የሩሲያ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኙ

የሩሲያ እና ዩክሬን አመራሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በሦስት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኙ።

ባለሥልጣናቱ ውይይት ለማድረግ በቱርክ ኢስታምቡል ሲገናኙ ሳይጨባበጡ ነው ወደ ታቀደው ንግግር የገቡት።

በጦርነት ላይ የሚገኙት አገራት የሚያደርጉት ውይይት ጉልህ የሆነ ውጤት ያመጣል ተብሎ ባይጠበቅም ትልቅ እርምጃ መሆኑን ተንታኞች ተናግረዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ውይይቱን እያስተባበሩ ያሉት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊደን እና ሌሎችም ባለሥልጣናት ናቸው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር "በተቻለው ፍጥነት" መገናኘት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ፑቲን ከቱርክ እና ከዩክሬን አመራሮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው ትራምፕ ፑቲንን ማናገር የሚፈልጉት።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊደን የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአፋጣኝ መድረስ የሚኖረውን ጠቀሜታ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።

ዩክሬን ቅድሚያ የምትሰጠው የውይይቱ ግብ ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠለት የተኩስ አቁም መሆኑን አስታውቃለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያ በበኩሏ ግቧ ዘላቂ ሰላም ማምጣት እና "ችግሩን ከሥሩ መንቀል" መሆኑን ይፋ አድርጋለች።

ተንታኞች እንደሚሉት ሩሲያ ያላት የተኩስ አቁም ፍላጎት ሳይሆን የጦርነቱ መነሻ የሆነውን ምክንያት መቅረፍ ይሆናል።

ይህም ከዩክሬን ሉዓላዊ አገር ሆና መቀጠል ጋር የሚጻረር ይሆናል። የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ማኅበርን (ኔቶ) መቀላቀልም አትችልም።

እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሊቀበሉ አይችሉም።

በሌላ በኩል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ማርኮ ሩቢዮ በቱርክ በሚካሄደው የዩክሬን እና የሩሲያ የሰላም ድርድር ብዙ ተስፋ እንደሌላቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

ለውጥ እንዲመጣ ዶናልድ ትራምፕ እና ቭላድሚር ፑቲን መገናኘታቸው አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሩቢዮ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን አመራሮች ጋር በኢስታንቡል ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት የዩክሬን አጋር የሆኑ ምዕራባውያን አገራት ሩሲያ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት እንድትመጣ ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ መስጠት እንደሚቀጥሉ እና በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉም አስታውቀዋል።

ዩክሬን እና ሩሲያ ወደ ውይይት ጠረጴዛው ከመምጣታቸው አስቀድሞ የሚደርሱበት ስምምነት ቅድመ ሁኔታ ያለው ይሁን ወይንስ ቅድመ ሁኔታን ከግምት የማይስገባ በሚለው ላይ የተለያየ አቋም አንፀባርቀዋል።

ትራምፕ በውይይቱ ላይ አለመኖራቸው የሚጠበቀውን ያህል ድርድሩን ፍሬያማ እንዳይሆን ያደርጋል የሚልም ግምት አለ።

ዜሌንስኪ "ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተኩስ አቁም" ለማድረግ ሩሲያ የማትስማማ ከሆነ "ፑቲን ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት የለውም" ብለው እንደሚወስዱት ተናግረዋል።

ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር ዜሌንስኪ ቢገናኙም ፑቲን በዚህ መድረክ አለመኖራቸው ውይይቱ የሚኖው ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተንታኞች ገልጸዋል።

ቱርክ ውይይቱን "በ360 ዲግሪ" የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመመራት ውይይቱን እንደምታሳልጥ አስታውቃለች።