በናይጄሪያ በሠርግ፣ ቀብር እና ሆስፒታል ላይ በተፈጸሙ የፍንዳታ ጥቃቶች በርካቶች ተገደሉ

የናይጄሪያ ጦር የቦኮ ሃራምን ሲዋጋ ቆይቷል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የናይጄሪያ ጦር ቦኮ ሃራም የተባለውን እስላማዊ ቡድን ሲዋጋ ቆይቷል

በናይጄሪያዋ ቦርኖ ግዛት አጥፍቶ ጥፊዎች በሠርግ ቤት፣ በቀብር ወቅት እና ሆስፒታል ላይ በፈጸሙት የተቀናጀ ጥቃት ቢያንስ 18 ሰዎች ተገደሉ።

የቦርኖ ግዛት ኃላፊዎች ትናንት ቅዳሜ ሰኔ 22/2016 በተፈጸመው ጥቃት ከሟቾቹ በተጨማሪ ቢያንስ 30 ሰዎች ቆስለዋል ብለዋል።

ከአጥፍቶ አጥፊዎቹ አንዱ እየተካሄደ በነበረ የሠርግ ስነ-ሰርዓት ላይ በፈጸመው ጥቃት ስድስት ሰዎችን ገድሏል።

የግዛቷ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ በጋዎዛ ከተማ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕይወታቸውን ካጡት መካከል ሕጻናት፣ ሴቶች እና አንዲት ነብሰ ጡር ሴት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

የግዛቲቱ ኃላፊዎች የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ጨምረው አሳስበዋል።

ቦርኖ ግዛት ባለፉት 15 ዓመታት በእሰላማዊ ቡድኑ ቦኮ ሃራም ስትታመስ ቆይታለች። በእስላማዊ ቡድኑ ጥቃት ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ የሚገመት ሲሆን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

ቦኮ ሃራም እአአ 2014 ላይ ከ270 በላይ ሴት ተማሪዎችን በቦርኖ ግዛት ከሚገኘው ትምህርት ቤት አግቶ ከወሰደ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረትን ስቧል።

የትናንቱን ጥቃት ቦኮ ሃራም እንደፈጸውም ቢታመንም እስካሁን ድረስ እስላማዊ ቡድኑ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን አልወሰደም።

ጥቃቱ የተፈጸመባት ጋዎዛ ከተማ እአአ 2014 በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ስር የነበረች ሲሆን ከአንድ ዓመት ጠንካራ ውጊያ በኋላ የናይጄሪያ መንግሥት ታጣቂዎቹን ከከተማዋ ማስወጣት ችሎ ነበር።

ይሁን እንጂ ቡድኑ በከተማዋ እና በከተማዋ ዙሪያ ጥቃቶችን እና እገታዎችን ሲፈጽም ቆይቷል።

ቦኮ ሃራም እአአ 2002 ላይ ሲመሰረት ትኩረት ያረገው የምዕራብውያኑንን ትምህርት መቃወምን ነበር። ይሁን እንጂ እአአ 2009 ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጀምሮ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ለእስላሚክ እስቴት ታማኝነቱን ገልጿል።

የናይጄሪያ መንግሥት ይህንን በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥቃቶችን ሲፈጽም የቆየን ታጣቂ ቡድን ለማስወገድ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

የአገሪቱ ጦር ባደረጋቸው ዘመቻዎች ቡድኑ ይዟቸው የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቁን ቢገልጽም የቡድኑ ህልውና ግን አላከተመም። አሁንም ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየሰነዘረ ይገኛል።