ሩሲያ እና ዩክሬን በመጀመሪያው ድርድራቸው የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, TURKISH FOREIGN MINISTER
በሦስት ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ለንግግር የተቀመጡት የሩሲያ እና ዩክሬን ባለሥልጣናት የጦር እስረኞችን ለመለዋወጥ ከስምምነት ላይ ደረሱ።
በቱርክ እና በአሜሪካ ግፊት ኢስታምቡል ውስጥ ከአርብ ጀምሮ ለንግግር የተቀመጡት የሁለቱ አገራት ተወካዮች ባደረጉት የመጀመሪያ ቀን ንግግር በውጥረት የተሞላ እንደነበር ተነግሯል።
ከዩክሬን ልዑካን መካከል ግማሽ የሚሆኑት አገራቸው በጥቃት ስር መሆኗን ለማመልከት ወታደራዊ ልብስ ለብሰው የተገኙ ሲሆን፣ ንግግሩ የተጀመረው በተደራዳሪዎቹ መካከል መጨባበጥ ሳይኖር ግራ እና ቀኝ ተራርቀው በተቀመጡ ጠረጴዛዎች ዙሪያ ነበር።
በድርድሩ ጅማሬ ላይ የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ባደረጉት ንግግር ልዑካኑ ወደ ሰላም ወይም ወደ ተጨማሪ ሞት እና ውድመት የሚወስዱ ሁለት አማራጮች ብቻ እንዳላቸው አሳስበው ነበር።
ለሁለት ሰዓታት ብቻ በቆየው ንግግር ወቅትም አለመግባባቶች ተፈጥረዋል። ሩሲያ "አዲስ እና ተቀባይነት የሌላቸው ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርባለች" ሲሉ አንድ የዩክሬን ባለሥልጣን ተናግረዋል።
ይህም ተኩስ አቁም ላይ ለመድረስ ዩክሬን ከራሷ ግዛት ወታደሮቿን እንድታስወጣ ጭምር የሚጠይቅ ቅድመ ሁኔታ መቅረቡን አመልክተዋል።
ሁለቱ አገራት በጣም አስፈላጊ በሆነው ተኩስ ማቆም ላይ ከስምምነት ለመድረስ ባይችሉም፤ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ የጦር ምርኮኞችን ለመልቀቅ ተስማምተዋል።
"ይህ አስቸጋሪ በነበረው የመጀመሪያ ቀን ጥሩ ውጤት ነው" ያሉት የዩክሬን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርሂያ ኪስሊይስቲያ "ለአንድ ሺህ ዩክሬናውያን ቤተሰቦች መልካም ዜና ነው" ብለዋል።
የእስረኞች ልውውጡ በቶሎ የሚከናወን መሆኑን የጠቀሱት የዩክሬንን ልዑካን የሚመሩት የመከላከያ ሚኒስትር ሩስተም ኡሜሮቭ "እስካሁን ቀኑን ባናሳውቅም መቼ እንደሚሆን እናውቃለን" ብለዋል።
ጨምረውም ቀጣዩ እርምጃ መሆን ያለበት የሁለቱ አገራት መሪዎች የሚያደርጉት የቀጥታ ንግግር መሆኑን ገልጸዋል።
የሩሲያን ልዑካን የመሩት የፕሬዝዳንት ፑቲን ረዳት ቭላድሚር ሜዲኒስኪ ቡድናቸው በንግግሩ ሂደት መርካቱን እና ግንኙነቱን ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ነገር ግን በዩክሬናውያን እና በአውሮፓውያን ወዳጆቻቸው ዘንድ ሩሲያ ወደ ድርድሩ የመጣችው ተኩስ እንዲቆም ያለውን ዓለም አቀፍ ግፊትን ለማለዘብ እና የተጣሉባትን ማዕቀቦች ለማላላት ዲፕሎማሲን ለጊዜ መግዣነት እየተጠቀመች ነው ነው የሚል ስጋት አለ።
ሁለቱ አገራት ለንግግር ቱርክ ውስጥ በተቀመጡበት ጊዜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወሳኙ ንግግር በእሳቸው እና በፕሬዝዳንት ፑቲን መካከል የሚደረገው ነው ብለዋል።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ፑቲን እና እኔ እስክንገናኝ ድረስ ምንም ነገር አይፈጠርም" በማለት በሁለቱ አገራት ንግግር ውስጥ ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ነገር ግን ፑቲን እና ትራምፕ መቺ እንደሚገናኙ የታወቀ ነገር የለም። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ንግግር "በእርግጥም አስፈላጊ" መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ለማዘጋጀት ግን ጊዜ እንሚፈልግ ተናግረዋል።
በፕሬዝዳንት ትራምፕ እና በፕሬዝዳት ፑቲን መካከል ንግግር የሚደረግ ከሆነ የዩክሬኑ አቻቸው የመሳተፋቸው ሁኔታ ግን እርግጠኛ አይደለም።















