የማሊው መሪ በተገደሉት የመከላከያ ሚኒስትር ቦታ ራሳቸውን ሾሙ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የማሊው ወታደራዊ መሪ ጄነራል አሲሚ ጎይታ ከሳምንት በፊት በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት የተገደሉትን የመከላከያ ሚኒስትርነት ቦታን ጠቅልለው ያዙ።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ እስላማዊ እና ተገንጣይ አማጺያን በጥምረት የከፈቱትን ጥቃት ተከትሎ ማሊ በከፍተኛ የደኅንነት ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

በጥቃቱ ወቅት በዋና ከተማዋ ባማኮ አቅራቢያ በሚገኘው የመከላከያ ሚኒስትሩ ሳዲዮ ካማራ መኖሪያ ቤት ላይ ኃይሎቹ ቦምብ በጫነ መኪና በፈጸሙት የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ባለሥልጣኑ መገደላቸው ተነግሯል።

ትናንት ሰኞ በማሊ ቴሌቪዥን ላይ በተነበበው መግለጫ ወታደራዊው መሪ ጄነራል ጎይታ የሟቹን ሚኒስትር ቦታ ደርበው መያዛቸው ተገልጿል።

የፕሬዝዳንትነት እና የመከላከያ ሚኒስትርነት ሥልጣን በጄነራሉ ቁጥጥር ሥር መግባቱ መንበራቸው በታጣቂዎች ስጋት ውስጥ በመውደቁ የበላይነታቸውን ለማጠናከር የተወሰደ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ተገንጣዩ የአዛዋድ ነጻነት ግንባር እና ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለው ጄኒም የተባለው እስላማዊ ቡድን በጥምረት በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች ላይ ከባድ ጥቃት ፈጽመዋል።

ከዚያ ጊዜ አንስቶም አማጺያኑ በዋና ከተማ እና በሌሎች የማሊ ከተሞች ላይ ከፊል ዕቀባ ጥለዋል።

የተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ በመሆኑ የማሊ እና የአጋሯ የሩሲያ ኃይሎች ከሰሜናዊዋ የኪዳል ከተማ እንዲወጡ አድርጓል። ይህም ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን የመጣው በጄነራሉ የሚመራ መንግሥት ኃይሎችን ጥንካሬ ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል።

ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ የማሊ ባለሥልጣናት በአማጺያኑ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ በርካታ ወታደሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታውቀዋል።

የማሊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ የቀድሞ እና በሥራ ላይ ያሉ ወታደራዊ መኮንኖች በአማጺያኑ ጥቃት ዕቅድ እና በመፈጸሙ ሂደት ውስጥ ተባባሪ መሆናቸው በምርመራ እንደተደረሰበት አመልክቷል።

የማሊ ባለሥልጣናት የተከፈተባቸውን ጥቃት ለመመከት ከጎረቤት ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ ኃይሎች ጋር በመጣመር በአማጺያኑ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።

ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ የሚመሩት በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጡ ወታደራዊ መሪዎች ነው። አገራቱ የቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሳይ ወታደሮችን በማስወጣት ከሩሲያ ጋር ወዳጅነት ከመመሥረታቸው በተጨማሪ በአካባቢያቸው ያሉ ታጣቂዎችን ለመዋጋት የጋራ ወታደራዊ ትብብር ፈጥረዋል።

ቢሆንም ግን በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች የሚፈጽሙት ጥቃት የቀጠለ ሲሆን፣ የሦስቱ አገራት ሠፊ ግዛት ከመንግሥታቱ ቁጥጥር ውጪ በአማጺያን ተይዘው ይገኛሉ።