እንደ ተዋጊ ጀቶች፣ታንኮች እና የጦር መርከቦች ያሉ ከባድ የጦር መሣሪያዎች እና የአየር ንብረት ስጋት

የፎቶው ባለመብት, Wojtek Radwanski/AFP via Getty Images
በዓለም ላይ ያሉ ጦሮች በአስቸኳይ መታጠቅ እንዳለባቸው እያሳሰቡ ነው።
ይህ እያሉ ያሉት የአየር ንብረት ቀውስ ዋነኛ የደኅንነት ስጋት በሆነበት እና የጦር መሣሪያዎች የካርቦን ልቀት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባወጡት አዲስ ሪፖርት ወታደራዊ ወጪ መጨመር የአየር ንብረት ቀውስን ሊያባብስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በዓለማችን የተራዘሙ ግጭቶች መስፋፋት ወደፊት ወታደራዊ ወጪዎች ለመጨመራቸው እና የካርቦን ልቀት ለመባባሱ አመላካች ነው።
አንዳንድ ባለሙያዎችም የአየር ንብረት ቀውስን ለመዋጋት መዋል ያለበት ሃብት ወደ ወታደራዊ ኃይል መዞሩ አሳስቧቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Zhang Wei/China News Service/VCG via Getty Images
የጦር ኃይሎች ምን ያህል ካርቦን ይለቃሉ?
በዓለም ላይ በወታደራዊ ኃይሎች ምክንያት ምን ያህል የካርቦን ልቀት እንደተፈጠረ ለክቶ እና መዝኖ የሚያሳይ የተረጋገጠ አሃዝ የለም።ሆኖም አንዳንድ መንግሥታት አሃዞችን አጋርተዋል።
አንዳንድ ባለሙያዎችም ይህንን አሃዝ በማስላት እና ትንበያዎች ላይ በመመስረት ዓለም አቀፍ መረጃን አቅርበዋል።
እንደ የተመድ ዋና ጸሐፊ አዲስ ሪፖርት ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወታደራዊው ዘርፍ የሚወጣውን የካርቦን ልቀት የሚያሳየው ጥሩ ግምት ከጠቅላላው ዓለም አቀፍ የግሪንሃውስ ጋዝ ልቀት በ3.3 እና በ7 በመቶ መካከል እንደሚደርስ ያሳያል።
ይህ ማለት በዓለም ላይ ያለው የጦር ኃይል እንደ አንድ አገር ቢታሰብ፣ ከቻይና፣ አሜሪካ እና ሕንድ በመቀጠል አራተኛው ከፍተኛ የካርቦን ልቀት ያለው አገር እንደሚሆን በአውሮፓውያኑ 2020 በግጭቶች እና አካባቢ ላይ የተሰራ ጥናት ያስረዳል።
ጥናቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በአካባቢ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ላይ የሚሰራው በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት እና በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ በሚሰራው ገለልተኛ በሆነው ግሎባል ሪስፖንሲቢሊቲ ተመራማሪዎች በጥምረት የተሰራ ነው።
በዓለም ላይ የጦር በጀት የመጨመሩ ሁኔታ እየባሰ እንደሚሄድም ይኸው ጥናት አመልክቷል።
ዓለም አቀፍ የጦር ወጪ በ2024 ወደ 2.7 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ9.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ይህም የቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃ ወዲህ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን በግጭቶች ላይ ጥናቶችን የሚያካሂደውና በስቶክሆልም የሚገኘው ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲቲዩት [ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም) ገልጿል።
ተቋሙ በጥናቱ በ2024 ከ100 በላይ አገራት ወታደራዊ ወጪያቸውን መጨመራቸውን ያሳየ ሲሆን በተለይ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ፈጣን ጭማሪ መታየቱን ጠቁሟል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እአአ በ2035 አባል አገራቱ የመከላከያ እና የፀጥታ ወጪያቸውን ከ2 በመቶ ወደ 5 በመቶ እንደሚጨምሩ አስታውቋል።
ይህ የተገለጸው ከኔቶ አባል አገራት የጦር ኃይሎች የሚወጣው የካርቦን ልቀት ከ2021 እስከ 2023 ባሉት ዓመታት ብቻ በ30 ሚሊዮን ቶን በጨመረበት ወቅት ሲሆን በዚሁ ተመሳሳይ ወቅትም ወታደራዊ ወጪዎች ጨምረዋል።
ይህ ማለት አገልግሎት ከሚሰጡ በግምት ከስምንት ሚሊዮን በላይ መኪናዎች ጋር የሚስተካከል እንደሆነ በዘላቂ ልማት ላይ የሚሰራው ትራንስናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Hakan Akgun/Anadolu via Getty Images
በከፍተኛ ደረጃ በካይ ከሆኑት ጥቂቶቹ
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከባዱ ፈተና እንደ ተዋጊ ጀቶች፣ታንኮች፣ የጦር መርከቦች እና ባሕር ሰርጓጆች ያሉ ከባድ የጦር መሣሪያዎች የካርቦን ልቀታቸውን እንዲቀንሱ ማድረግ ነው። ምክንያቱም እነዚህ የጦር መሣሪያዎች አገልግሎት ለመስጠት የሚጠቀሙት ከፍተኛ ነዳጅ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ኃይል ከሚያስፈልጋቸው ማሽኖች መካከል ተዋጊ ጀቶች እንደሚገኙበትም ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።
በአሜሪካ ጦር ውስጥ ጀቶች የሚጠቀሙት ነዳጅ አሁን ላይ የአሜሪካ የጦር መሥሪያ ቤት ተብሎ የተሰየመው የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት፣ ባለፉት አምስት አስርት ዓመታት ከተጠቀመው አጠቃላይ ኃይል 55 በመቶውን እንደሚይዝ ጥናት አመልክቷል።
በ2022 በኔቸር ጆርናል ላይ የታተመ ጥናት እንደገለጸው አንድ የአሜሪካ አየር ኃይል ኤፍ -35 ተዋጊ ጀት በአንድ ጊዜ 185 ኪሎሜትር ርቀት ሲበር የሚለቀው በካይ ጋዝ አንድ የዩኬ የቅኝት መኪና በዓመት ከሚለቀው ካርቦን ጋር የሚስተካከል ነው።
ጥናቱ በየዓመቱ በአሜሪካ ጦር ጥቅም ላይ የሚውል ጀት በአገሪቱ ያሉ 6 ሚሊዮን የመንገደኞች ተሽከርካሪዎች ከሚለቁት ካርቦን ጋር እኩል መሆኑንም ጥናቱ አክሏል።
ይህም ቢሆን ግን አሜሪካ ወታደራዊ በጀቷን ቀድሞ ከነበረው በ2024 በ5.7 በመቶ መጨመሯን እና ይህም በዓለም ላይ ለመከላከያ ኃይል የሚወጣ ከፍተኛ ወጪ መሆኑን በስቶክሆልም የሚገኘው ዓለም አቀፉ የሰላም ምርምር ተቋም ገልጿል።
የግጭት እና የአካባቢ ታዛቢ የሆኑት ዳግ ዌር "የጦር መሣሪያዎችን ክምችት ለመጨመር ምርቶችን ማስፋፋት እየጨመረ ቢሆንም እነዚህ ምርቶች የካርቦን ልቀታቸውን ዝቅተኛ ለማድረግ የሚደረገው ቴክኖሎጂያዊ ጥረቶች ግን ውስን ናቸው" ብለዋል።
ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች . . .
ወታደራዊ ወጪዎች መጨመራቸው ለካርቦን ልቀት ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም ወታደራዊ ዘርፉን ከበካይ ጋዝ ነጻ ለማድረግ እቅድ ይኖረው እንደሁ ቢቢሲ የአሜሪካ የጦር መሥሪያ ቤትን ጠይቋል።
ለጥያቄው የፔንታገን ኃላፊ ቃል አቀባይ ሲን ፓርኒል በኢ-ሜይል ምላሽ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በምላሻቸው " የአሜሪካ የጦር መሥሪያ ቤት ከጦርነት ተልዕኮ ጋር የማይጣጣሙ የአየር ንብረት ፕሮግራሞችን እና ኢንሺየቲቮችን ያስወግዳል" ብለዋል።
ጨምረውም " ገዳይነት፣ በዋና ግንባሮች የጦር ወጊያን እና ዝግጁነትን ለማሻሻል ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው። ይህንንም በሦስት መንገዶች እያደረግን ነው። አንደኛው የተዋጊውን ሥነ ምግባር በማላበስ፣ ወታደራዊ ኃይላችንን እንደገና በመገንባት እና መከላከያን እንደገና በማቋቋም" ሲሉ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ለኔቶም ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።ሆኖም ድርጅቱ እየጨመረ የመጣውን የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ያደረገው ጥረት ውጤታማ አለመሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።
በብራስልስ በሚገኘው የጦር እና ንግድ ማኅበራት ድርጅት ውስጥ የፖሊሲ ከፍተኛ ኦፊሰር የሆኑት ዲሚትራ ኮቶውዚ እንደሚሉት" አሁን ላይ ለወታደራዊ ወጪ ከሚመደበው ገንዘብ አንጻር የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ብዙ አይደለም።"
" የአውሮፓ የመከላከያ ኢንደስትሪዎች ዘላቂነትን እና የኃይል አጠቃቀምን ለማቀናጀት በእቅዳቸው ውስጥ ማካተት ቢጀምሩም አሁን ላይ የሚመረቱ የመከላከያ ሥርዓቶችን ተግባር ላይ ለማዋል ዓመታትን ይወስዳል" ብለዋል ኮቶውዚ።

የፎቶው ባለመብት, Syed Mahamudur Rahman/NurPhoto via Getty Images
የጦርነት ዳፋ
ግጭቶች በአየር ንብረት ላይ የሚያስከትሉትን ጉዳት በትክክል መገመት ባይቻልም አሁን ላይ የሚካሄዱ ጦርነቶች በአካባቢ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ አሳይተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2024 የወጣ አንድ ሪፖርት በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ 175 ሚሊዮን ቶን ግሪንሃውስ ጋዝ እንደተለቀቀ ይገመታል።
ግንቦት ላይ የታተመ ሌላ አንድ ጥናት ደግሞ በእስራኤል እና ጋዛ ጦርነት በቀጥታ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ወደ 1.9 ሚሊዮን ቶን ካርበን ተለቋል። ይህ 36 አገራት እና ግዛቶች በዓመት ካላቸው ልቀት የሚልቅ እንደሆነ ጥናቱ ያስረዳል።
የብሪታኒያ የቀድሞ ጀነራል እና የቀድሞ የኔቶ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሪቻርድ ኑጊ" ፈጣን የጦር ጀት ወይም ታንክ ከበካይ ጋዝ ልቀት ነጻ የሆነ ቴክኖሎጂ እስካሁን የለንም" ብለዋል።
በመሆኑም ቴክኖሎጂ ካልተቀየረ በስተቀር እውነታውን መካድ እንደማይቻል እና በሚፈለገው መጠን የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ እንደማይቻል ኑጊ አክለዋል።
በሌላ በኩልም ለመከላከያ ኃይል ብዙ ገንዘብ መመደብ ማለት የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለመግታት በቂ ገንዘብ የለም ማለት ነው።
መስከረም ላይ የወጣው የተመድ ዋና ጸሐፊ ሪፖርት ለመንግሥታቱ ድርጅት የዘላቂ የልማት ግቦች ያለው ዓመታዊ የበጀት ጉድለት 4 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ለኃይል እና ለአየር ንብረት ሥራዎች ተብሎ የተመደበ መሆኑን አሳይቷል።
ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ወጪ በ2035 6.6 ትሪሊየን ዶላር ሲደርስ፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያጋጥመው የበጀት ጉድለት ወደ 6.4 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ሪፖርቱ አስጠንቅቋል።
ሪፖርቱ ጨምሮም የዓለማችን ሃብታም አገራት፣ ለአየር ንብረት ቀውስ ተጋላጭ ለሆኑ አገራት ከሚሰጡት ገንዘብ ከ30 እጥፍ በላይ በራሳቸው ጦር ላይ እንደሚያውሉ ገልጿል።
በቅርቡ በአዘርባጃን በተካሄደው የኮፕ29 የአየር ንብረት ድርድር፣ ያደጉ አገራት በ2035 በዓመት 300 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመስጠት ቢስማሙም በማደግ ላይ ያሉ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን አስከፊ ተፅዕኖ ለመዋጋት በዓመት ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በአዘርባጃን፣ ባኩ በተካሄደው በዚህ የኮፕ29 የአየር ንብረት ድርድር፣ የፓናማ የአየር ንብረት ለውጥ ልዩ ተወካይ የሆኑት ጁዋን ካርሎስ፣ "የዓለም የጦር ወጪ 2.5 ትሪሊየን ዶላር ደርሷል፤ እርስ በእርስ ለመገዳደል ብዙ አይደለም፤ ሕይወትን ለማዳን አንድ ትሪሊየን ዶላር መጠየቅ ግን ምክንያታዊ አይደለም" ሲሉ ወታዳራዊ ወጪን እና የአየር ንብረት ቀውስን ለመግታት እየተሰጠ ያለውን ትኩረት አነጻጽረዋል።
ሆኖም አሁንም ቀድሞ የተገቡ ቃሎች ተግባራዊነት ላይም ጥርጣሬ አለ።
የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ 11 ለጋሽ ድርጅቶች የልማት ድጋፋቸውን እንደሚያቋርጡ አስታውቀዋል።ይህ የውጭ ድጋፍ ከ2025 እስከ 2027 ድረስ ያለውን ለአየር ንብረት የሚውል የገንዘብ ድጋፍን የሚያካትት ነው።
ለምሳሌ ዩናይትድ ኪንግደም በ2027 ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢዋ ትሰጥ የነበረውን 0.5 በመቶ የእርዳታ ወጪን ወደ 0.3 በመቶ በመቀነስ የመከላከያ ኃይሏ ላይ የምታፈሰውን ገንዘብ እንደምትጨምር ገልጻለች።
" ወደድንም ጠላንም የጦር ኃይል ይኖረናል" ብለዋል ገነራል ኑጊ።
" ወታደራዊ ኃይሉ በጦርነት ወቅት የካይ ጋዝ ልቀት እንዳይጨምር ማድረግ የሚችለው በመጀመሪያ ደረጃ የማይነካ ጠንካራ ጦር ሲኖረው ነው። ኔቶ እና ብሪታንያ ለማድረግ እየሞከሩ ያሉትም ይህንን ነው" ሲሉም አክለዋል።
እዚህ ላይ ጠንካራ የጦር ኃይል መገንባት ሰዎችን አስከፊ ከሆነው የአየር ንብረት ተፅዕኖ ይጠብቃል ወይስ ችግሩን ያባብሳል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።















