የጀርመን ቀኝ አክራሪ ፓርቲ ስድስት የአካባቢ ምርጫ እጩዎች በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ሞቱ

የጀርመን ቀኝ አክራሪ ፓርቲ አርማ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Image

በጀርመን ምዕራባዊ ግዛት በቅርብ ለሚካሄደው የአካባቢ ምርጫ ሊወዳደደሩ የነበሩ የጀርመን ቀኝ አክራሪ ፓርቲ ስድስት ዕጩዎች በጥቂት ሳምንታት ውሰጥ መሞታቸው ተገለጸ።

ስድስቱ ዕጩዎች ኤኤፍዲ የተሰኘው የቀኝ አክራሪ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ በምዕራባዊ ጀርመን ኖርዝ ራይን ዌስት ፋሊያ በተሰኘችው ግዛት በመጪው መስከረም በሚደረገው ምርጫ ተወዳዳሪ ነበሩ።

ፖሊስ ከፖለቲከኞቹ ሞት ጋር ተያይዞ ግድያን የሚያመለክት ምንም አጠራጣሪ ነገር እንደሌለም አስታውቋል።

የዕጬዎቹን ሞት ተከትሎ አዳዲስ የምርጫ ካርዶች መታተም እንዳለባቸው እንዲሁም በፖስታ ድምጻቸውን የላኩ መራጮች እንደገና እንዲመርጡ ይደረጋል ተብሏል።

18 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ኖርዝ ራይን ዌስት ፋሊያ ግዛት መስከረም 4/ 2018 ዓ.ም በምታካሂደው የአካባቢ ምርጫ 20 ሺህ ዕጩዎች እንደሚወዳደሩ ተገልጿል።

የዕጩዎቹ ሞት በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኗል።

የግዛቲቷ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ 'ግሪንስ ኤንድ ሶሻል ዴሞክራትስ' የተሰኘው ፓርቲን ጨምሮ የሌሎች ፓርቲዎች ዕጩዎች መሞታቸውን ጠቁሟል።

ኤኤፍዲ በየካቲት ወር በተደረገው የፌደራል መንግሥት ምርጫ የጀርመን ሁለተኛው ትልቅ ፓርቲ መሆን ችሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአገሪቱ የስለላና የደህንንት ኤጀንሲ ፓርቲውን በቀኝ ክንፍ አክራሪ ጽንፈኝነት ፈርጆ የነበረ ሲሆን በፍርድ ቤት በቀጠለው አቤቱታ ምክንያት ይህንን ፍረጃ በጊዜያዊነት አቁሞታል።

ሆኖም በሶስት የጀርመን ምስራቃዊ ግዛቶች ኤኤፍዲ አሁንም በጽንፈኝነት እንደተፈረጀ ነው።

መጀመሪያ የፓርቲው አራት ዕጩዎች ሞት ዜና የወጣ ሲሆን ተከትሎም ሁለት ተጠባባቂ ዕጩዎች ሞተዋል መባላቸውን ተከትሎ በርካታ የሴራ ጽንሰ ሃሳቦች በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ።

የፓርቲው ተባባሪ መሪ አሊስ ዌይደል እነዚህ ሴራዎችን ለማስተባባል ሳይሞክሩ በጡረታ ላይ ያሉት የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ስቴፋን ሆምበርግ የሞቱ እጬዎች ቁጥር "የማይታመን ነው" ሲሉ የለጠፉትን ጽሁፍ አጋርተዋል።

ከዕጩዎች ሞት ጋር ተያይዞ እየተነሱ ያሉ አሉባልታዎችን የተጠየቁት በግዛቲቷ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኔት ኬይ ጎትስቻልክ "በአሁኑ ወቅት ያለኝ ከፊል መረጃ ነው።ሆኖም እየተነሱ ያሉ ጥርጣሬዎችን የሚደግፍ አይደለም" ብለዋል።

ፖለቲከኛው "ወደ ሴራ ትንተና ከመገባቱ በፊት ሞቶቹ ላይ ምርመራ እንዲደረግ" የፓርቲያቸው ፍላጎት እንደሆነ ለፖለቲኮ በርሊን ፖድካስት ተናግረዋል።

ፖሊስ አራቱ ዕጩዎች የሞቱት በተፈጥሯዊ ምክንያት ወይም ከቤተሳባቸው የግል መረጃ መጠበቅ ጋር በተያያዘ ምክንያት እንደሆነ ለጀርመኑ የዲፒኤ የዜና ወኪል አስታውቋል።

በቀጣዩም የሞቱት ሁለት እጩዎች መንስዔው በተመሳሳይ መሆኑ ተገልጿል።

ከሶስት ዓመት በፊት በተካሄደው ባለው የአካባቢ ምርጫ ኤፍዲ በጀርመን የኢንዱስትሪ ማዕከል በምትባለው ሩሁር ቫሊ ማግኘት የቻለው ድምጽ 5.4 በመቶ ብቻ ነበር።

ሆኖም በዘንድሮው የካቲት ወር ላይ በነበረው የፌደራል ምርጫ ፓርቲው 16.8 በመቶ ማግኘት የቻለ ሲሆን ይህንንም ድል በአካባቢ ምርጫ እንደሚደግመው የህዝብ አስተያየቶች ያሳያሉ።

ጸረ ስደተኛ ፖሊሲ ያለው ይህ ፓርቲ አሜሪካዊው ቱጃር ኤለን መስክን ጨምሮ በርካታ የቀኝ አክራሪዎች ድጋፍ አግኝቷል።