"በነጮች የተከበበ ጥቁር በግ" ያለበት የልዕልት ዳያና ሹራብ በ1.14 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

ልዕልት ዳያና ሹራቡን ደርባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በርካታ ነጭ በጎች የከበቡት የጥቁር በግ ምስል ያለበት የልዕልት ዳያና ሹራብ ኒው ዮርክ ውስጥ ለጨረታ ቀርቦ በ1.14 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ።

ጨረታው የተከፈተው በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 31 ነው።

ጨረታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች እስኪቀሩት ድረስ ከፍተኛው ተጫራች ለሹራቡ ያቀረበው ዋጋ 200 ሺህ ዶላር ነበር።

ሶዜቢስ የተሰኘው አጫራች ሹራቡ ቢያንስ 50 ሺህ፤ ቢበዛ ደግሞ 80 ሺህ ዶላር ያወጣል የሚል ግምት ነበረው።

ድርጅቱ ጨረታውን ማን እንደረታ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ይህ የልዕልቷ ሹራብ ባለፈው መጋቢት ነው ከአንድ መኖሪያ ቤት ቆጥ ላይ የተገኘው።

“የሕዝብ ልዕልት” እየተባለች የምትጠራው ዳያና ንብረት የነበሩ በርካታ ዕቃዎች ለጨረታ ቀርበው ቢሸጡም ይህ ሹራብ ከፍተኛውን ዋጋ ይዟል።

ፎርድ ኢስኮርት የተሰኘው የዳያና መኪና ባለፈው ዓመት በ806 ሺህ ዶላር መሸጡ አይዘነጋም።

አታላህ ክሮስ የሚባለው ልዕልት ዳያና ብዙውን ጊዜ አንገቷ ላይ የምታደርገው መስቀል ለአሜሪካዊቷ ‘ሪያሊቲ ቲቪ’ ኮከብ ኪም ካርዳሺያን በ203 ሺህ ዶላር ባለፈው ጥር ተሸጧል።

ረብጣ ዶላር ያወጣው ሹራብ ዲዛይን ዳያና በንጉሣዊው ቤተሰብ ውስጥ የነበራትን ሥፍራ የሚያሳይ ነው ተብሎ ይታመናል።

ነገር ግን የፋሽን ታሪክ ተመራማሪዎች እንዲሁ ታዘወትረው የነበረ ሹራብ እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም ይላሉ።

ከማሕበራዊ ሚድያ ዘመን ቀድሞ በፎቶግራፈሮች አማካይን በጋዜጣ የሚወጡ ዜናዎች የዳያናን ሹራብ 'ዋርም ኤንድ ዎንደርፉል' የተሰኘው ሹራብ አምራች እንደሠራው ዘግበው ነበር።

ልዕልቷ ትዳር ከመሠረተች በኋላ ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ሹራቡ እንደተበተነ እና ድጋሚ መሠራት እንዳለበት ለአምራቹ ደብዳቤ ፅፎ ነበር።

ጨረታውን ያከናወነው ድርጅት ቤተ-መንግሥቱ ለሹራብ አምራቹ የፃፈውን ደብዳቤ እንዲሁም ለምትኩ ሹራብ የተፃፈውን የእናመሰግናለን ደብዳቤ በጨረታው አካቷል።

ሹራቡ ትክክለኛው የዳያና ልብስ መሆኑን ለማረጋገጥም ከነቀዳዳው ነው ለጨረታ ያቀረበው።