሪያል ማድሪድ፣ ፒኤስጂ፣ ባርሴሎና እና አርሰናል ተጋጣሚዎቻቸውን በደርሶ መልስ ውጤት ማሸነፍ የቻሉ ቡድኖች ሲሆኑ ዛሬ ምሽት ዶርቱሙን ከፒኤስቪ እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ከ ኢንተር ይገናኛሉ።
ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉት ቡድኖች ተጋጣሚዎቻቸውን የፊታችን አርብ በሚወጣ ዕጣ የሚለዩ ይሆናል።